የመጀመርያው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በነሐሴ ወር ይካሄዳል

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበር (ሴካፋ) ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዘጋጀው የሴቶች ዋንጫ በነሐሴ ወር በዩጋንዳ አዘጋጅነት ይደረጋል።

ውድድሩ ከጥቂት ወራት በፊት በፀደቀውና ለሴቶች እና ለታዳጊዎች እግር ኳስ ትኩረት በሚሰጠው የሴካፋ የ5 ዓመት ዕቅድ መሠረት የሚደረግ ሲሆን ሁሉም የሴካፋ አባል ሃገራት በውድድሩ እንደሚሳተፉ መግለፃቸውን የማህበሩ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ አስታውቀዋል።

“ብዙ ሰዎች በምስራቅ አፍሪካ ስላለው ደካማ የሴቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴ ሲናገሩ እንሰማለን። በአዲሱ የ5 ዓመት ዕቅድ በክፍለ አህጉሪቱ ያለውን የሴቶች እግር ኳስ ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን መስራት ይኖርብናል። ከነዚህ ስራዎች አንዱ ይህንን ውድድር ማዘጋጀት ነው። ተሳታፊ ቡድኖች በቂ ዝግጅት በማድረግ ጥሩ ፉክክር ያሳዪናል ብዬ እጠብቃለሁ” ሲሉ ነው ዋና ፀሃፊው የተናገሩት።

ሴካፋ እ.ኤ.አ. በ2007 ከፊፋ የተሠጠውን የ25 ሺህ ዶላር ድጋፍ በመጠቀም የሴቶች ውድድር ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም አዘጋጅ ሃገር ዛንዚባር በመጨረሻ ሰዐት ራሷን በማግለሏ ምክኒያት ሳይሳካ ቀርቷል። ዘንድሮ ተመሳሳይ ነገር እንደማይፈጠር እና ዩጋንዳ ውድድሩን ለማዘጋጀት ከወዲሁ ዝግጅቷን ማጠናቀቋን የሃገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ሞስስ ማጎጎ ተናግረዋል። ፕሬዘዳንቱ ዩጋንዳ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ማድረግ መቻሏ የሴካፋ ውድድርን በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት እንደሚረዳት ነው የገለፁት።

የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን በድምር ውጤት በማሸነፍ ለካሜሮኑ የአፍሪካ የሴቶች ዋንጫ ማለፍ የቻለችው ብቸኛዋ የሴካፋ ሃገር ኬንያ ውድድሩን ለዝግጅት የምትጠቀምበት ሲሆን ዋንጫውን ለማንሳትም ቅድመ ግምቱን አግኝታለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *