በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሣኔ ተላለፈ

(የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መግለጫ)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲኘሊን ኮሚቴ ሚያዚያ 09 ቀን 2008 ዓ.ም የቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ ክለቦች የኘሪሚየር ሊግ ጨዋታ በተካሄደበት ወቅት በአዲስ አበባ ስታዲየም የተከሰተውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል በጥልቀት ከመረመረ በኋላ የቅጣት ውሣኔ አስተላልፏል፡፡

በእዚሁ መሠረት በዕለቱ ለተፈጠረው የደጋፊዎችና የንብረት ጉዳት እንዲሁም ለሁለተኛው የጨዋታ ጊዜ መዘግየት ሁለቱ ክለቦች ተጠያቂ ሆነው በመገኘታቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ 12000.00 /አሥራ ሁለት ሺህ ብር/ አዳማ ከተማ 5000.00 /አምስት ሺህ ብር እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፡፡

የዲስኘሊን ኮሚቴው ከጨዋታው ታዛቢ በቀረበለት ሪፖርት መሠረት የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ንብረት ማውደማቸውን እና በግለሰቦች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ለማረጋገጥ ከመቻሉም በላይ በዕለቱ ለተሰባበሩት 119 ወንበሮች የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ እንዲሁም በሁለት የቁም መፀዳጃዎች ላይ ለደረሰው ውድመት የአዳማ ከነማ ደጋፊዎች ጥፋተኛ መሆናቸው በመረጋገጡ የወደሙትን ንብረቶች ክለቦቹ እንዲተኩ ወይም ዋጋውን እንዲከፍሉ በኮሚቴው ውሣኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

የገንዘብ ቅጣትና ንብረት የመተካት ውሣኔ የተላለፈላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስና አዳማ ከተማ ውሣኔው በደረሳቸው በስምንት ቀናት ውስጥ ውሣኔውን ተፈፃሚ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በውሣኔው ቅር የተሰኘ አካልም ይግባኝ የማቅረብ መብቱ ተጠብቆለታል፡፡

በተጨማሪም ሁለቱ ክለቦች ስለስፖርታዊ ጨዋነት ደጋፊዎቻቸውን በማስተማር በ15 ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉም ውሣኔ እንደተላለፈባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *