የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከጋና ጋር ለሚያደርገው ሁለተኛ የማጣርያ ጨዋታ ዝግጅት እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ሰአት በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ቡድኑ ከሶማልያው ጨዋታ ዝግጅት ጀምሮ ከ80 በላይ ተጫዋቾችን የጠራ ሲሆን ትላንት ደግሞ 11 ተጫዋቾችን መቀነሱ ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ከእድሜ ፣ ወጥ ስብስብ አለመኖር እና የትጥቅ አለመሟላት ችግሮች ጋር በመጪው እሁድ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ጋናን ለመግጠም እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡
የፌዴሬሽኑን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ ብሄራዊ ቡድኑ በተደጋጋሚ በርካታ ተጫዋቾችን መጥራቱ እና መቀነሱ ፌዴሬሽኑ ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡
” ይህ የተፈጠረው ውጤት ከመፈለግ የተነሳ አዳዲስ ወጣቶችን በተመለከቱ ቁጥር ለማካተት መጣራቸው ፣ የተጨዋቾች የአቋም መውረድ ፣ የጉዳትና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮች የፈጠሩት ክፍተት ነው ። እኛ ላይ እንኳን በጣም ስራ በዝቶብናል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ሰአት ለ11 ተጨዋቾች ፖስፖርት እንዲወጣላቸው ተነግሮን እየተሯራጥን ነው ። ፖስፖርቱ ላይደርስ ይችላል፡፡ ጫናው በጣም ከፍተኛ ነው ። ነገር ግን የተቻለንን እገዛ እያደረግን ነው፡፡ ” ብለዋል፡፡
አቶ ወንድምኩን ብሄራዊ ቡድኑ በተለያየ ትጥቅ ልምምድ እየሰራ የሚገኘው በፌዴሬሽኑ የትኩረት ማነስ ሳይሆን አዳዲስ ተጫዋቾች በየጊዜው ስለሚመረጡ እና ወጥ የሆነ ስብስብ ባለመኖሩ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡
” ትልቁ ችግር የተጨዋቾች በተደጋጋሚ መቀያያየር የፈጠረው ነው ። አሁን ይመረጣል ነገ ደግሞ ይቀነሳል፡፡ ከፍተኛ የወጥነት ችግር አለ። በተመረጡት ተጫዋቾች ልክ ትጥቅ ሲገዛ እንደገና ሌሎች ተጫዋቾች ይካተታሉ፡፡
“በፌዴሬሸኑ በኩል ለዝግጅቱና ለውድድሩ ከፍተኛ ክትትል እያደረገና ጠንክሮ እየሰራ ነው፡፡ ባለፉት ቀናት የማበረታቻ ሽልማተት ሰጥተናል ፤ ቀጣይ የጋናን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉም ሽልማት ለመስጠት ቃል ሁሉ ገብተናል። በተጣበበ ሁኔታ ለሚቀርቡሉን ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠን ነው የምንገኘው ። በዕድሜ ጉዳይ በMRI ምርመራ የተጣራ ስራ ለመስራት ሲባል ማስረጃዎችን በማዘጋጀት ጥረት ተደርጓል። ስለዚህ በእኛ በኩል ለብሔራዊ ቡዱኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው” ብለዋል፡፡