” በ8 ጨዋታዎች ግብ ላለማስተናገዴ ትልቁን ሚና የሚወስዱት የቡድን አጋሮቼ ናቸው ” ወንድወሰን አሸናፊ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2ኛ ዙር ከተጀመረ ወዲህ የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ወንድወሰን አሸናፊን ግብ የሚደፍር ተጫዋች አልተገኘም፡፡ ሙገር ሲሚንቶን ለቆ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወላይታ ድቻን የተቀላቀለው ወንድወሰን በክለቡ የመጀመርያ አመቶ ቆይታው መልካም የውድድር አመት እያሳለፈ ይገኛል፡፡

ወንድወሰን ግቡን ባለማስደፈሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሁለተኛው ዙር ከጀመረ በተደረጉ 8 ጨዋታዎች ጎል አልተቆጠረብህም፡፡ ምን ይሰማሃል?  አስበኸውስ ታውቃለህ? 

አዎ ፤ ከአንደኛው ዙር ጀምሮ ይኸን ነገር አስበው ነበር፡፡ በፊትም ሙገር እያለው እንደዚህ ያሉ ነገሮች አስብ ነበር፡፡ በነዚህ ስምንት ጨዋታዎች ምንም ጎል አልተቆጠረብኝም፡፡ ለራሴ በጥሩ አቋም ላይ ነኝ ብዬ አስባለው፡፡ እስካሁን ባለው ነገር በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ጎል ያለማስተናገድህ ምስጢር ምንድን ነው? የግል ብቃትህ ፣ የተከላካዮች ጥንካሬ ወይስ ሌላ?

እስካሁን ጎል አለመቆጠሩ የኔ ጥንካሬ ብቻ አይደለም፡፡ ትልቁን ሚና የሚወስዱት የቡድኑ አባላት ናቸው፡፡ አሁን በጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ ስላለን ስንከላከልም ስናጠቃም በጋራ ነው፡፡ ስለሆነም ውጤቱ የሁላችንም ነው፡፡ የእከሌ የእከሌ ነው አልልህም ፤ የሁላችንም የስራ ውጤት ነው፡፡

በቀጣይ ጨዋታዎች የግብ ያለማስተናገድ ሪኮርድህን ለማስጠበቅ ምን የተለየ ነገር ለማድረግ ትሰራለህ?

እንግዲህ ከቡድኔ አባላት ጋር በመሆን ይህን ጎል ያለማስደፈር ግስጋሴዬን ለማስጠበቅ ነው፡፡ እኔ በግሌ የተቻለኝን ለመስራት ጥረት አደርጋለው ፤ ቀሪ ጨዋታዎችን በቡድን መንፈስ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ጎል እንዳይቆጠርብን እንሰራለን፡፡

በርካታ ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት የዘለቀው ሮበርት ኦዶንካራ ነው፡፡ የሮበርት የ13 ጨዋታ ሪከርድ ላይ እደርሳለሁ ብለህ ታስባለህ?

አዎ ሪከርዱ ኦዶንካራ ጋር እደሆነ አውቃለው፡፡ በቀጣይ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች ላይ ጎል እንዳይቆጠርብኝ በማድረግ ሪከርዱን ለመስበር ከቡድን ጓደኞቼ ጋር እሞክራለው፡፡ እሰብራለው ብዬም አስባለው፡፡

ወቅታዊ አቋሜ ለብሄራዊ ቡድን ያስመርጠኛል ብለህ ታስባለህ?

ያው የኔ አላማ በሊጉ ጥሩ ግብ ጠባቂ ሆኖ መጨረስ ነው፡፡ በየጨዋታው አቋሜን ጠብቄ በጨረስኩ ቁጥር ይህ እድል መምጣቱ አይቀርም፡፡ አሁን ላይ ሆኜ እንዲህ ነው ማለት አልችልም፡፡ ጥሩ አቋም ላይ ስለምገኝ እድሉን ባገኝ ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ለብሄራዊ ቡድን ባለመጠራትህ ምን ተሰማህ?

ባለመጠራቴ ውስጤ ቅር ቢለውም የአሰልጣኙ ስራ በመሆኑ ምንም ማለት አልችልም፡፡ ጥሩ ብቃቴን እያሳየሁ ባለሁበት ወቅት መጠራት ነበረብኝ ፤ ግን ይህ አልሆነም፡፡ በዚህም ውስጤ ቅር ቢሰኝም አሁን ያለኝን ብቃት በቀጣይ አጠንክሬ እሰራለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *