ዛሬ ረፋድ በተካሄደው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ክለቡን ለቀጣዮቹ 4 አመታት እንዲመሩ በድጋሚ የተመረጡት አቶ አብነት ገብረመስቀል ከጉባኤው በኋላ የሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጉዳዮች ከፋፍለን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡
ስለ ጠቅላላ ጉባኤው
‹‹ ብዙ ውይይቶች ከተካሄዱ በኋላ ደጋፊውም ማንሳት የፈለጋቸውን ሀሳቦች አንስቶ በሙሉ አብራርተናል፡፡ እኔም ይህን ያህል አመት ከሰራው በኋላ በሌላ ሃይል ይተካ ብዬ ወርጄ ነበር፡፡ ደጋፊው ሊዋጥለት ስላለቻለ ለሚቀጥሉት 4 አመታት እንድቀጥል ስለደረገ ተመልሻለሁ፡፡ በዚህም መላውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ አመሰግናለሁ፡፡ ››
‹‹ አንደኛ ደክሞኛል ፣ ሁለተኛ ደጋፊው ይምረጥ፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ስልጣኑን ለእኔ ሰጥቶ ጥፋት ሲመጣ ሁሉ ነገር እኔ ላይ እንዲወደቅ አልፈልግም፡፡ ለዛ ነው ለመልቀቅ የፈለግኩት፡፡ የክለቡ ትልልቅ ሰዎች ክለቡን በትነኸው መሄድህ ነው ብለው ነው የመለሱኝ፡፡ በዛም ላይ የደጋፊዎች ስሜት ጥልቅ ነበር፡፡ ከቤተሰቤ የመጣውን ነገርም ማፍረስ ይከብዳል፡፡ ››
ስለ ፕሮፌሽናሊዝም
‹‹ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለክለቦች ያስቀመጠው የመተዳደርያ ደንብ መሻሸል አለበት፡፡ ስለ ፕሮፌሽናልዝም ስናወራ የሚያግዱን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ክለብ ራሳችንን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግና ወደ ፕሮፌሽናሊዝም ለመግባት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላትጥናት በማስጠናት ላይ እንገኛለን፡፡ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴርም ለክለቦች ያወጣውን መተዳደርያ ደንብ መፈተሸ አለበት፡፡ ክለቦች ንብረት እንዲኖረን እንኳ ህጉ አይፈቅድልንም፡፡
የሴቶች ተሳትፎ
‹‹ ሴቶች ወደዚህ ቦርድ እንዲመጡ ብዙ ጥረናል፡፡፡ ነገር ግን እንደ ባህል ሴቶች አሁን ነው ወደ ስፖርቱ መምጣት የጀመሩት፡፡ ሌላው የሚያሻሻቸው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ወጣት በነበርኩበት ወቅት በየስታድየሙ የሴቶች ቁጥር ብዙ ነበር፡፡ አሁን ስፖርታዊ ጨዋነት የለም፡፡ ሴቶች ስታድየም ካልሄዱ እንዴት ሴት አመራር ይኖረናል፡፡ ስድቡን ፈርተው ነው የማይመጡት፡፡
‹‹ በመጀመርያ የሴቶቹን ቡድን ያቋቋምነው ተገደን ነው፡፡ ፊፋ ክለቦች የሴት ቡድን ካላቋቋሙ የወንድ ቡድን እሰርዛለሁ ብሏል ብለው ዋሽተው ነው ሳናምንበት ያቋቋምነው፡፡ ቅም ነገሩ ማቋቋሙ ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ በቀትር ነው የሚጫወቱት ፣ ወጣቶቹም በትምህርት ሰአት ይጫወታሉ፡፡ ቤተሰብ ያለው ሰው በዚህ ሰአት እንዴት ውድድር አውጥቶ ይመራል፡፡ ያም ሆኖ በተሻለ ሁኔታ የሴቶቹ ቡድን ተጠናክረው እንዲቀርቡ እናደርጋለን፡፡
ግጭቶች
‹‹ የመናገር ነጸነት የማምንበት ነገር ነው፡፡ ድምፅ መታፈን የለበትም፡፡ እኛም ስራችን ማዳመጥ ነው፡፡ አሁን የመጨረሻ ሁለት እና ሶስት ወር ላይ በተፈጠሩ ችግሮች ዙርያ እኛ ጋር በቀጥታ መናገር ሲችሉ ከበስተጀርባ እንዲያወሩ ኋላ ላይ ደግሞ ፊት ለፊት እንዲሸነግሉ አልፈልግም፡፡ የግል ፀባቸውን ወደ ክለቡ ማምጣት የለባቸውም፡፡ አንዱ አንዱን ለማጥቃት ሲነሳ የተጎዳው ክቡ ነው፡፡ የራሳችን ሬድዮ ፣ ጋዜጣ ፣ ጽህፈት ቤት አለን፡፡ ያንን ትተው ነገሮችን ማሟሟቅ ወደሚፈልጉ ሚድዎች መውሰድ ይፈልጋሉ፡፡››