ዚምባቡዌ፣ ጋና እና ጊኒ ቢሳው የጋቦን ትኬታቸውን ቆርጠዋል

ዚምባቤዌ ከ10 ዓመታት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ስትመልስ ጊኒ ቢሳው የኬንያን ማሸንፍ ተከትሎ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አህጉሪቱ ታላቅ ውድድር የሚያሳፋትን ዕድል አግኝታለች፡፡ የ2015 የፍፃሜ ተፋላሚዋ ጋና ሞሪሽየስን 2-0 በማሸነፍ ዳግም ለአፍሪካ ዋንጫው ቀርባለች፡፡

ከምድብ 12 ዚምባቡዌ ማላዊን ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 በማሸነፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚወስዳትን ትኬት ቆርጣለች፡፡ ኖሌጅ ሙሶና፣ ለማሜሎዲ ሰንዳውንስ ምርጥ ብቃቱን በውድድር ዘመኑን ያሳየው አማካዩ ካማ ቢሊያት እና ከትበርት ማላጂላ የድል ግቦቹን አስገኝተዋል፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ስዋዚላንድ ጊኒን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች፡፡ ምድቡን ዚምባቡዌ በ11 ስትመራ ስዋዚላንድ በ8 ትከተላለች፡፡

ብላክ ስታርስ የሞሪሽየስን የተከላካይ መስመር ለመስበር 67 ደቂቃዎች አስፈልጓቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ እና ኢትዮጵያዊያን ረዳቶቹ በመሩት ጨዋታ ጋና 2-0 ሞሪሽየስን ረትታለች፡፡ የጋናን የድል ግቦች የአሳሞሃ ጂያን በጉዳት ከብሄራዊ ቡድኑ አለመካተቱን ተከትሎ ብላክ ስታርስን በአምበልነት የመራው አንድሬ አዩ እና የመስመር አማካዩ ክርስቲያን አቱሱ አስገኝተዋል፡፡ በምድብ 8 ሩዋንዳ በሞዛምቢክ መሸነፏን ተከትሎ ጋና ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ ጋና ምድቡን በ13 ነጥብ ትመራለች፡፡
ጊኒ ቢሳው ከምድብ አምስት በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ለአፍሪካ ዋንጫው ቀርባለች፡፡ ናይሮቢ ላይ ኬንያ ከመመራት ተነስታ ኮንጎ ብራዛቪልን 2-1 ማሸነፍ ችላለች፡፡ ኮንጎ በኢስማኤል ጎንዛሌዝ ግብ 1-0 ብትመራም አዩብ ቲምቤ እና ኤሪክ ጆና ባስቆጠራቸው ግቦች የሃራምቤ ከዋክብቶቹ የምድብ ማጣሪያውን የመጀመሪያ ሶስት ነጥባቸውን አሳክተዋል፡፡ የኮንጎን መሸነፍ ተከትሎ ጊኒ ቢሳው ምድቡን በበላይነት ማጠናቀቋን አረጋግጣለች፡፡
በምድብ ሁለት አንታናናሪቮ ላይ በግብ በተንበሸበሸው ጨዋታ ዲ.ሪ. ኮንጎ ባለሜዳዋን ማዳጋስካርን 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች፡፡ ኮንጎን ለአሸናፊነት ያበቁ ግቦች ሴድሪክ ባካምቡ እና በጣልያን የሚጫወተው ፖል ሆዜ ምፖኩ ሁለት ሁለት ሲያስቆጠሩ ያኒክ ቦላሲ እና ጆርዳን ሮሊ ቦታካ ቀሪዎቹን ግቦች አክለዋል፡፡ የማዳጋስካርን የመስተዛዘኛ ግብ ጆን ራኮቶኖሜንጃናሃሪ በስሙ አስመዝግቧል፡፡ በምድቡ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ አንጎላን 3-1 አሸንፋለች፡፡ ምድቡን  ኮንጎ በ12 ነጥብ ስትመራ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በ10 ነጥብ ትከተላለች፡፡

ሞኖሮቪያ ላይ ላይቤሪያ ከቶጎ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ ለላይቤሪያ ጊዚ ዶርቦር እና ዊልያም ጄቦር ሲስቆጥሩ ፍሎይድ አይቲ እና ኮድጆ ላባ ለቶጎ ግቦቹን አስገኝተዋል፡፡ ምደብ አንድን ላይቤሪያ በ10 ነጥብ ስትመራ ተመሳሳይ ነጥብ የሰበሰበችው ቱኒዚያ ሁለተኛ ነች፡፡ ቶጎ በስምንት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

ቡርኪናፋሶ ኮሞሮስን 1-0 በመርታት የምድብ 4ን መሪነት ከዩጋንዳ ተረክባለች፡፡

የዕሁድ ውጤቶች፡
ላይቤሪያ 2-2 ቶጎ
ማዳጋስካር 1-6 ዲ.ሪ. ኮንጎ
ስዋዝላንድ 1-0 ጊኒ
ኬንያ 2-1 ኮንጎ ብራዛቪል
ኮሞሮስ 0-1 ቡርኪናፋሶ
ሴሶቶ 1-2 ኢትዮጵያ
ዚምባቡዌ 3-0 ማላዊ
ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 3-1 አንጎላ
ሞሪሽየስ 0-2 ጋና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *