የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት 3 ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ደደቢት እና አዳማ ከተማ ድ ቀንቷቸዋል፡፡ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጥል የውድድር ዘመኑ 3ኛ ሐት-ትሪክም ተመዝቧል፡፡
በ09፡00 አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ፈጣን እንቅስቃሴ ፣ የግብ ሙከራወች እና ጥቂት ግርግሮችን ባስተናገደው ጨዋታ የግብ ማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰዱት አርባምንጭ ከተማዎች ናቸው፡፡ በ36ኛው ደቂቃ ተሾመ ታደሰ ከእንዳለ ከበደ የተሸገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፎ አዞዎቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም በአርባምንጭ ከተማ መሪነት ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተሸጋሪ እና የቆሙ ኳሶች የግብ ማቆጠር አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም ግብ ለማስቆጠር ረጅም ደቂቃዎች ለመጠበቅ ተገደዋል፡፡ በ76ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ሁለት የጊዮርጊስ ተጫዋቾችን አልፎ ለአመለ ሚልኪያስ ያቀበለውን ግልጽ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶ የተመለሰው ኳስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የማዕዘን ምት ሆኗል፡፡ ከማዕዘን የተሸገረውን ኳስም ደጉ ደበበ በግንባሩ በመግጨት የሊጉን መሪ አቻ ማድረግ ችሏል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ በካታንጋ ከጨዋታው መጀመርያ ጀምሮ በመበሻሸቅ ላይ በነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባምንጭ ከተማ ደጋፈዎች መካከል ግርግር የተከሰተ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሎች በፍጥነት አረጋግተውት ጨዋታው ቀጥሎ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡
አዳማ ላይ አዳማ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 1-0 አሸንፏል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሚካኤል ጆርጅ ብቸኛዋን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ውጥረት በተሞላበት ጨዋታ በ26ኛው ደቂቃ ሱሌይማን መሃመድ በሽመልስ አበበ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣ ሲሆን የድሬደዋ ከተማ ተጨዋቾች ግልፅ የሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል በፌዴራል ዳኛ ዳዊት አሳምነው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
በ11፡30 ደደቢት ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል ዳሽን ቢራ ላይ አስመዝግቧል፡፡ ዳሽን ቢራ በየተሻ ግዛው አማካኝነት የግብ ማስቆጠር ቅድሚያውን የወሰደ ሲሆን አጀማመሩም ጨዋታውን በድል የሚወጣ አስመስሎት ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ወደ ጨዋታው ሪትም መግባት የቻሉት ደደቢቶች በዳዊት ፍቃዱ አማካኝት ባገኙት የአቻነት ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ ደደቢቶች በቀላሉ የዳሽን ቢራን የተከላካይ ክፍል መስበር የቻሉ ሲሆን ዳዊት ፍቃዱ ከርቀት የመታው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ደደቢትን መሪ አድርጓል፡፡ ሳሚ ሳኑሚ በ78ኛው ደቂቃ 3ኛውን ሲያክል ጨዋታው ሊገባደድ የሴኮንዶች እድሜ ሲቀረው የእለቱ ኮከብ ዳዊት ፍቃዱ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በደደቢት 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ደደቢት ከ6 ጨዋታ በኋላ ወደ ድል የመለሰውን ውጤት ሲያስመዘግብ አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊትን ተክተው በጊዜያዊነት ለተረከቡት አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም በመጀመርያ ጨዋታ የመጀመርያ ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የዳዊት ፍቃዱ ሐት-ትሪክም ከኤዶም ሆሶውሮቪ እና ሳዲቅ ሴቾ በመቀጠል በውድድር ዘመኑ የተመዘገበ 3ኛ ሐት-ትሪክ ሆኗል፡፡
የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ነገ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሲደረጉ በ09:00 ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና ፣ 11:30 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከተማ ይጫወታሉ፡፡