የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የ2008 የክለቦች የፉትሳል ዋንጫ ከጎ-ቴዲ ስፓርት ጋር በመተባበር በ8 ክለቦች መካከል ከሰኔ 5-19 እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፉትሳል ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ስምንት ቡድኖች በሁለት ምድቦች ተከፍለው የሚፋለሙ ሲሆን አሸናፊ ለሚሆነው ቡድን የአስር ሺህ ብር ሽልማት ይበረከትለታል፡፡ በተጨማሪም ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ቡድኖች የሜዳልያ እንዲሁም ለኮከብ ግብ አግቢ እና ለኮኮብ ተጫዋቾች የዋንጫ ሽልማቶች ይሰጣሉ ተብሏል፡፡
የፉትሳል ኮሚቴው ውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦችን የመመዝገብ ስራ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ቢሰራም የውድድሩ ዋነኛ ስፖንሰር ከሆነው ጎ-ቴዲ ስፖርት ጋር የድርድር ስራ የተሰራው ቀደም ብሎ ነበር፡፡
የምድብ ድልድል
ምድብ አንድ
አበበ ቢቂላ ፣ ኪምብሪያ ኢትዮጵያ ፣ ቲጂ እና ጓደኞቹ ፣ ሊና ሆቴል
ምድብ ሁለት
ኢኤስኤፍ (ኢትዮጵያን ሶከር ፋውንዴሽን) ፣ ጂኬ ኢትዮጵያ ፣ ብሉቤል ፣ አሴጋ ፉትሳል
ዘመናዊ የስፖርት ትጥቆችን በማስመጣት የሚታወቀው ጎ-ቴዲ ስፖርት ውድድሩን በብቸኝነት ስፖንሰር እንዳደረገው የተገለፀው ይህ ውድድር እሁድ ሲጀምር ታላላቅ እንግዶች እና የስፖርት አፍቃሪያን በሚገኙበት በድምቀት ሲጀመር 4:30 ላይ በምድብ አንድ የሚገኙት አበበ ቢቂላ ከሊና ሆቴል እንዲሁም 5፡30 ላይ ኪምብሪያ ኢትዮጵያ ከቲጂና ጓደኞቹ በሚያደርጉት መርሃ ግብሮች የመክፈቻ ጨዋታዎች በድምቀት የሚደረጉ ይሆናል፡፡
ለሁለት ሳምንት በሚቆየው ውድድር ላይ ከፍተኛ ተስጥኦ ያላቸው ወጣት እና ዝነኛ ተጨዋቾች እንደሚሳተፉ ሲገለፅ ሁሉም የውድድር መርሃ ግብሮች ገርጂ አካባቢ በሚገኘው በብሄራዊ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ጂምናዝየም ይደረጋል፡፡ የመግቢያ ዋጋውም ነጻ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ በ1930 እንደተጀመረ የሚነገርለት ይህን የፉትሳል ጨዋታ በሀገራችን ለማሳደግ እና የውድድሩን ደንቦች በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ለማፅረፅ በቅርቡ የተቋቋመው የፉትሳል ኮሚቴው ውድድሩን ለማዘጋጀት እንዲያስብ እንዳደረገው የገለፁት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፉትሳል ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮናስ ሃጎስ የፉትሳል ስፖርትን በመላው የሃገሪቱ ክፍል ለማስፋፋት እቅድም እንዳላቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ የስፖርት አፍቃርያንም በስፍራው በመገኘት እንዲዝናኑና ቡድኖቹን እንዲያበረቱ የኮሚቴው ሰብሳቢ ጨምረው ተናግረዋል፡፡