ብሄራዊ ሊጉ የሚጀመርበት ቀን በ1 ሳምንት ተራዘመ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን የሚጀመርበት ቀን በአንድ ሳምንት መራዘሙን ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሊጉ በሳምንቱ መጨረሻ ህዳር 17 እና 18 እንዲጀመር ክለቦች በእጣ ማውጣቱ ስነስርአት ወቅት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም የዳኞች እና ታዛቢዎችን ክፍያ ከፍለው ባለማጠናቀቃቸው ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን በ1 ሳምንት ተራዝሞ ህዳር 24 እና 25 በሚደረጉ ጨዋታዎች እንዲጀምር ተወስኗል፡፡

ብሄራዊ ሊጉ አምናም በተመሳሳይ የሚጀመርበት ቀን በዳኞች እና ታዛቢዎች ክፍያ በወቅቱ አለመጠናቀቅ ምክንያት በጥር ወር መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ በ5 ምድቦች እና 55 ክለቦች መካከል የሚካሄድ ሲሆን የየምድባቸው አሸናፊዎች እና በጥሩ 2ኛነት ያጠናቀቀ አንድ ክለብ በቀጥታ ወደ 2010 ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *