ሉሲዎቹ በፊፋ የሃገራት ደረጃ መሻሻልን አሳይተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በ2016 የመጨረሻ ወር የፊፋ ኮካ ኮላ የሃገራት ደረጃ ላይ መሻሻልን ማሳየት ችለዋል፡፡ በመስከረም ወር በዩጋንዳ ሰሜናዊ ከተማ ጂንጃ ላይ በሴቶች ሴካፋ ቻምፒዮና ላይ ተሳትፈው ሶስተኛ ደረጃነትን ማግኘት የቻሉት ሉሲዎቹ ከነበሩበት 105ኛ ወደ 102ኛነት መምጣት ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሴቶች እግርኳስ የሃገራት ደረጃ 1143 ነጥቦችን ማግኘት የቻለች ሲሆን ለደረጃ መሻሻሉም የሴካፋ ዋንጫ ውጤት ይጠቀሳል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ አለማለፉ የ2016 ደረጃው ላይ ያለጥርጥር አሉታዊ ጎን ነበረው፡፡ በሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ሉሲዎቹ ካደረጓዋቸው አራት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለት ሲያሸንፉ በአንዱ አቻ ወጥተው በአንዱ ሽንፈትን ቀምሰዋል፡፡

የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫን ማሸነፍ የቻለችው ናይጄሪያ እንደተጠበቀው በአህጉሪቱ ቀዳሚ ሲሆን ከዓለም 35ኛ ስትሆን ጋና እና ካሜሮን ከአፍሪካ 2 እና 3ኛ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ 13ተኛ ላይ መቀመጥ ችላለች፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በደረጃ ሰንጠረዡ የበላይ ስትሆን ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓን፣ ስዊድን፣ ብራዚል እና ሰሜን ኮሪያ እስከ10 ያሉትን ደረጃዎች በቅደም ተከተል ይዘዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ የሴቶች እግርኳስ የተሻለ እንቅስቃሴ በዓመቱ ያሳየችው ኬንያ 122ኛ ላይ መቀመጧ የፊፋ ሃገራት ደረጃ አወጣጥ ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ በሃገራት ደረጃው ላይ መካተት የቻሉት 127 ሃገራት ብቻ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *