በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሶስት ሳምንታት ምንም ግብ ሳያስተናግድ ተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ ስምንት ግቦችን አስቆጥረው በድንቅ ሁኔታ ሊጉን የጀመሩት ፈረሰኞቹ በአራተኛው ሳምንት በፋሲል ከተማ ጎንደር ላይ አስደንጋጭ ሽንፈትን ካስተናገዱ በኃላ በተከታታይ ያደረጓቸውን ሁለት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ሊጉን ከመምራት ያገዳቸው ባይኖርም በመጨረሻ ካደረጓቸው ሶስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች ሁለቱን ብቻ ማሳካት ችለዋል፡፡
በዚህ ምክንያት የክለቡ ደጋፊዎች ባሳለፍነው ሳምንት ይርጋለም ላይ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለግብ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በክለቡ አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ላይ ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡ ጫና ውስጥ እንደሆኑ በስፋት እየተወራባቸው የሚገኙት ሆላንዳዊው የፈረሰኞቹ አለቃ ማርት ኖይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የሊጉ ጥንካሬ ነጥቦች እንዲጥሉ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል፡፡
“ባሳለፍነው አመት እንዲሁም በመጀመሪያው የጊዮርጊስ ቆይታዬ ከተለያዩ ሜዲያዎች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደካማ እንደሆነ ሲናገሩ እድምጫለሁ፡፡ ነገርግን በዚህ አመት ባየሁት ነገር መናገር እንደምችለው ሊጉ ደካማ እንዳልሆነ ልናገር እወዳለሁ፡፡ በዘንድሮው የውድድር አመት ቡድኖች በጣም ተጠናክረውና ተፎካካሪ ሆነው መጥተዋል፡፡ በተለይም በመከላከል አወቃቀር በኩል በጣም ተደራጅተው ቀርበዋል ፤ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በመሰንዘር ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ግቦችን ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ በዚህም እስካሁን ለገጥምናቸው ቡድኖች ክብር እሰጣለሁ፡፡ በዚህ ጠንካራ ሊግ ነጥብ ብንጥል የሚያስገርም አይደለም፡፡ ነገርግን በዚህ ታላቅ ክለብ በተከታታይ ነጥብ መጣል ተቀባይነት እንደሌለውም አውቃለሁ፡፡ ስለዚህም ደጋፊዎች ተቃውሞ ቢያሰሙ የሚያስገርም አይደለም ፤ ግን ደግሞ በእግርኳስ ውስጥ ማሸነፍ መሸነፍ አቻ ያለም እንደሆነ ሊረዱ ይገባል፡፡ ” ብለዋል፡፡
አሰልጣኝ ማርት ኑይ ባሳለፍነው እሁድ ከቡድናቸው ደጋፊዎች ተቃውሞ እንዲቀርብባቸው ምክንያት የሆነውን ጨዋታ ማሸነፍ እንደነበረባቸው ይናገራሉ፡፡
” ከሲዳማ ቡና ጋር ያደረግነው ጨዋታ ከባድ ነበር ፤ እንደሚታወቀው ሲዳማ ቡና በሊጉ አናት ካሉ ቡድኖች አንዱ ከመሆኑ በተጨማሪ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት እንደመግጠማችን በኔ እይታ ጨዋታውን በጥሩ መልኩ ተቆጣጥረነው ነበር፡፡ ነገርግን እንዳለመታደል ሆኖ ግብ ማስቆጠር አልቻልንም ፤ በዚህም ምክንያት አቻ ልንወጣ ችለናል፡፡ ከጨዋታው በኃላ በተመለከትኩት ቪድዮ እንደተመለከትኩት ከሆነ ሲዳማዎች ወደ እኛ ግብ ጠባቂ ሮበርት 4 ሙከራዎችን ብቻ ነው ማድረግ የቻሉት፡፡ ከነዚህም አብዛኞቹ ሙከራዎች ከግብ ክልል ውጪ የተሞከሩ ነበሩ ፤ በእለቱ እድለኛ ስላልነበርን ጥሩ መንቀሳቀስ ብንችልም አሸናፊ የምታደርገዋን ግብ ማስቆጠር ባለመቻላችን ያለ ግብ አቻ ለመለያየት ተገደናል፡፡”
ቅዱስ ጊዮርጊስ ረቡዕ በወጣው የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ እጣ ከሲሸልሱ ኮት ዲ ኦር ጋር ተደልድሏል፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኑይ ግን ስለጨዋታው ለመናገር ጊዜው ገና መሆኑን በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
” እንደሚታወቀው አምናም በቅድመ ማጣሪያው የተደለደልነው ከሲሸልስ ቡድን ጋር ነበር፡፡ ሲሸልስ የደሴቶች ስብስብ ናት ፤ እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት ኮት ዲ ኦር አምና ከገጠምነው ቡድን ከሚገኝበት በተለየ ደሴት ላይ ከመገኘቱ በቀር ከአምናው ብዙ የተለየ ነገር የለውም፡፡ በተጨማሪ በዘንድሮው ድልድል መሠረት የመጀመሪያ ጨዋታችንን የምናደርገው ከሜዳችን ውጪ መሆኑ ከአምናው ሊለየው ይችል ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ሆኖ እንዲህ ይሆናል ብሎ መናገር ባይቻልም ከአምናው ብዙም የተለየ ነገር ይኖራል ብዬ አልጠብቅም እንደ አምናው ሁሉ አሁንም ለማሸነፍ እንጫወታለን ፤ ከቻምፒየንስ ሊጉ ጨዋታ በፊት በሊጉ ዘጠኝ ጨዋታዎች ይጠብቁናል፡፡ ስለዚህ ለጊዜው ትኩረታችን የሚሆነው ከቻምፒየንስ ሊጉ እኩል ትኩረት የምንሰጠው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ነው፡፡ በቀጣይ ጊዜው ሲደርስ የሚሆነውን የምናየው ይሆናል፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን አገባደዋል፡፡
ከፈረሰኞቹ ጋር በተያያዘ ዜና በቀጣይ ለሚጠብቃቸው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር እንዲሁም የሊግ ጨዋታዎች አንድ የመሀል ተከላካይ እንዲሁም አንድ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች ከቡርኪናፋሶ በማስመጣት የሙከራ ጊዜ ተሰጥቷቸው ከቡዱኑ ጋር ልምምዳቸውን እየሰሩ ይገኛል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ7ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻን በነገው እለት በ9:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡