የጨዋታ ሪፓርት | አርባምንጭ ከተማ መከላከያን ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

በ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ አበባ ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው መከላከያ ከ6 ጨዋታዎች በኃላ የመጀመሪያ ሽንፈቱን አስተናግዷል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ የቻሉት መከላከያዎች ነበሩ፡፡ በዚህም የጨዋታውን የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ 5 ያክል ደቂቃዎች ብቻ አስፈልጓቸዋል፡፡ በ5ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደስታ ከመሀል ያሳለፈለትን ኳስ የተሻ ግዛው ከተቆጣጠረ በኃላ በተሻለ ቦታ ለሚገኘው ማራኪ ወርቁ ቢያቀብለውም ማራኪ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳ ሊያድንበት ችሏል፡፡  በአንጻሩ በ8ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጭ ከተማው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ፀጋዬ ወደ መከላከያዎች የግብ ክልል አልፎ የግብ ሙከራ ሊያደርግ ሲል በመከላከያው ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች አዲሱ ተስፋዬ ቢጠለፍም ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት ፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ይልቅ ለተቃራኒ ቡድን ቅጣት ምት በመስጠታቸው የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ቡድን ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ከመሀል ሜዳ በረጃጅሙ ከፊት ላሉት ፈጣን አጥቂዎች የተሻ ግዛው ማራኪ ወርቁ በሚለቀቁ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደረጉ የተስተዋሉት መከላከያዎች በ21ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝ ያሻገረለትን ኳስ በሀይሉ ግርማ ወደ ግብ ቢሞክርም አንተነህ መሳ አድኖበታል፡፡

አርባምንጮች በ24ኛው እና በ25ኛው ደቂቃ ላይ በተከታታይ በአማኑኤል ጎበና ከርቀት እንዲሁም ገብረሚካኤል ያዕቆብ ሳይጠቀሙባቸው የቀሩት ኳሶች በመጀመሪያው አጋማሽ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በእለቱ ጨዋታውን የመሩት አልቢትር  በሚወስኗቸው በርካታ ውሳኔዎች ላይ በጨዋታው ከወትሮው ቁጥራቸው አነስ ቢልም ከነበሩት የአርባምንጭ ደጋፊዎች በተደጋጋሚ  ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ነበር፡፡

በ36ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች በግራ መስመር ያገኙትን ቅጣት ምት ወንድሜነህ ዘሪሁን በጥሩ ሁኔታ አሻምቶ ፀጋዬ አበራ ወደ ግብነት በመቀየር አዞዎቹን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

በ41ኛው ደቂቃ የአርባምንጭን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲመራ የነበረው ፀጋዬ ከግራ መስመር  ያቀበለውን ኳስ ገብረሚካኤል ከተቆጣጠረ በኃላ ግብጠባቂው አቤል ማሞን በግሩም ሁኔታ ካታለለ በኃላ በመከላከያ ተከላካዮች ጥፋት ተሰርቶበት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ገብረሚካኤል ያዕቆብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ በእንግዶቹ አርባምንጭ ከተማ 2-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ከመጀመሪያው በተሻለ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውን ወደ መሀል ሜዳ በማስጠጋት የበለጠ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በበሀይሉ ግርማ እንዲሁም በማራኪ ወርቁ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ተጠቃሽ ነበሩ፡፡

አርባምንጮች ደግሞ በመጠኑም ቢሆን ወደ ኃላ በማፈግፈግ ከተከላካዮች በቀጥታ ወደፊት በሚላኩ ኳሶች ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ላይ ታደለ መንገሻ ያሾለከለትን ኳስ ገብረሚካኤል ሞክሮ የውጪኛው መረብ የመታችው ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በ70ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች ወደ ጨዋታው ሊመለሱበት የሚችሉበትን አጋጣሚ የግብጠባቂው አንተነህ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ምንተስኖት ከበደ ቢሞክርም ኢላማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች፡፡ በአርባምንጭ ከተማዎች በኩል ደግሞ በ71ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ታደለ እና ፀጋዬ ተቀናጅተው በመሄድ የተገኘችውን እድል ፀጋዬ አበራ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡

በ79ኛው ደቂቃ ላይ ከአርባምንጭ ከተማ ግብ ክልል በቅርብ ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት ሳሙኤል ታዬ በግሩም ሆኔታ አስቆጥሮ መከላከያን ወደ ጨዋታው መልሶታል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ጦሩ የበለጠ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው ያገኘውን ፍፁም ግለፅ የሆነ የማግባት አጋጣሚ በአስገራሚ ሆኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

በቀሩቱ ደቂቃዎች አርባምንጭ ከተማ ውጤት ለማስጠበቅ ያደረጉት የመከላከል ጥረት ፍሬ አፍርቶ ጨዋታውን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል፡፡ ይህም ውጤት በ3ኛው ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፉ በኃላ ላለፉት 6 ጨዋታዎች ሳይሸነፉ ለዘለቁት መከላከያዎች ከ6 ጨዋታዎች በኃላ ያጋጠማቸው  የመጀመሪያ ሽንፈት ሲሆን በአንጻሩ በሊጉ አስከፊ ጅማሮ ያደረጉት አርባምንጭ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 16 አሳድገው በአስገራሚ ግስጋሴያቸው ቀጥለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *