የ2009 የኢትዮጵያ ከ17 ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዙር ውድድር አፈፃፀም ግምገማ ማክሰኞ ከ3፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ 15 ክለቦች በተሳተፉበት ፕሪምየር ሊጉ የአንደኛ ዙር አፈፃፀም ሪፖርት፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሪፖርት እና የዳኛ ኮሚቴ ሪፖርት ቀርቧል፡፡
በሪፖርቱ የውድድር ተሳትፎ እና ፉክክር ካለፉት ዓመታት የተሻለ ሆኖ መገኘቱ፣ የእድሜ ማጣራት ስራ ላይ የተሰራው ስራ አጥጋቢ መሆን እና ክለቦች ለውድድሩ ትኩረት መስጠታቸው ጠንካራ ጎን መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ ሲቀርብ አነስተኛ የተመልካች ቁጥር፣ የአልፎ አልፎ የሚኖሩ የዳኝነት ውሳኔ ስህተቶች፣ የመወዳደሪያ ሰዓት እና ሜዳ የመቀያየር ችግሮች በደካማ ጎንነት ቀርበዋል፡፡
ክለቦችም መሻሻል አለባቸው ያሏቸውን ችግሮች በግምገማው ላይ አቅርበዋል፡፡ በተደጋጋሚ ክለቦች የመጫወቻ ሜዳዎች ምቹ አለመሆንን እንደችግር አንስተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም በውድድር መደራረብ የተነሳ እየተጎዳ ስለሚገኝ የ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ በሚገኙ አራት ሜዳዎች ላይ በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ጎፋ የሚገኘው የኤሌክትሪክ ሜዳ፣ ሲኤምሲ የባንክ ሜዳ እና ቃሊቲ አከባቢ የሚገኙት መድን እና የኒያላ ሜዳ ውድድሮችን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ሜዳዎች ለታዳጊ ተጫዋቾች አለመመቸታቸው በተጨማሪ በአግባቡ የተሰመሩ የሜዳ ላይ መስመሮች አለመኖራቸው ክለቦች በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡ አንድ ክለብ በውድድር ዓመቱ የሚያደርገው የጨዋታዎች ማነስ ታዳጊ ተጫዋቾች በቂ የሆነ የጨዋታ በብዛት እንዳያገኙ እያገዳቸው እንደሆነ ክለቦቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ከ17 ዓመት በታች ሊጉ ያለበት ወቅታዊ ደረጃን ገምግሞ ሪፖርት የማቅረብ ረገድ የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴው የሚያደርገው ክትትል አነስተኛ መሆን፣ ችግሮች ሲነሱ ፌድሬሽኑ ችግሮችን እምኖ ወደ ትግበራ ሲገባ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩ፣ የፕሮግራም አወጣጡ የአብዛኞቹን ተማሪ ተጫዋቾችን ያመከለ እንዲሆን ክለቦቹ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የእድሜ ተገቢነት ላይ ፌድሬሽኑ በውድድር አመቱ ጥሩ ስራዎችን ቢሰራም አንዳንድ ክለቦች ውጤት አጥብቆ በመፈለግ ከእድሜ በላይ የሆኑ ተጫዋቾችን እያሳለፉ እንደሚገኝ ክለቦች ቅሬታቸውን አቅረበዋል፡፡ አንዳንድ ክለቦች በበጀት እጥረት ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ክልል ወጥተው ጨዋታዎች ለማደረግ አለመፈለጋቸው ውጤት ላይ እና የታዳጊ ተጨዋቾች የሚያገኙት ልምድ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው ክለቦቹ በአስተያየታቸው ገልፀዋል፡፡ ሊጉን የሚከታተል የሚዲያ ይሁን የተመልካች ቁጠር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው ሲሉም ክለቦቹ ጠቅሰዋል፡፡
ፌድሬሽኑ ለተነሱት ጥየቄዎች መልስ ሰጥቷል፡፡ በተለይ የመጫወቻ ሜዳን በተመለከተ ክለቦች እርስበእርስ ተቀራርበው ቢሰሩ እና ቢግባቡ የበለጠ ተመራጭ እንደሚሆን ፌድሬሽኑ በመፍትሄ ሃሳቡ ገልጿል፡፡ የእድሜ ተገቢነትን በተመለከተም የተጀመረውን መልካም ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፌድሬሽኑ ጠቅሷል፡፡