ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የወጣውን የቅጥር ማስታወቂያ አልፈው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ በመሆን የተመረጡት የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በሳምንቱ መጨረሻ ክለቡ ከድሬዳዋ ከተማ ከሚያደርገው ጨዋታ በኋላ ሊለያዩ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡
አዳማን በወረደበት አመት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በማሳደግ ያለፉትን ሦስት አመታት ጠንካራ ተፎካካሪ ያደረጉት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ መሆናቸውን ተከትሎ ብሄራዊ ቡድኑን እያሰለጠኑ የክለብ ስራን ደርቦ መያዝ እንደማይቻል ደንቡ ላይ በመቀመጡ ለመለያየታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ሳምንት ቡድኑ ከድሬዳዋ ጋር የሚያደርገው ጨዋታም አሰልጣኝ አሸናፊ ቀይ ለባሾቹን በዋና አሰልጣኝነት የሚመሩበት የመጨረሻ ጨዋታ እንደሚሆንና ከክለቡ ጋር በይፋ እንደሚለያዩ ሶከር ኢትዮዽያ አረጋግጣለች።
አዳማ ከተማ በቀጣይ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የሚረከበውን አሰልጣኝ ያላሳወቀ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያ ጉዳዩን በመከታተል ወደ እናንተ የምታደርስ ይሆናል፡፡