“በሁለተኛው ዙር ተፎካካሪ ሆነን እንቀርባለን” ቢያድግልኝ ኤልያስ 

ጅማ አባ ቡና በታሪክ የመጀመርያውን የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡ በቡድኑ ውስጥ የሊጉ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ቢያድግልኝ ኤልያስ በመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ ጥሩ መንቀሳቀስ ከቻሉ ተጫዋቾች ይጠቀሳል፡፡ ሁሉንም ደቂቃዎች ከተሰለፉ ጥቂት ተጫዋቾች መካከል የሆነው ቢያድግልኝ 2 ጎለሎች በስሙ ማስመዝገብም ችሏል፡፡ ቢያድግልኝ ስለ አንደኛው እና ሁለተኛው ዙር እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሰጠውን አስተያየት እነሆ፡፡

የመጀመሪያ ዙር እንቅስቃሴ

“ቡድኑ በዘንድሮው አመት ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንደማደጉ በመጀመሪያው ዙር ያስመዘገብነው ውጤት ከሞላ ጉደል ጥሩ የሚባል ነው፡፡ በቡድናችን ውስጥ የሚገኙት አብዛኞቹ ተጫዋቾች በፕሪሚየር ሊጉ የመጫወት ልምድ የሌላቸው እና አቅማቸውን ማሳየት የሚፈልጉ ጥሩ አቅም ያላቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ በዚህም በሁለተኛው ዙር ከአዲሱ አሰልጣኛችን ጋር በመሆን የተሻለ ነገር ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን፡፡”

ስለ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ

“እንደሚታወቀው አሰልጣኝ ገብረመድህን በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ጥሩ አሰልጣኞች አንዱ ነው፡፡ እስካሁን በነበረን አጭር ቆይታ ከአሰልጣኙ የማናውቃቸውን አዳዲስ ነገሮች እየተማርን እንገኛለን፡፡ በተለይ ወጣቶቹ የፕሪሚየር ሊጉን ውድድር ጠልቆ ያለማወቅ ችግሮች አለባቸው ፤ አሰልጣኙ በዚህ ላይ ስራ እየሰሩ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በታክቲኩ አዳዲስ ነገሮችን ወደ ቡድኑ ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን፡፡”

ስለ ሁለተኛው ዙር እቅዳቸው

“ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በሊጉ ቆይታውን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በተሻለ በሁለተኛው ዙር ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን እንቀርባለን፡፡ በእርግጠኝነት ሊጉ ሲጠናቀቅ ጥሩ ደረጃን ይዘን እናጠናቅቃለን፡፡”

ወደ ብሔራዊ ቡድን ስለመመለስ

“የትኛውም አሰልጣኝ አንድን ተጫዋች ለብሔራዊ ቡድን የሚጠራው ሜዳ ገብቶ በውድድሮች ላይ መጫወት ሲችል ነው፡፡ እኔም በቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረኝ ቆይታ እምብዛም የመጫወት እድሉን አላገኘሁም፡፡ በዚህም ለተወሰነ ያህል ጊዜ ከብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውጪ ልሆን ችያለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ3 አመት ተጫውቻለሁ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ የማገልገል አቅሙ አለኝ፡፡ እኔም ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመሆን ዳግም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን መለያ ለመልበስ ጠንክሬ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *