ከሌሶቶ ጨዋታ በፊት የሚነሱ ተስፋ እና ስጋቶች

አስተያየት በአብርሃም ገ/ማርያም እና ሚካኤል ለገሰ

ጋቦን ለምታስተናግደው የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) የመጀመሪያ የማጣርያ ጨዋታቸውን በባህርዳር ሁለገብ ስታድየም የፊታችን እሁድ ሰኔ 7 ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ያደርጋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለዚሁ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከዛምቢያ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አከናውኖ በዛምቢያ አቻው 1ለ0 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለሚያደርገው ጨዋታ አሠልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከመረጧቸው 24 ተጨዋቾች ውስጥ ከግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው እና ራምኬል ሎክ በስተቀር ሁሉም የቡድን አባላት ዝግጅታቸው ባህርዳር ላይ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ አሠልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ለምከተለው አጨዋወት ይሆኑኛል ብለው በመረጧቸው ተጫዋቾች የጨዋታ ባህርይ ፣ ዮሃንስ ሳህሌ በደደቢት በነበሩበት ወቅት ከሰሩት ቡድን ፣ የብሄራዊ ቡድኑ የቅርብ አመታት አጨዋወት እና ከዛምቢያ ጋር ካደረጉት የወዳጅነት ጨዋታ በመነሳት የብሄራዊ ቡድኑ ተስፋ እና ስጋቶችን እንዲህ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

ተስፋዎች

የተጋጣሚዎች ደረጃ እነ ስነ-ልቡና

የእሁድ የብሄራዊ ቡድኑ ተጋጣሚ ሌሶቶ እና ሲሸልስ በንፅፅር ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ቀላል ተጋጣሚ ይመስላሉ፡፡ ቡድኖቹ በእግርኳሱ ካርታ ላይ በውጤታማነት እምብዛም የማይታወቁ ከመሆናቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያን የቅርብ ጊዜ የሜዳ ውጪ አቋም ስንመለከት ቡድናችን ከሁለቱ ተጋጣሚዎቹ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ከፍተኛውን ነጥብ ይወስዳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ቡድኑ በቅርብ አመታት ከጋቦሮኒ ፣ ብራዛቪል ፣ ኮቶኑ እና ፕሪቶርያ ነጥቦች ይዞ የተመለሰ ሲሆን በሜዳው ጭምር በሚሸነፍበት ወቅት እንኳ ማሊን አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ይህ የሚያሳየው ቡድኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከሜዳው ውጪ ቢያንስ ነጥብ ተጋርቶ የመመለስ ስነ-ልቡናዊ ጥንካሬ እየያዘ መምጣቱ ነው፡፡ ቡድኑ ከሁለቱ ተጋጣሚዎች ከፍተኛ የሚባለውን ነጥብ በማግኘት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቡድን ከሆነው አልጄርያ ጋር ለሚያደርጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የስነ-ልቡና ስንቅ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ብሄራዊ ቡድኑን ከመረከባቸው በፊት ደደቢትን ቀስ በቀስ በማስተካከል አሸናፊ ቡድን አድርገውት ነበር፡፡ አሰልጣኙ ደደቢትን ከመሰናበታቸው በፊት ቡድኑ ላይ ከፈጠሩት ለውጥ ዋንኛው የተከላካይ መስመሩን የገነቡበት መንገድ ነው፡፡ ቡድኑ በዮሃንስ ሳህሌ ዘመን የተከላካይ መስመሩ የተዋሃደ ፣ ቡድኑ በሚያጠቃበት ወቅት ወደ መሃል ሜዳ ተጠግቶ በመከላከል እና ከጨዋታ ውጪ አጨዋወትን በመቆጣጠር እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ የመስመር ሽግግር ከሊጉ ክለቦች የተሻለ የሚባል አጨዋወትን መፍጠር ችለዋል፡፡ ቡድኑን 7 ወራት ብቻ በማሰልጠናቸው በቡድኑ የፈጠሩት ለውጥ የተጋነነ እንዳልሆነ የሚነሳው ክርክር ምክንያታዊ ቢሆንም ቡድኑን ሲረከቡ ከነበረው ሁኔታ አንፃር የፈጠሩት ለውጥ የሚካድ አይደለም፡፡ አሰልጣኙ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንደሚናገሩት የቡድኑ ሰላም እና ስነ-ስርአት የሚያስጠብቁ ከሆነ በፍጥነት ውጤት ባያመጡ እንኳ ቢያንስ ተስፋ የሚሰጥ ቡድን ሊሳዩን ይችላሉ፡፡

የተጫዋቾች በመልካም አቋም ላይ መገኘት

በቅርብ ጊዜያት ከተደረጉ የብሄራዊ ቡድን ምርጫዎች በተሻለ የዘንድሮው በወቅታዊ አቋም ላይ የተመሰረተ የተጫዋቾች ምርጫ ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊት በጉዳት እና አቋም መውረድ ረጅም ጊዜ ያልተጫወቱ ተጫዋቾች ሲመረጡ የቆዩ ሲሆን ዘንድሮ በቂ ጨዋታ የተጫወተ ተጫዋች ለምርጫቸው ዋንኛ መስፈርት እንደነበር አሰልጣኙ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

ከሌሴቶ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አቤል ማሞ በግብ ጠባቂነት ፣ የተከላካይ መስራቸውን ከስዩም ፣ ሳላዲን ፣ አስቻለው እና ዘካርያስ አማካይ ክፍሉን ከጋቶች ፣ ሽመልስ ፣ በኃይሉ እና ምንተስኖት ፣ የአጥቂ መስመሩን ከሳላዲን እና ኡመድ እንደሚያዋቅሩ የሚጠበቅ ሲሆን አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች የዘንድሮውን የውድድር ዘመን በመልካም አቋም ያሳለፉ ናቸው፡፡ ሁለቱ የመሃል ተከላካዮች በአሁኑ ሰአት በሊጉ ከሚጠቀሱ ምርጥ ተከላካዮች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ሳላዲን ለአመዛኞቹ የሊጉ አጥቂዎች በፍጥነት እና ጉልበት አስቸጋሪ ተከላካይ ሲሆን ሰው በሰው የመከላከል ችሎታው መልካም ነው፡፡ አስቻለው ደግሞ ተስፋ የተጣለበት ወጣት ሲሆን ዘንድሮ በዮሃንስ ሳህሌ ደደቢት ቋሚ አሰላለፍ ሰብሮ መግባት የቻለ ተጫዋች ነው፡፡

ዘካርያስ በግራ መስመር ተከላካይነት የውድድር ዘመኑን በወጥ አቋም ያሳለፈ ሲሆን በማጥቃት እና በመከላከል ተመጣጣኝ አገልግሎት የሚሰጥ ወጣት ነው፡፡ ከዛምቢያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ከበርካቶች አድናቆት ያተረፈው ዘካርያስ የቡድኑን የመከላከል ሚዛን ለመጠበቅ ተመራጭ ተጫዋች ያደርገዋል፡፡ በተለምዶ የሊጉ ክለቦች በማጥቃት ወቅት ሁለቱም የመስመር ተከላካዮች በአንድ ጊዜ የፊት ለፊት የማጥቃት እንቅስቃሴ (overlapping movement) ከማድረጋቸው በተጨማሪ ከጀርባቸው ትተውት የሚሄዱትን ክፍተት ያማከለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይስተዋልም፡፡ ዘካርያስ የብሄራዊ ቡድን ልምዱ አነስተኛ ቢሆንም በቅዱስ ጊዮርጊስ ያሳየውን በብሄራዊ ቡድን ከደገመ ይህንን ክፍተት የማይደፍንበት ምክንያት አይኖርም፡፡

ስዩም ተስፋዬ በደደቢትም ሆነ ብሄራዊ ቡድኑ ባለፉት 5 አመታት ቦታውን ሲሸፍን ቆይቷል፡፡ የተጫዋቹ ችግር የነበረው ከተከላካይ ክፍሉ የመነጠል እና በማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት ከጀርባው ሰፊ ርቀትን ጥሎ የመሄድ ችግርን ዘንድሮ በመጠኑ ቀርፏል፡፡ እድሜው መግፋቱና አምበል ተደርጎ መሾሙ ሀላፊነት እንዲሰማውና እንዲበስል ያደርገዋል፡፡ በኃይሉ አሰፋ የውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ተመርጧል፡፡ የዋልያዎቹ 2ኛ አምበል የብሄራዊ ቡድን ልምዱን ከወቅታዊ ድንቅ አቋሙ ጋር አዋህዶ በማጣርያ ጨዋታዎቹ ምርጥ ግልጋሎት ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል ፣ ጋቶች እና ምንተስኖትም ምርጥ የውድድር ዘመን አሳልፈዋል፡፡ ሽመልስ ውጪ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች በተሻለ በርካታ ጨዋታ ያደረገ ሲሆን በግብፅ የተሳካ የውድድር ዘመን ማሳለፉን ቀጥሏል፡፡ ሳላዲን ሰኢድ ብዙ ጨዋታ ለአል-አህሊ ማድረግ ባይችልም የብሄራዊ ቡድናችን መተማመኛ ነው፡፡ ኡመድ ኡኩሪ ለረጅም ወራት ከጨዋታ ርቆ መቆየቱ በወቅታዊ አቋሙ ላይ ተፅእኖ ሊያሳርፍ ቢችልም ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች በብሄራዊ ቡድኑ ማልያ ያሳየው መሻሻል በኢትሃዱ አጥቂ ላይ ተስፋ እንድንጥል ያደርገናል፡፡

 

ሊታዩ የሚገባቸው ድክመት እና ስጋቶች

የመከላከል አጨዋወት

በብሄራዊ ቡድኑ በባሬቶ እና ከእርሳቸው በፊት በነበሩት ዘመናት በሚያደረጋቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም ሆነ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ የነበሩ የመከላከል አጨዋወት ድክመቶች ዋጋ ሲያስከፍሉን ተመልክተናል፡፡ በተለይ ደግሞ የተከላካይ መስመሩ የሚዋቀርባቸው የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች ውህደት እምብዛም ሲሆን ተመልክተናል፡፡ እንደ አብነትም ከአልጄርያ ጋር በተደረጉ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ግቦቹ የተቆጠሩበት መንገድ የመከላከል አጨዋወታችን ላይ ትኩረት እንድናደርግ ያስገድደናል፡፡

ቡድናችን በተለይም ደረጃቸው ከፍ ካሉ ቡድኖች ጋር ሲጫወት ተጋጣሚዎችቻን ግብ የሚያስቆጥሩት በአራቱ የመሃል ተከላካዮቻችን መካከል (Channels) ያለው ክፍተት በማስፋቱ ፣ በተከላካዩ እና በአማካዩ መስመር መካከል ያለው ክፍተት (between the lines) ባለማጥበብ የተጋጣሚ የማጥቃት አማካዮች ሰፊ የማሰብያ ጊዜ እና ቀዳዳ እንዲያገኙ በማድረግ አልያም በመስመር በሚደረግ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ ዝግመታዊ ሽግግር ለተጋጣሚ የመስመር አጥቂዎች ሰፊ የመሮጫ ቦታ ክፍተት በመተው ነው፡፡

የዋልያዎቹ የመከላከል ችግር በአጠቃላይ ብሄራዊ እግርኳሱ ላይ የሚታየው አጠቃላይ ችግር ነፀብራቅ ነው፡፡ የጨዋታ ውጪ አጨዋወት ፣ ኳስን ከተከላካይ መስመር የመመስረት ፣ ወደ መሃል ሜዳው ተጠግቶ መከላከል ወይም በጥልቀት አፈግፍጎ በተደራጀ ሁኔታ መከላከል ፣ በቀጠና እና በሰው በሰው የመከላከል ፣ ትኩረት (በተለይም በመጨረሻቹ 20 ደቂቃዎች) ፣ መረጋጋት (የደጋፊ እና የተጋጣሚ ቡድንን ጫና መቋቋም) ፣ 50/50 አጋጣሚዎችን የማሸነፍ ፣ የአየር እና የቆሙ ኳሶች ላይ የመድከምና የመሳሰሉት ችግሮች በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የተለመዱ በመሆናቸው ይህ ችግር በአጭር ጊዜ ይቀረፍ የሚል ጫና ውስጥ ልናስገባቸው አይገባም፡፡

ብሄራዊ ቡድናችን ከተጫዋቾቹ ባህርይ ተነስቶ የመከላከል አጨዋወቱን ካላሻሻለ በቀር በሌሎች የአውሮፓ ቡድኖች ላይ ያየነው የመከላከል አጨዋወትን እንደወረደ መተግበር አደገኛ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን አሁን በሊጉ ክለቦች ላይ ወደ መሃል ሜዳው ተጠግቶ መከላከል እየተለመደ ቢመጣም አጨዋወቱ ወደ መሃል ሜዳ ከመቅረብ በዘለለ የተጠና ባለመሆኑ ቡድኖቻችን በቀላሉ ግብ እንዲቆጠርባቸው በር ከፍቷል፡፡ በተለይም የውጪ ዜጋ የሆኑ አጥቂዎች (ፊሊፕ ዳውዚ እና ሳሚ ሳኑሚ) በዚህ አጨዋወት ወደ ሜዳ የሚገቡ ቡድኖች ላይ የመስፈንጠር ችሎታቸውን ተጠቅመው ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ሰፊ ክፍተት ሲጠቀሙና በቀላሉ ግብ ሲያስቆጥሩ ተመልክተናል፡፡

አልጄርያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ቡድኖች በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች ፈጣን እና ጉልበተኛ አጥቂዎችን በመጠቀም ግብ ማስቆጠር አልያም በፈጣን መልሶ ማጥቃት በፍጥነት ወደ ግብ ደርሶ አደጋ መፍጠር የተለመደ በመሆኑ ተከላካዮቻችን ከጀርባቸው ሰፊ ርቀት ትተው የሚከላከሉ ከሆነ ርቀቱን ለማጥበብ የሚፈልገውን ፍጥነት ፣ ትኩረት እና ጉልበት ያሟላሉ ተብሎ አይታሰብም፡፡

የተከላካይ አማካዮቹ ነገር

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዛምቢያ ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ከታዩ ችግሮች መካከል በአራት ተጫዋቾች በተዋቀረው የአማካይ ክፍል ልብ ላይ የነበሩት ጋቶች ፓኖም እና ምንተስኖት አዳነ ጥምረት በተጫዋቾቹ የአጨዋወት ባህርይ ምክንያት ስኬታማ አለመሆኑ ነው፡፡ ጋቶች በቅብብል ላይ ለሚመሰረትና በርካታ የመሃል አማካይ ተጫዋቾችን ለሚይዝ ቡድን የሚያመች የጨዋታ ባህርይ ቢይዝም 4-4-2 ለሚጠይቀው ትጋት ፣ ሰፊ ቦታ(ቀዳዳ) መሸፈን እንዲሁም በጎንዮሽ እንቅስቃሴ የመስመር ተከላካዮች ወደፊት ሲጓዙ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመድፈን የሚሆን የጨዋታ ባህርይ የለውም፡፡ በሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት ዘመን አስራት መገርሳ ላይ የሚታየው ለተከላካይ መስመሩ እጅግ የመጠጋትና ከሌሎች አማካዮች መራቅ በጋቶች ላይም ይስተዋላል፡፡

ዘንድሮ ድንቅ አቋሙን ያሳየው ምንተስኖት አዳነ የጨዋታ ባህርይ ከጋቶች ይልቅ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚሳተፍ እንዲሁም በፍጥነት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል የሚደርስ ተጨዋች ነው፡፡ ነገር ግን ቀጥተኛ አጨዋወቱ በሜዳ ቁመት የሚጫወት የተገደበ አማካይ አድርጎታል፡፡ ምንተስኖት ዘንድሮ በቡድኑ በማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት ከጨዋታ አቀጣጣይነት ይልቅ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል በመሮጥ አደጋ የሚፈጥር አማካይ ነው፡፡ ምንተስኖት እንደጋቶች ሁሉ በ3 አማካዮች በሚዋቀር የ4-3-3 አሰላለፍ ከአማካይ ተከላካዩ ግራ አልያም ቀኝ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ከ2 የተካላካይ አማካዮች አንዱ ቢሆን የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእርሱን ክፍተት በሌሎች አማካዮች መድፈን ስለሚያስችል በአማካይ ክፍሉ ላይ መመጣጠንን መፍጠር ይቻላል፡፡

ቡድኑ ከዛምቢያ ጋር በተደረገው ጨዋታ ሁለቱ ተጫዋቾች ከሜዳው ወርድ ይልቅ በቁመት የተጣመሩ ሲሆን በጨዋታው የተከሰተው ከመስመር ተከላካዮች/አማካዮች ጋር መቀባበያ አማራጮችን የመፍጠር ፣ የመስመር አማካዮች እና የአማካይ ክፍሉ መነጣጠል ችግር መንስኤ ከአማካዮቹ አጨዋወት ጋር የተያያዘ መሆኑ በ2ኛው አጋማሽ ብሩክ ቃልቦሬ እና ፍሬው ሰለሞን ሁለቱን ተክተው ሲገቡ በግልፅ ታይቷል፡፡ በተለይም ፍሬው ወደ ፊትም ሆነ ወደ ጎን የተሳኩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አማካዮችን ከአጥቂዎች ጋር በማገናኘት እንዲሁም ከቡድኑ ተነጥለው ለታዩት የመስመር አማካዮች የመቀባበያ አማራጭ በመፍጠር የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል፡፡

( የተጫዋቾቹ የአጨዋወት ባህርይ እና የቡድኑ አጨዋወት ጋር አልተጣጣመም ማለት ተጫዋቾቹ ደካማ ናቸው ማለት እዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ )

ሽግግር…

ሽግግር (transition) በዘመናዊ እግርኳስ በተለይም ባለፉት 5 አመታት የታላላቅ ቡድኖች የስኬት መሰረት ሆኖ በስፋት እያገለገለ ይገኛል፡፡ ቡድኖች ከመከላከል ወደ ማጥቃት ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርጉት የሽግግር ፍጥነት ወይም ዝግመት መጠን ውጤታቸው ላይ ተፅእኖ ያሳድራል፡፡ በኢትዮጵያ ክለቦች ይህ አጨዋወት እምብዛም ባይለመድም አሁን አሁን ፈጣን የመስመር ተጫዋቾችን የያዙ የሊጉ ቡድኖች ይህንን አጨዋወት ሲተገብሩ ተመልክተናል፡፡ እንደ ቡድን ደደቢት ከሌሎች ክለቦች በተሻለ አጨዋወቱ ስኬታማ ሆኖለት ታይቷል፡፡ ቡድኑ ኳስ የማይቆጣጠር ቢሆንም ወደ መሃል ሜዳ ቀርቦ በመከላከል ኳስን ሲነጥቁ በፈጣን የመስመር ሽግግር (attacking flank transition) ወደ ግብ ሲደርሱ አስተውለናል፡፡ የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ሳሚ ሳኑሚ አመዛኙን ግብ ከመረብ ያሳረፈው እንዲህ ባለ አጨዋወት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ መነሻነትም ከኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በንፅፅር ለአጨዋወቱ ተስማሚ የሚመስሉትን አስቻለው ግርማ እና በኃይሉ አሰፋን በተለይም ለኢትዮጵያ ቀላል ተጋጣሚ ይሆናሉ ተብለው የታሰቡት ሌሴቶ እና ሲሸልስ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ቢተገብሩት አዋጭ ሊሆን ይችላል፡፡ ከአፍሪካ ቡድኖች በፈጣን የሽግግር አጨዋወት ከሚታወቁት አልጄርያ ጋር በሚደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኑ በተለይ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረጉ ሽግግሮች ላይ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል፡፡ ቡድኑ ኢትዮጵያ ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ስንመለከት በተለይ በመስመር ለሚደረጉ የሽግግር አጨዋወቶች ትኩረት መስጠት እንዳለብን ያስገነዝበናል፡፡

የማጥቃት አጨዋወት

ብሄራዊ ቡድናችን እንደ ሊጉ ክለቦች ሁሉ ባለፉት 10 አመታት 4-4-2ን በአመዛኙ ተጠቅሟል፡፡ ቡድናችንን ባሰለጠኑት አሰልጣኞች ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ የምንመለከተው አንድ አይነት አጨዋወት ያላቸው የሳጥን ውስጥ አጥቂዎች የማሰለፍ ሁኔታ በወቅ የአጥቂዎች ባህርይ ምክንያት ተመሳሳይ መልክ ይዞ ሊቀጥል ይችላል፡፡

በዚህ ዘመን የፊት አጥቂዎች ዋነኛ ስራ ግብ ከማስቆጠር ይልቅ ወደ ጎን እና ወደ ኃላ ከኳስ እና ያለኳስ እንቅስቃሴ በማድረግ የተጋጣሚ ተከላካዮችን ቅርፅ እና ትኩረት መበታተን ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን ፈጣን የመስመር አጥቂዎች እና ወደኋላ ያፈገፈጉ አጥቂዎችን (false 9) ከተከላካዮች ትኩረት በማራቅ በቀላሉ ግብ እንዲያስቆጥሩ የሚያመቻቹ ናቸው፡፡

የብሄራዊ ቡድን አጥቂዎቻችን ጌታነህ እና ሳላዲን ተመሳሳይ አጥቂዎች ሲሆኑ ሁለቱም በአንድ ላይ ማሰለፍ በተከላካዮች ትኩረት ስር እንዲቆዩና በቀላሉ ለመቆጣጠር አመቺ እንዲሆኑ ከማድረጉ በተጨማሪ እንቅስቃሴያቸው ሳጥን ውስጥ የተገደበ ስለሚሆን ከጫና ነፃ የሚሆኑት የተጋጣሚ የመስመር ተከላካዮች በነፃነት ወደፊት እንዲጓዙ እድልን ይፈጥራል፡፡ አሁን በቡድኑ ካሉት አጥቂዎች በንፅፅር ኡመድ ኡኩሪ ከውስጥ ወደ መስመር እንዲሁም ከመስመር ወደ ውስጥ በመግባት አደጋ የመፍጠር ብቃት ባለቤት በመሆኑ የብሄራዊ ቡድኑ አሰላለፍ በሁለት አጥቂዎች የሚመሰረት ከሆነ ከአንደኛው ጋር ተጣምሮ የተሻለ ሊግባባ ይችላል፡፡

የህዝቡን እምነት ማጣት

ብሄራዊ ቡድኑ በታሪኩ ከፍተኛ ወደተባለ ከፍታ ከደረሰበት ውጤታማ ጉዞ በኋላ በፍጥነት ቁልቁል መውረዱ (ከናይጄርያ ጋር በተደረገው የአለም ዋንጫ የፕሌይ ኦፍ ግጥሚያ እና ኢትዮጵያ ምንም ግብ ሳታስቆጥር በተሰናበተችበት ቻን መካከል የነበረው የጊዜ ክፍተት 3 ወራት ብቻ ነበሩ፡፡) ብሎም ከዛ ወዲህ ወደ ውጤታማነት አለመመለሱ ህዝቡ እና ከሞላ ጎደል አብዛኛው የመገናኛ ብዙሃን በቡድኑ ላይ የነበረው ተስፋ እንዲሟጠጥና ‹‹ ድሮም የኢትዮጵያ ኳስ›› ወደሚል ተስፋ የመቁረጥ ንግግር እንዲያመራ አድርጎታል፡፡ የዮሃንስ ሳህሌ ቡድንም ለውጤታማነት የሚያስፈልገው የህዝብ እና የመገናኛ ብዙሃን ድጋፍ መቀዝቀዙ በውጤታማነቱ ላይ ጉልህ ተፅእኖ ማሳረፉ የማይቀር ነው፡፡ ቡድናችን የህዝቡን እምነት መልሶ ለማግኘት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የግድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ የማሸነፍ ግዴታ ደግሞ ቡድኑን ጫና ውስጥ መክተቱ የማይቀር ነው፡፡

መልካም እድል ለዋልያዎቹ !!!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *