አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ እና ወልድያ ተለያይተዋል

ያለፉትን ሁለት የውድድር አመታት ወልድያን ያሰለጠኑትና ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጎ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ እንዲያጠናቅቅ የረዱት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከወልድያ ጋር በስምምነት መለያየታቸውን ክለቡ ይፋ አድርጓል፡፡

የክለቡ የቦርድ አመራር አባላት ትላንት ባደረጉት ስብሰባ በስምምነት መለያየታቸውን የገለፀ ሲሆን የመለያየታቸውን ምክንያት ግን ሳያሳውቅ ቀርቷል። ክለቡ አያይዞ ምክትል አሰልጣኙ ኃይማኖት ግርማ እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ ይልማ ከበደ ከክለቡ ጋር እንደሚቆዩ የገለጸ ሲሆን ወልድያን በዋና አሰልጣኝነት ተረክቦ የሚሰራውን አሰልጣኝ በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ተናግሯል ።

ከወልድያ  ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በክለቡ ዙርያ ያለሉ አካላትን ለነበራቸው ቆይታ አመስግነዋል፡፡ በወልድያ የነበረው ቆይታቸው በጣም አድካሚና አስደሳች እንደነበር ገልጸው ከጤና ጋር በተያያዘ ጉዳይ ከክለቡ መለያየታቸውን ተናግረዋል፡፡  በቆይታቸው ለተደረገላቸው ድጋፍም ደጋፊውን ፣ የቡድኑን አመራር ፣ የከተማው ከንቲባን አመስግነዋል። አንዳንድ ደጋፊዎች ከእግር ኳስ መርህ የወጣ ተቃውሞ ለክለቡ ቀጣይ ጉዞ እንደማይጠቅም ጠቆም አድርገውም አልፈዋል።

የአንደኛው ዙር መጠናቀቅን ተከትሎ በአንዳንድ ደጋፊዎች ተቃውሞ የተነሳ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ለክለቡ የመልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው ከውይይቶች በኋላ ወደ ክለቡ አሰልጣኝነት መመለሳቸው የሚታወቅ ነው።

የቀድሞው የመከላከያ ፣ ደደቢት እና ንግድ ባንክ አሰልጣኝ በቀጣይ ማረፊያቸው የት እንደሆነ ከመናገር የተቆጠቡ ቢሆንም ሶከር ኢትዮዽያ ባደረገችው ማጣራት በቅርብ ቀናት ውስጥ የቀድሞ ክለባቸው ደደቢትን በዋና አሰልጣኝነት ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህ የሚሆን ከሆነ ለአሰልጣኝ ረጅም ጊዜ የመስጠት ትዕግስት ያጣው ደደቢት በ2005 በክለቡ ታሪክ የመጀመርያውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሲያገኝ አሰልጣኝ የነበሩት ንጉሴን ካሰናበተ ከ3 አመታት በኋላ በድጋሚ የሚቀጥር ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *