በኢትዮጵያ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ ከተለመዱ ጉዳዮች አንዱ የተጫዋቾች ለሁለት ክለብ መፈረም እና ውዝግብ ውስጥ መግባት ዋነኛው ነው፡፡ ክሪዚስቶም ንታምቢም አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ተጫዋች ሆኗል፡፡
ክሪዚስቶም ንታምቢ ጅማ አባ ቡናን ለቆ አዳማ ከተማን ለመቀላቀል መስማማቱ የሚታወስ ሲሆን በትላንትናው እለት ደግሞ ከአዳማ የተሻለ ክፍያ ካቀረበለት ኢትዮጵያ ቡና ጋር ተስማምቶ በይፋ ለመፈረም በፌዴሬሽን በተገኘበት ወቅት በስፍራው በአጋጣሚ ከነበሩት የአዳማ ከተማ አመራሮች ጋር ፊት ለፊት መገናኘቱ ተጫዋቹን አጣብቂኝ ውሰጥ ከቶታል፡፡
አዳማ ከተማ ከተጫዋቹ ጋር በደሞዝ ተስማምቶ የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት እስኪከፈት ድረስ ቅድመ ኮንትራት መፈረሙን በመግለጽ የፈረመበትን ማስረጃ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያቀረበ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም ተጫዋቹ የክለቡ ንብረት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዳስገባ ታውቋል፡፡
ከኢትዮዽያ ቡና ህዝብ ግኑኙነት ባገኘነው መረጃ የንታምቢ ተገቢነት ለክለቡ መሆኑን የገለፁ ሲሆን አዳማ ሰነድ ላይ የፈረመው የዝውውር መስኮቱ ሳይከፈት በመሆኑ እና ይህ ደግሞ ህጋዊ መሰረት የሌለው ስለሆነ ፌዴሬሽኑ ትክክለኛ ውሳኔ በመወሰን የኢትዮዽያ ቡና ተጨዋች ያደርገዋል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ጉዳዩን ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የመራው ሲሆን በቀጣዩ ሳምንት መጀመርያ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ንታምቢ ለሁለቱም ክለቦች ፈርሞ ከተገኘም በደንቡ መሠረትም ከፍተኛ ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡
በዘንድሮው ክረምት የንታምቢ አይነት ጉዳይ ሲከሰት የመጀመርያው አይደለም፡፡ ወደ ወልዲያ ያመራው ብሩክ ቃልቦሬ በቅድሚያ ለኛ ፈርሟል በማለት ድሬዳዋ ከተማ ክስ ማቅረቡ እና ጉዳዩ በፌዴሬሽን እየታየ መሆኑ ይታወቃል፡፡