የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሀዋሳ አምርቷል

የኢትየጵያ ብሄራዊ ቡድን ኬንያ በ2018 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) ለማለፍ የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ 10:00 ሰዓት በሃዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ያደርጋል። ከጨዋታው በፊት ቡድኑ ለአቋም መለኪያ ይረዳው ዘንድ ወደ ዛምቢያ አቅንቶ ጨዋታውን በአቻ ውጤት ያጠናቀቀ ሲሆን ቡድኑ ትላንት ምሽት አዲስ አበባ ገብቷል።

ብሄራዊ ቡድኑ ዛሬ ረፋድ ላይ ጨዋታው ወደሚደረግበት ሀዋሳ ያመራ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በዛምቢያው ጨዋታ ያሉትን ተጨዋቾች ከተመለከቱ በኃላ የፋሲል ከተማውን የግራ መስመር ተከላካይ አምሳሉ ጥላሁን ቀንሰው በቦታው የአርባምንጭ ከተማው ተካልኝ ደጀኔን ወደ ቡድኑ ጠርተዋል። በተጨማሪም አሰልጣኙ ባሳለፍነው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ለቆ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያመራው ታደለ መንገሻን ወደ ስብስባቸው ያካተቱ ሲሆን ውሳኔው ቡድኑ በመስመር አማካይ በኩል ያለበትን ክፍተት ለመድፈን ይረዳዋል ተብሎ ይታሰባል።

ብሄራዊ ቡድኑ በሀዋሳ ሳውዝ ስታር ሆቴል ማረፊያውን ያደረገ ሲሆን በዛሬው እለት ከሰዓት ልምምዱን አከናውኗል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *