​ዋሊድ አታ ለአዲሱ ክለቡ የሊግ ግብ አስቆጥሯል

በናጅራን ስፖርት ክለብ ጋር የነበረውን ውል በስምምነት አፍርሶ ለአል ካሊጅ ለመጫወት የፈረመው ዋሊድ አታ በሳውዲ አረቢያ አንደኛ ዲቪዚዮን የመጀመሪያ ግቡን በማስቆጠር አል ካሊጂ ወሳኝ አንድ ነጥብ ከሜዳው ውጪ እንዲያገኝ ረድቷል፡፡

ጅዳ በሚገኘው ኪንግ አብደላ ስፖርትስ ሲቲ ሪዘርቭ ስታዲየም የተደረገው የጅዳ እና አል ካሊጂ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል፡፡ ባለሜዳዎቹ ለረጅም ደቂቃዎች ሲመሩ የቆዩ ሲሆን የመሃል ተከላካዩ ዋሊድ በ87ኛ ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ክለቦቹ ነጥብ ተጋርተው ጨዋታቸውን እንዲጨርሱ አስችሏል፡፡ ዋሊድ ከኢትዮጵያዊ እናት እና ኤርታራዊ አባት በተወለደባት ሳውዲ ግብ ሲያስቆጥር የመጀመሪያው ሲሆን የስዊድኑ ኦስተርሰንድስ 4-2 በተረታበት የሊግ ጨዋታ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ ካሳረፈ በኃላ በነጥብ ጨዋታ ግብ ሳያስቆጥር ቆይቷል፡፡

አል ካሊጅ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በፕሪንስ ናያፍ ቢን አቡደልአዚዝ ስፖርትስ ሲቲ ስታዲየም አል ሙጃዛል ክለብን አስተናግዶ 1-0 መርታት የቻለ ሲሆን በግብ ክፍያ ተበልጦ በ4 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ከሳውዲ ፕሮፌሽናል ሊግ እንደ አል ካሊጅ ሁሉ የወረደው አል ዋህዳ ክለብ ሊጉን በ4 ነጥብ ሲመራ አል ሾአላ፣ አል ናሃዳ፣ ሃጃር ኤፍሲ አል ሃሳ፣ አል ኦሩባ እና አል ቃኦማ ሌሎች ተመሳሳይ ነጥብ ያላቸው ክለቦች ናቸው፡፡

በሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ አል ካሊጅ በሜዳው አል ጣሂልን የሚስተናግድ ይሆናል፡፡ ሁለት ክለቦች በቀጥታ ወደ ዋናው ሊግ ሲያድጉ ሶስተኛው አዳጊ ክለብ ደግሞ በመለያ ጨዋታ የሚያልፍ ይሆናል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *