የዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ

10:30 | የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር ፌዴሬሽኑ ለችግሮቹ ተግባራዊ እርምጃዎች እስኪወስድ ከነገ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 3 ሳምንታት ማንኛውም ውድድር ላለመዳኘት ከውሳኔ ላይ ደርሷል።

08:48 | በአሁኑ ሰዓት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ብቻ ቀርተው ውይይት ማድረግ ጀምረዋል። የአቋም መግለጫም ይጠበቃል።

ልዑልሰገድ በጋሻው (የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ)

” አንድ ቡድን መሪ ሁኔታ ሊያረጋጋ ሲገባው እያሳደደ መደብደብ ተቀባይነት የለውም። ይህ ጠበቅ ያለ ውሳኔ ያስፈልገዋል። ”

” ነገ የተጠራውን ስብሰባ አልደግፈውም። ምክንያቱም እኛ ስንሰደብ ለመስማት ነው ስብሰባ የሚጠራው? ለምሳሌ ” ለሚ የእጁን ነው ያገኘው” ያለኝ የክለብ አመራር አለ። ”

“የማህበሩ ውሳኔ ቀጣይነት ይኖረዋል ወይ? ከአመታት በፊት የአአ ዳኞች አንዳኝም ብለው ከሌሎች ቦታዎች ሲዳኙ ተመልክተናል። ”

” ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ የሚባለው ካልቀረ በቀር አንዳኝም ማለት አለባችሁ። ” 

” ፊታችሁ ቆሜ ያለ ሀፍረት መናገር እፈልጋለሁ። ስለ ዳኛ ነፃነት ፣ ስለ ሰው ልጅ መብት ለማውራት መሰብሰባችንን አደንቃለሁ። ወቀሳውም ንግግሩም አግባብ ነው። ”

” እግርኳስ ራሱ ፖለቲካ ነው። እናንተ መስደብ የምትችሉት ፌዴሬሽንን ብቻ ስለሆነ ነው የምትሰድቡን። ሌላውን አካል ለመስደብ ለምን አትሞክሩም? ስለማትችሉ! ”

” ስርዓት አልበኝነትን የበዛው እኛ ስላልሰራን ነው ወይስ ዘረኝነት እና ክልላዊነት ስለነገሰ ነው? ንግግራችሁ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ሆኗል። ”

አበበ ገላጋይ

” መድረክ የሚመሩ ሰዎች የራሳቸውን ተልዕኮ እያስፈፀሙ ነው። ” ለሚካኤል አርዓያ የሰጡት መልስ

” የፕሪምየር ሊጉ በአስቸኳይ እንዲቋረጡ ያደረግነው ክለቦች ወደ ጨዋታ ቦታቸው ስላልተንቀሳቀሱ ነው። ከፍተኛ ሊጉ ግን አብዛኛዎቹ ጉዞ አድርገዋል። ፋሲል ከተማ ከውሳኔው በፊት አዲስ አበባ ደርሶ ስለነበር ወደ ጎንደር ተመለሱ ማለት ከብዶናል። እንዲጫወቱ አዘናል ”

” …ሁኔታው እልባት እስኪያገኝ ድረስ ግን ሁሉም ውድድር ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ እንዲቋረጥ ወስነናል። ”

ሚካኤል አርዓያ

” እኛ የፌዴሬሽን የምርጫ ማስፈፀሚያ መሳርያ መሆን አንፈልግም።”

” ዛሬ ስብሰባ ለማድረግ እንኳ ብዙ መሰናክል ገጥሞናል። የፌደሬሽኑ ዋና ፀኃፊ አቶ ሰለሞን ይህ ስብሰባ እንዲደረግ አልፈቀዱም ነበር።”

” ህግ በፌዴሬሽን ተጥሷል። አሁን የወልዲያ እና የወልዋሎ እያልን የምናነሳው ከአመታት በፊት ህግ እየተጣሰ እዚህ ደርሰን ነው። ”

” ለእኛ ስራ የምናመሰግነው እግርኳስ ፌዴሬሽን ሳይሆን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ነው። ስታድየም ልምምድ እንድንሰራ እና ሙያዊ እገዛ የሚያደርግልን አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ነው። ”

” ምርጫ ተመርጦ ህጋዊ ፌዴሬሽን እስኪኖር ድረስ ስራ ማቆም አለብን። ” 

ቴዎድሮስ ምትኩ

” እኔ እያሱን ብሆን ምን ላደርግ እንደምችል አላውቅም። ለምን አልቀጣም። ምን ሊቀርብኝ ነው? (በለቅሶ ታጅቦ የተናገረው..) ”

” ክብር ያጣነው በተመልካች እና ተጫዋች አይደለም። በፌዴሬሽኑ ነው የተዋረድነው። እባካችሁ አስከብሩን (በለቅሶ ታጅቦ የተናገረው) ” 

ቦጋለ አበራ

” ስለተጎዱ ዳኞች ህክምና ምን እየታሰበበት። ከማኅበራችን ግለሰብ ተወክሎ የሜዳዎችን ደህንነት አብሮ መገምገም አለበት። ”

” እኛ ተጨማሪ ስራ ያለን ሰዎች ነን። መዳኘት ቢቀርብን የምንጎዳው ነገር የለም። አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ግን ስራቸው ነው ሊያስቡበት ይገባል።

ተስፋዬ ኦሜጋ

” አንድ አቋም በመያዝ ለካፍ እና ፊፋ ማሳወቅ አለብን። በዚህ ሁኔታ ማጫወት እንደሌለብን አቋማችንን መግለፅ አለብን።

” እንደነ ባምላክ ያሉ አምባሳደሮቻችን በውጪ ሀገራት በሞተር ታጅበው ይንቀሳቀሳሉ። እዚህ ደግሞ እንደ ሌባ ይታያሉ።”

” ተጫዋቾች እኮ መደብደብ አይደለም የጎል ብረቱ ላይ መስቀል ነው የቀራቸው። ከዚህም የባሰ ነገር ሳይከሰት ስለ ክልል እና ፖለቲካ ማሰብ ትተን አንድ አቋም መያዝ አለብን። ” 

ክንዴ ሙሴ

” ፕሪምየር ሊጉ ብቻ አይደለም መቋረጥ ያለበት። የባሰ ጥሰት እየተፈፀመባቸው የሚገኙት ሌሎች ሊጎችም መቋረጥ አለባቸው። ”

” ውድድሩ ከቀጠለ በዳኞች ኢንሹራንስ ዙርያ ይታሰብበት።” 

ሊድያ ታፈሰ

” የተሰበሰብነው ስሜታችንን ለመግለፅ ብቻ ሳይሆን አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆን አለበት

” ዳኝነት ሜዳ ላይ ወድቆ ሲደበደብ በአደባባይ ታየ። እኔ በበኩሌ ዳኛ ነኝ ለማለት አፍሬያለሁ። ክብር እና ማንነቴ እንዲዋረድ አልፈልግም

” ሙያችን መሬት ላይ ወድቆ ሲደበደብ አየን። እያሱ ሳይሆን የተደበደበው ፍትህ እና ዳኝነት ነው።

” እኔ ስወስን ተመልካች፣ አመራር እና ተጫዋች ካልቀበለኝ እኔ ሜዳ ውስጥ ምን እሰራለሁ?

” ቀጪ የተቀመጠበት ቦታ ላይ ቅጣት አንሺ ምን ይሰራል?

” ፌዴሬሽኑ ሜዳ አውርዶ ነው ያስደበደበን። እፈሩ ፤:ልታፍሩ ይገባል። ማህበሩ የእኛ እያንዳንዱ ቁስል ይሰማችሁ ፤ መስራት ካልቻላችሁ ውረዱ ፤ አላሰራ ካላችሁ ደግሞ ማህበሩ ራሱ ይቅር። ”

ኤፍሬም ደበሌ

” የወልዋሎው ቡድን መሪ ሚድያ ላይ ቀርቦ ተጫዋቾቼ ዳኛውን እንዳይከተሉ ለማገድ ነበር የሄድኩት። እያሱ የማዕዘን ምት ምልክቱን ነቅሎ ሲሮጥ ሊማታ መስሎኝ ነው የተማታሁት ሲል ነበር። ቅጣቱ እንዲቀልለት ነው? ለነገሩ ቢቀጣም ይነሳለታል..

” ማህበራችን ራሱ ምን እየሰራ ነው? ስራዎችን ለመስራት ዳኞች እና ኮሚሽነሮች እስኪሞቱ ነው የሚጠበቀው? ጋዜጣዊ መግለጫ ብቻ ምን መፍትሄ አመጣ? ቢያንስ ከወልዲያ ጀምሮ የተወሰኑ ውሳኔዎች በድጋሚ እንዲጤኑ ጫና አሳድሩ። ካልሆነ ከአመራርነት ቦታው ልቀቁልን። ”

ሚካኤል ጣእመ

” የክልል ፖሊሶችን አምነን የምንዳኝ ሰዎች ተሳስተናል። ጂንካ ላይ እኮ ዳኝተን ስንወጣ አንድ ፖሊስ ብቻ ነበር ያጀበን። እንደ ደሬዳዋ ያሉ ሊመሰገኑ የሚገቡ ከተሞችም አሉ።

” እግርኳስ እና ፖለቲካ አትቀላቅሉብን። በፊፋ ህግ መንግስት ጣልቃ የማይገባ ከሆነ ለምንድነው ፖለቲከኞች እየመጡ የሚያዙን። ” እኛ እንዲህ ስለሆንን ነው እንዲህ የምታደርጉት…” ሲሉን ” እኛ አያገባንም በህጉ መሰረት ነው የምንዳኘው ” ብለን ስንመልስ ፌዴሬሽኑ ግን በጎን እነሱን እየሰማ እና እየተጠመዘዘ ነው ችግር እየተፈጠረ ያለው።

” ነጥብ መቀጣት ጥሩ ነበር። ክለቦች የገንዘብ ቅጣት ከተቀጡ የህዝብ ገንዘብ ነው ለመክፈል አይቸገሩም።

” እኛ ባናጫውት የሚቀርብን ነገር የለም። ፌዴሬሽኑ ከፈለገ በዶላር እየከፈለ ዳኛ ማስመጣት ይችላል። እስኪ የትኛው ክለብ ነው ኢንተርናሽናል ጨዋታ ላይ የውጪ ዳኛ ሲዳኘው የሚቃወመው?

” ሀገሪቱ እኮ የምትጠራው በነ ባምላክ እና ሊዲያ እንጂ በጊዮርጊስ እና ቡና አይደለም። ”

” ዳኛ የሚያባልጉት ክለቦች ናቸው ፤ ዳኛ የሚሰድቡት ክለቦች ናቸው። ምክንያቱም አመራሮች ጥቅም ፍለጋ ነው የሚሯሯጡት ፤ ከፕሪምየር ሊጉ ቢወርዱ በጀታቸው ስለሚቀነስባቸው እንጂ ለከተማቸው እና ለህዝባቸው አስበው አይደለም። ደጋፊ ሲረብሽ እኛን አይወክሉም እያሉ የሚክዱት እኮ ለከተማቸው ስለማያስቡ ነው።

” ሁኔታዎች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እስኪመጣ ድረስ ባናጫውት መልካም ነው። የሚከፈሉ ቅጣቶች ለምንድነው በኢንሹራንስ መልክ ዳኞች መልከ የማይሰጠው።

” እስኪ ውድድሩ ይዘጋ እና የሚሆነውን እንይ… የተጎዱ ሰዎች እስኪያገግሙ ማጫወት የለብንም ማለት አለብን።

” ሚድያዎች ከአአ ወጣ ብላችሁ እዩ ፤ ግጦሽ መሬት ላይ ተጫወቱ እየተባለ አይሆንም ስንል ብቁ ነው አጫውቱ እንባላለን። አጥር በሌለው ሜዳ ላይ እያጫወትን በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከገባ እንደ ሀጢያት ነው የሚቆጠረው። ”

እያሱ ፈንቴ

” በምን ቋንቋ መናገር እንደምችል አልገባኝም። በእግርኳስ ቋንቋ ላውራ ብል ፖለቲካ ይባልብኛል። እኔ በወቅቱ ብቸኝነት ነው የተሰማኝ፤ ሁኔታው ሲፈጠር ቆሞ ከመመልከት ውጪ ሊገላግል የመጣም የለም። ፍፁም ገብረማርያም ብቻ ነው እገዛ ለማድረግ ሲጥር የነበረው። ሁኔታው ጠባብ እንድሆን ፣ ሀገሬ ላይ ቢሆን ኖሮ ነው ያስባለኝ። አንድ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ስደበደብ ቆሞ ማየት ነበረበት? ይህ የማይሰማው አካል ካለ በጣም ያሳዝናል።

” እኔ በብሔር ምክንያት ጨዋታውን ማጫወት የለበትም ከተባለ መነሳት ነበረብኝ። ነገር ግን ፕሪ-ማች ላይ ምንም ነገር ሳይነሳ ሜዳ ውስጥ ስሰማ የነበረው ነገር በሙሉ ዘግናኝ ነበሩ። ጨዋተው በሰላም እንዲያልቅ ብዙ ነገር ተቋቁሜ ነበር እስከ ድብደባው ድረስ የዘለቅኩት። ዛሬ በቴሌቪዥን ታይቶ ትኩረት አገኘ እንጂ እስከዛሬ ስንደበደብ ፌዴሬሽኑ የት ነበር? ማህበሩ የት ነበር? ከዚህ በኋላ ዳኝነትን ልቀጥል አልቀጥል ፈጣሪ ነው የሚያውቀው..”

ለሚ ንጉሴ

” ወልዲያ ላይ ከሚገባው በላይ ተደብድበናል። ሙስጣፋ ብዙ ደም ፈሶታል። ያለ ገላጋይ በግልፅ ነው የተደበደብነው። እኔ እንደሞትኩ ነው የምቆጥረው። ጉዳቱ አካሌ ላይ የደረሰ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቤ ፣ ልጆቼ ፣ ጎረቤቶቼ ፣ የስፖርት አፍቃሪው ፣ ዘመዶቼ ፣ ዳኞች እና ሁኔታውን የተመለከቱ ሁሉ ጉዳት ነው።

” ዳኝነት የህይወት መስዋዕትነት ሊከፈልበት የሚገባ ሙያ አይደለም። እኛ የፊፋን ህግ የሚተገብር ሙያተኞች እንጂ ጦር ሜዳ የዘመትን ወታደሮች አይደለንም።

” ላሉበት አካባቢ ወገንተኛ የሆኑ የፀጥታ አካላት ይህን ተግባር ማቆም አለባቸው ፤ ውጤትን አላግባብ ለማግኘት የሚፈልጉ የክለብ አመራሮች ከራሳቸው ፍላጎት በዘለለ ማሰብ አለባቸው ፤ የደጋፊ አስተባባሪዎችም የጨዋታ መንፈስ እንዳይረበሽ ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ዋስትናችን ምንድነው። ”

የዳኞች እና ታዛቢዎች የሙያ ማህበር ፕሬዝዳንት – ትግል ግዛው

” በወልዲያ ላይ የዲሲፕሊን ኮሚቴ የወሰነው ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ያረካን ባይሆንም ለወሰነው ውሳኔ አድናቆት አለን። ነገር ግን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው የወሰነው የቅጣት ማቅለያ ሙያችንን በእጅጉ ያረከሰ እና ከጠበቅነው በታች የሆነ ‘አሳፋሪ’ ውሳኔ ነው። ውሳኔው ” ዳኛው ዛሬ ቢጎዳም ነገ ማጫወቱ አይቀርም” ከሚል የመነጨ የሚመስል እና አግባብነት የሌለው ነው። ይህ ለእያንዳንዳችን ዳኞች ቁስል የፈጠረ ውሳኔ ነው። ”

” የወልዋሎው ቡድን መሪ የፈፀመውን ድብደባ በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲጠየቅበት እናደርጋለን። ይህን የማድረግ መብቱም አለን። “