እያሱ ፈንቴ በወልዋሎ ቅጣት ዙርያ አስተያየቱን ሰጥቷል

ሚያዝያ 22 ቀን 2010 በአአ ስታድየም የተደረገው የመከላከያ እና ወልዋሎ ጨዋታ በዳኛው እያሱ ፈንቴ ላይ በደረሰ ድብደባ መቋረጡ ይታወሳል። የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴም ባለፈው ዓርብ ጥፋተኛ ናቸው ባላቸው ተጫዋቾች እና የቡድን መሪው ላይ ከ6 ወር እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣቶች አስተላልፏል።

የተወሰደውን የዲሲፕሊን ውሳኔ ተከትሎ ከወልዋሎ እግርኳስ ክለብ አመራሮች እና ደጋፊዎች ዘንድ ውሳኔው “ኢ-ፍትሀዊ ነው” በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ በተለያዩ መንገዶች ሲገለፅ በዕለቱ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት የመራው እና በተጫዋቾች እና ቡድን መሪው ጥቃት የደረሰበት ፌደራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ ፌዴሬሽኑ የወሰደው የዲሲፕሊን ውሳኔ እንደጠበቀው አለመሆኑን ለሶከር ኢትዮዽያ በዚህ መልኩ ተናግሯል።

” እኔ ውሳኔውን በዚህ መንገድ አልጠብቅም ነበር። በቀደምም ሰምተሀል ቱርክ ውስጥ አንድ ተጨዋች ዳኛን ገፍቷል ተብሎ 16 ጨዋታ ሲቀጣ። ይህ ደግሞ እንዳያችሁት ቅንብር የነበረው ድብድብ ረዳት ዳኞች ወደ እኔ እንዳይደርሱ ተይዘው እኔ ብቻ ስደበደብ ታይቷል። ስለዚህ እኔ የምጠብቀው እንዳውም እነዛ ለመደብደብ የተጋበዙት ተጨዋቾች በሙሉ እድሜ ልክ ቅጣት ነበር የምጠብቀው። 2 – 1 በሆነ ውጤት ወልዋሎ በመከላከያ ተሸንፏል እኮ መመለት ይቻላል። የተሸነፍን ቡድን ፎርፌ መስጠት እንዲህ አይነት ቅጣት ሰምቼም አይቼም አላቅም። ለማንኛውም ቅጣቱ ተመጣጣኝ ነው ብዬ አላስብም።

” ይህን እውነት በመናገሬም ልቀጣ እንደምችል እጠብቃለው። ምክንያቱም እንደምታየው ነው ። ትልቁ ወንጀል እየሆነ ያለው በዚህ ዘመን እውነት መናገር ነው። ስለዚህ እቀጣለው ብዬ እሰጋለው ፤ እኔ በፌዴሬሽኑ እጅ ስላለው ። ግን እኔ ተቀጣው አልተቀጣው ግድ የለኝም ብዙ ከጀርባዬ ላሉ ዳኞች ነው የምናገረው። ከዚህ በኋላ የእኔ ጉዳይ ችግር የለውም። “