የአሰልጣኞች ገጽ – ወርቁ ደርገባ [ክፍል 3]

የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን ካለፉት ሳምንታት የቀጠለው የአሰልጣኝ ወርቁ ደርገባን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።

በዛሬው የክፍል ሦስት መሰናዷችን ስለ ቴክኒክ ጉዳዮች እናወጋለን። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።


ክፍል አንድን ማግኘት እዚህ ይጫኑ ፡ LINK


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


በተደጋጋሚ “ተጫዋቾቻችን በቴክኒክ ክህሎት የበለጸጉ ናቸው፡፡” የሚል አስተያየት ይዘወተራል፡፡ ይህን መሰል ምስክርነት የሚሰጡት ራቅ ብለው ያሉ አካላት ማለትም ተመልካቾችና የተወሰኑ የስፖርት ሚዲያ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ አብዛኛው የእግርኳስ ተመልካች ይህን መሰል ምልከታ ኖረውና “የኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ቴክኒካዊ ብቃት እያላቸው ነገር ግን አልተሰራባቸውም፡፡” ወደሚል ድምዳሜ እየተደረሰ ነው፡፡ ለተጫዋቾቹ የበለጠ ቅርበት ያላችሁ አሰልጣኞች በመሆናችሁና ለረጅም ጊዜ በስራ አብራችሁ ስለምታሳልፉ እነሱንና ችሎታቸውን በደንብ የማወቅ እውነታ ያለው እናንተ ጋር እንደሆነ እናስባለን፡፡ እውነት እግርኳስ ተጫዋቾቻችን የላቀ የቴክኒክ ተክህኖ ያላቸውና የሚባለውን ያህል <Technically Gifted> ናቸው?


★ ተሰጥኦን ማውጣት ወይም መለየት (Talent Scouting) በሚለው ስርዓት በአካዳሚና በግለሰቦች በሚቋቋሙ ማሰልጠኛ ማዕከላት ውስጥ የሚገቡት ልጆች ከመጀመሪያው ሲመረጡ የምታየው ይህንን ነገር ነው፡፡ “Is he talented or not?” – ባለ ክህሎት ነው ወይስ አይደለም? ከየሰፈሩ የሚወጡትን ልጆች እናውቃለን፤ እናያለን፡፡ ሆኖም ለልጆቹ በነበራቸው ተፈጥሮአዊ ችሎታ እንዲቀጥሉ የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀና ተገቢውን ስልጠና አልሰጠናቸውም፡፡ ተጫዋቾቹን በችሎታ መመዘኛዎች መሰረት አውጥሀቸዋል አልያም በጥሩ ክህሎት ባለቤትነት አይንህ ውስጥ ገብተው ወስደሀቸዋል፡፡ ችግሩ የሚጀምረው እዚህ ጋር ነው፡፡ ተጫዋቾቹ የነበራቸውን ችሎታ እንዲያጎለብቱ የሚሰጣቸው የስልጠና አይነት በትክክል ያንን ለማድረግ የሚያስችል ነው ወይ? ቴክኒካዊ ችሎታቸው በጥሩ ደረጃ የሚገኙ ልጆች አሉ፤ ሆኖም ጥራቱን የጠበቀ፣ በእድሜና በችሎታ ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ ስልጠና የሚያገኝበት ተቋም የለውም፡፡ በቃ በጉልበቱም በጥረቱም አንድ ክለብ ይገባል፤ አስፈላጊውን ስልጠና ሳያገኝ ያድጋል፤ በዚህ መንገድ ወደ ላይ ይመጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ቴክኒካል ስልጠና ለምን ያህል ጊዜ ይሰጠዋል? የእድሜ እርከንን ለማየት ስለሰራሁበት የአሰግድን አካዳሚ እንደ አብነት ላንሳ፦ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ለሚገኙ ልጆች የሚሰጠውን ልምምድ እንከታተልለታለን፡፡ ሰልጣኞቹ በሳምንት ሶስት ቀን የሚሰሩ ከሆነ “በየትኛው የስልጠና አይነት የበለጠ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል?” የሚለውን ትኩረት ሰጥተን እናየዋለን፡፡ ምክንያቱም ባለ ተሰጥኦ መሆናቸውን ተማምነናል፤ ስለዚህ በእድሜ ደረጃቸው የሚገባቸውን ስልጠና ቶሎ ቶሎ እንዲያገኙ እናደርጋቸዋለን፡፡ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችማ በየአካባቢው አሉ፤ ነገር ግን ደረጃውን የጠበቀና በእውቀት የታገዘ ክህሎት ማሳደጊያና መስሪያ ቦታ የለም፡፡ ይህንን እርግጠኛ ሆኜ ነው የምነግራችሁ – በኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ኳስ መጫወት የሚችሉ ልጆች አሉ፡፡ ልዩነቱ በሌሎች አገሮች በተሰጥኦ ላይ ይሰራል፤ እኛ አገር ግን አልሰራንባቸውም፡፡ የስልጠና ስራ ማለት እንዲሁ ዝም ብሎ ተጫዋቾችን ሰብሰብ አድርጎ ሮጥ ሮጥ በል፤ እንደዚህ አድርገህ ምታ፤……” አይደለም! የልጆቹ ጊዜ ሳያልፍ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ የሆኑ ቴክኒካዊ ክህሎት፣ ታክቲካዊ ግንዛቤና የተሻለ አካል ብቃት ይዘው ማደግ አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ ኖሯቸው ወደ ላይ ሲመጡ ደግሞ ተገቢውን ስራ ትሰራባቸዋለህ፡፡ እስካሁን በእግርኳሳችን በዚህ መልኩ አልሰራንም እንጂ የተጫዋቾች ችግር የለብንም፡፡ አንድ ትልቅ ማዕከል ተቋቁሞ በስልጠናው ዘርፍ ባሉ ሁሉም ጉዳዮች የበቁ ባለሙያዎችን ሰብስቦ ቢሰራ መልካም ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ አሁን በአካዳሚ መስራት ስለተጀመረ በማዕከሉ <Elite>ን እና <Mass>ን መለየት መቻል አለብን፡፡ በአካዳሚ ውስጥ ባለ ተሰጥኦ ያልሆኑ ግን ደግሞ የኳስ ፍቅር ያላቸው ልጆች ይገባሉ፡፡ እነዚህንና ባለ ክህሎት የሆኑትን በአግባቡ መለየት ሳንችል ካደባለቅናቸው “Talented” የሆነው የሚገባውን ስልጠና ልናሳጣው ነው፡፡ ስለዚህ የእግርኳስ አካዳሚ ሲከፈትም በተለይ ለባክህሎቶቹ ልዩ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ በመውደድ ደረጃ ለሚሳተፉትም እንዲሁ ጥሩ ክትትል እናደርጋለን፡፡ ይህንን የመለየትና በጠቀስኳቸው ዘርፎች የመመደቡን ስራ የሚሰራልህ ማን ይሆናል? ይኸው በእግርኳስ ማዕከሉ ውስጥ የሚገኘው የቴክኒክ ክፍል ነው! አሁን ያለው ሁኔታ ግን ድብልቅልቅ ያለ ነው፡፡ ቤተሰቦች ክፍያ እየፈጸሙ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ የሚሰራና ጥሩ ችሎታ ኖሮት እድገቱን በኳሱ ውስጥ ለማድረግ የሚመጣውን የመቀላቀል ውሳኔዎችን እናያለን፡፡ ይበልጥ የምንሰራው የትኛውን ልጅ ለማሳደግ ነው? ይህን የምታስተካክለው ችሎታ የሌለውን በመከልከል ሳይሆን በሰልጣኞች ብቃት ላይ የተመሰረተ ክፍፍል በማድግ ነው፡፡ ወጣቶች አካዳሚ ሲመሰረት ዋናው አላማ በሁሉም የስፖርት ዘርፍ በብስክሌቱ፣ በሩጫው ፣በእግርኳሱም ይሁን በሌሎችም በተመረጡ ሰልጣኞች ላይ እንዲሰራ ነበር፡፡ ሆኖም የተመረጡትና በአካዳሚው የመሰልጠን እድልን ያገኙት ልጆች ከየት ነው የተገኙት? በምን መስፈርት ተመረጡ? ትክክለኞቹ ሰዎች ተመልምለዋል? ለዚህ ነው ከአካዳሚው ልናወጣ የምንችለውን ልጆች ያላገኘነው፡፡ በእኔ እምነት መሰረታዊና ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና ላይ አልተሰራም፡፡ አካዳሚው የ’Elites’ ማዕከል ነው፤ ስለዚህ ስልጠናውን ከተጫዋቾቹ ተፈጥሮአዊ ችሎታ ጋር እያያያዝን መስጠት አለብን፡፡ስልጠናውና ስራው የግድ ነገ ለብሔራዊ ቡድን ሊጠቅሙ የሚችሉ ባክህሎት ተጫዋቾችን ከማፍራት ጋር መገናኘት አለበት፡፡


 

ሀሳቡን ያነሳነው <በተጫዋቾች ቴክኒካዊ ችሎታ> ዙሪያ የሚሰጡት አስተያየቶች ጥልቀት ባለው መሰረታዊ የቴክኒክ ግንዛቤ የተቃኙ ስለማይመስለን ነው፡፡ በሰፈር ውስጥም ሆነ በየስታዲየሞቹ በሚካሄዱት ጨዋታዎች በጥቂት ቁጥሮችና በተወሰኑ ምጣኔዎች የሚደረጉትን የሚቆራረጡና ልኬታቸውን ያልጠበቁ ቅብብሎች እናስተውላለን፡፡ አልፎአልፎ ለትንሽ ሰኮንዶች የሚታዩትና በመጠኑ ድግግሞሽ ያላቸው የተሳኩ ቅብብሎች የቴክኒክ ብቃት ማሳያ መሆን ይችላሉ ወይ?


★ አይደሉም! አይሆኑምም! ከላይ እንዳስቀመጥኩት አንድን ተጫዋች በቴክኒካዊ ችሎታ ለመገምገምና ‘ቴክኒካዊ ተሰጥኦ ያለው ነው? ወይስ አይደለም?’ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተቀመጡ መመዘኛዎች አሉ፡፡ ተጫዋቹን አንተ ሳታስተምረው በፊት በሚጫወትበት አካባቢ ያለውን የኳስ ቁጥጥር ችሎታ፣ የቅብብል ስኬት፣ እይታውን፣ በጭንቅላት የመግጨት ብቃቱንና ሌሎችንም ታያለህ፡፡ ይህን ተመልክተህና “በስልጠናው የበለጠ ብገራው የሚያድግ ነገር አለው፡፡” ብለህ ያለውን ተፈጥሮአዊ ነገር ታዳብርለታለህ፡፡ ደረጃውን ወደጠበቀ የስልጠና ስርዓት ውስጥም ታስገባዋለህ፡፡በመቀጠልም በዘለቄታዊነት፣ ተከታታይነት ባለውና በየእድሜ እርከኑ የሚያስፈልገውን ስራ ታሰራዋለህ፡፡ የትኛውም ተጫዋች ሁሉን ጨርሶና ችሎ አታገኘውም፤ ይልቁንም አሰልጣኙ የሚጨምርለት ነገር ነው ተጫዋቹን የበለጠ የሚያሳድገው፡፡ ተጫዋቹ እኮ 20% የሚሆን ይዞ አይመጣም፤ በስልጠናው ነው ትልቅ ተጫዋቾችነት ደረጃ ላይ የሚደርሰው፡፡


ስለዚህ ቴክኒካዊ ችሎታ በተፈጥሮ የተገኘ ተሰጥኦ ላይ ስልጠና ሲታከልበት የሚዳብር ብቃት ማለት ነው?


★ አዎ! በስልጠና መታገዝ አለበት፡፡ ያለበለዚያማ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሁሉንም ነገር ጨርሶ የምታገኘው ተጫዋች የለም፡፡ ማን አሰራውና!


በሀገራችንግርኳስ በብሔራዊ ቡድንም ይሁን በክለቦች “የቴክኒክ ኮሚቴ” ሚና አዘወትሮ የሚነሳው በአሰልጣኞች ሹምሽር ጉዳይ ነው፡፡ ሌሎች የተብራሩና ተጠቃሽ ኃላፊነቶቹ ምንድን ናቸው? የኮሚቴው አባላቶች የሚመረጡትስ እንዴት ባለ መንገድ ይሆን?


★ በእርግጥ በሀገሪቱ በተቋም ደረጃ ያለና በዲፓርትመንት ተለይቶ የተቋቋመ ሳይሆን በተናጠል በክለቦችና በብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚሰራ አካል ሲሆን ብዙውን ጊዜ አባላቱ ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት የሚመረጡ አሰልጣኞችም ይኖሩበታል፡፡ ከኮሚቴው የሚጠበቀው ሐላፊነት ገዘፍ ያለ ቢሆንም አባላቱ ስራውን የሚሰሩት አመቺ ጊዜ ሲኖራቸው ነው፡፡ በተደጋጋሚም በዚህ መንገድ የተለመደው አሰራር ላይ ጥያቄ አንስተን ” አግባብ አይደለም፤ አደጋ አለው፤… ችግራችንን ተረዱልንና ኮሚቴው በቋሚ ሰራተኞች ይመራ!” ብለን አቤቱታ አቅርበናል፡፡ ስራውን የሚሰራው አካል በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እየተዘዋወረና ይህ ካስቸገረም ባለሙያዎችን እየመደበ የሚያስተባብር መሆን አለበት፡፡ አስተማሪ ሆኖ ሲመቸው በሳምንት አንድ ጊዜ ሐሙስ-ሐሙስ እየተሰበሰበ ስለእግርኳስ ምን አውቆ ምን ሊሰራ ይችላል? እንግዲህ እኛ ጋሽ ታዴ ጋር ተጫዋች ሆነንና ከዚያም በፊት ከነበሩት ጊዜያት ጀምሮ የቴክኒክ ኮሚቴ አወቃቀርና አሰራር ይህን የሚመስል ነው፡፡ እንዲያውም የማስታውሰው በጋሽ ታዴ ቡድን ውስጥ የትጥቅ አቅርቦት ላይ የሚሰራው ሰው የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ነበር፡፡ ከመሰረቱ በዚህ መልኩ ተያይዞ የመጣና የማይለወጥ ዘርፍ ሆኗል፡፡ እግርኳስ በመደበኛነትና በቋሚነት “ስራዬ”ብለው ቀን በቀን አብረው በሚሰሩ፣ በችግሮች ዙሪያ ጥናት በሚያደርጉና ውጤቱን ከነመፍትሄ ሐሳቡ ለሚመለከታቸው አካላት – ለፌዴሬሽኑ፣ ለክለቦች፣ ለክልል የስፖርት ጽ/ቤቶች…የሚያቀርቡ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ዋናውና በትልቅ የተቋም ቁመና የሚመሰረተው የቴክኒክ ክፍል በየክልሎቹ የሚገኙትን የቴክኒክ ኮሚቴዎች እየተቆጣጠረ በየጊዜዉ ሪፖርቶችን እንዲያቀርቡ ማድረግና ምን እየሰሩ እንደሆነ መጠየቅ አለበት፡፡ አለበለዚያ በበጎ ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አወቃቀርና አካሄድ ብዙም አያስኬድም፡፡ እግርኳሱን የሚያስተዳድሩት ሰዎች “ቢያንስ ስፖርቱን ይወቁት!” የምንለውም ለዚሁ ነው፡፡ አመራሮቹ ቴክኒካል እውቀቱና ልምዱ ባይኖራቸውም በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን በዲፓርትመንት ደረጃ መመደብ አለባቸው፡፡ሪፖርቶች የሚቀርቡበት መንገድስ? ለምሳሌ በቅርቡ ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በጋና 5-0 ከተሸነፈ በኋላ ቴክኒክ ኮሚቴው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ሪፖርት እንዲያቀርቡ ጠየቃቸው፡፡ እሳቸውም ወደ ሶስት ገጽ የተጠጋ “ሪፖርት” አቀረቡ፡፡ ከዚያም በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ ውይይት ሳይደረግበት መዝገብ ቤት ገቢ ተደረገ፡፡ ሪፖርቶች እንዴት ባለ ስርዓት እና ለማን መቅረብ ይኖርባቸዋል? አሰልጣኙን ገምግሞ ሪፖርት ማዘጋጀት ያለበት አካልስ ሊኖር አይገባም?


★ በትክክል መኖር አለበት እንጂ! የአሰልጣኙን ሪፖርቶች የሚቀበለው ቴክኒክ ዲፓርትመንቱ ወይም ኮሚቴው ነው፡፡ አሰልጣኙ የመሰለውን ሊጽፍ ይችላል፡፡ ይህን ጽሁፍ እየገመገመ አሰልጣኙን ቁጭ አድርጎ ጥያቄዎችን ማንሳትና ስለቀረበው ሪፖርት ማብራሪያ እንዲሰጥ ማድረግ አለበት፡፡ እኔ በፊት ከነመንግስቱ ጋርም ይሁን ለብቻዬ ስሰራ በተለመደው ሁኔታ “ሪፖርት አቅርቡ!” እንባላለን፡፡ ሪፖርቱን ስንጨርስ እናስገባለን፡፡ “ኮሚቴው ሐሙስ ይሰበሰብበታል፡፡” ተብሎ ውጤቱን እየጠበቅን በመሀል በጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ እንሄዳለን፡፡ “በቃ ተዉት! እሱ እኮ የለም፡፡” ይባልና ይቀራል፡፡ ቴክኒክ ኮሚቴ ተቋማዊ የሆነ መደበኛ ክፍል ቢኖረው ግን በእያንዳንዱ ጨዋታ ስለሚኖር ክስተት፣ እየተሰጠ ስለሚገኘው ስልጠና፣ እያጋጠሙ ስላሉ ችግሮችና ሌሎችም ሒደታዊ ሁነቶችን የሚያሳዩ መረጃዎች ይቀመጣሉ፡፡ ግምገማውም በነዚህ ወቅታዊ በሆኑ መረጃዎች ላይ ይመሰረትና ይደረግ ነበር፡፡አባለቱ እኮ ደስ ሲላቸው ነው የሚመጡት፤ ማን ይጠይቃቸዋል? የእግርኳስ ስራ በየቀኑ ጥብቅ ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ ቋሚ ዲፓርትመንት አለመኖሩ እና አባላቱ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ በጎ ፈቃደኞች መሆናቸው አሰራሩን እድገት እንዳይታይበት አድርጓል፡፡ እኔ ለወደፊቱም እንዴት እንደምንዘልቀው አይገባኝም፡፡ ፌዴሬሽኑን “ይህን የቴክኒክ ዲፓርትመንት አቋቁም!” ስትለው “ገንዘብ የለኝም!” ይልሀል፡፡ ያለ ለውጥ እየባከነና እየጠፋ ያለው ገንዘብ ግን ብዙ ነው፡፡ ለአንድ ተጫዋች ከሚከፈለው ወርሀዊ ደመወዝ ተቀራራቢ በሆነ ገንዘብ ብዙ ባለሙያዎችን መቅጠር ይቻላል፡፡ ደግሞም እኮ ከፊፋ የሚመጣ ገንዘብ አለ፤ ከልብ በሆነ ቅንነት በርከት ያሉና እውቀቱ ያላቸው ሰዎችን በመሰብሰብ በኢትዮጵያ ክልሎች እየተዘዋወሩ እንዲሰሩ በማድረግ የተሻለ ነገር ማምጣት ይቻላል፡፡

 


በ1980ዎቹ የክልል 14 ቡድኖች የሚካፈሉበት ውድድር ሲጋመስ ጋዜጦች ላይ እንደነ ስዩም አባተና ካሳሁን ተካን የመሳሰሉ ትልልቅ አሰልጣኞች በተጫዋቾች ብቃት፣ በቡድን ውህደትና በመሳሰሉት የሜዳ ላይ ጉዳዮች በሁሉም ተሳታፊ ክለቦች ግምገማን ያካሄዱ ነበር፡፡ ግምገማው በወቅቱ ለእግርኳሱ ይሰጥ የነበረው ጠቀሜታ ምን ነበር? አሁን እንዲህ አይነት ምዘና ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡ በእርግጥ በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች ባሉ የስፓርት ፕሮግራሞች ላይ በቀጥታ በሚተላለፉ የውጪ ጨዋታዎች ላይ የራሳቸውን ምልከታ ከመስጠት ባለፈ በኢትዮጵያ የተለያዩ የሊግ እርከኖች የሚገኙ ቡድኖች ላይ ግምገማ ሲደረግባቸው አይታይም ፡፡ ምክንያቱ ምን ይሆን?


★በትክክል! በጊዜው ጥሩ ቴክኒካዊ ግምገማዎች ተለምደው ነበር፡፡ ከላይ የነበሩት የወቅቱ አመራሮች የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡ በየክለቡ የታየው ቴክኒካዊ የጨዋታ ትንታኔዎችን የመስጠት ጠንካራ ፉክክርም የመጣው ከአሰልጣኞችና ከክልሎች ቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በሚገኝ ማነሳሻ ነበር፡፡ ተጫዋቾችም ለማወቅና ለመማር ጉጉ ነበሩ፡፡ <በምርጥ ቡድኖች> ውድድር ላይ ግምገማ ተደርጎ እንኳ የክለብ ከቀረ ትጠየቃለህ፡፡ እንደማስታውሰው ሰውነት ቢሻው ብሄራዊ ቡድኑን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ ይሄ ነገር በመጠኑም ቢሆን ዘልቋል፡፡ የሰውነትን ቡድን ውጪ ሆነህ ከምትተቸው ተሰብስበህ የምታየውን ችግር ብትነግረው ነው የሚጠቅመው፡፡ ስለዚህ ጋሽ ሰውነት ለፌዴሬሽኑ አሳውቆ “ባለሙያዎች በኮሚቴ መልክ ተሰባስበው እንዲያርሙኝ” በማለቱ ትልቅ ነገር አድርጓል፤ ተጠቅሞበታልም፡፡ ስምንት አባላት ሆነን በየጊዜዉ ጨዋታዎችን እንገመግማለን፤ ለሱ አንዳንድ አስተያየቶችን እንሰጠዋለን፡፡ ሰውነትም ደስ ብሎት ይቀበላል፡፡ በዚህም ጥሩ ነገር ሊታይ ቻለ፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ግምገማ ማካሄድ ማለት ማስተማር ማለት ነው፤ የሚጫወቱትን እንዲያውቁ ማድረግ፡፡ አሁን ግን እውቀት ተጠላ፤ አዛዡም ጠፋ፡፡ አሰልጣኙ ሳይሆን ተጫዋቹ የሚያዝ ነው የሚመስለኝ፡፡ እኔ አካል ብቃት ማሰራት እወዳለሁ፤ አምንበታለሁም፡፡ እንደዛፍ ቆሞ ውሎ እንደ ዛፍ የሚጋደምና በቀላሉ መነሳት የማይችል ተጫዋች የአካል ብቃት ልምምድ ስታሰራው “በቃኝ!” ብሎ ያዝሀል፡፡ ለክለብ አመራር ሄዶ “ይህ አሰልጣኝ እንደዚህ አይነት ልምምድ እያሰራን ነው፡፡” ብሎ ያወራብሀል፡፡ ለአሰልጣኞች መባረር ዋና ምክንያትም የተጫዋቾች አዛዥ- የአሰልጣኞች ታዛዥ መሆን ነው፡፡ የድሮ ተጫዋቾች እኮ አንተ ከሰጠኃቸው ስልጠና በተጨማሪ ተደብቀው በራሳቸው ልምምድ ያደርጋሉ፡፡ እኔ መድንን ሳሰለጥን ሱሉልታ ነበር ልምምድ የምናሰራው፡፡ አንዳንዴ ልምምዱን ከጨረስን በኋላ የመጓጓዣችን መኪና ሲያረፍድ የእግር መንገድ (walk) እያደረግን መኪናውን እንጠብቀዋለን፡፡ የአሰልጣኞች ቡድን አባላቶቹ ቀስ እያልን ከኋላ ከኋላ ስንከተላቸው እየራቁ ይሄዱና ጠመዝማዛው ቦታ ሲደርሱ ሩጫ ይጀምራሉ፡፡ አስቡት እንግዲህ ያን ሁሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላም ሳይደክማቸው በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ ሮጠው እኛ በመኪና እየመጣን ሰሜን ሆቴል ጋር እናገኛቸዋለን፡፡ የአሁኑን ጊዜ ተጫዋቾች የስራ ፍላጎት ግን ብሩ አበላሸው፡፡ የመማርና የማወቅ ፍላጎቱ የዛን ጊዜው ይበልጣል፡፡ በእርግጥ የአሁኖቹን ሁሉ መጥፎ አትልም፤ ቢሆንም አንዱ ሌላውን ይጎትታል፡፡ የክለብ ልምምዶች ላይ ብትመለከቱ ጥሩ የመስራት ፍላጎት ያለውን ተጫዋች ሌላኛው ” ቀስ በል እስቲ! ረጋ እያልክ” የሚሉት ተጫዋቾች ስለሚኖሩ በመሸማቀቅ ጥረቱን ይቀንሳል፡፡ ወጣቶቹ በተለይ ትልልቆቹን ይፈራሉ፡፡ አንዳንዶቹም ሲያሻቸው “አመመኝ!” ብለው ይሄዳሉ፤ ገንዘባቸውን ቀድመው ወስደው ሊሆን ስለሚችልም ምንም አይመስላቸውም፡፡ ነገ ውጤት ሲጠፋ ግን የሚባረረው አሰልጣኙ እንጂ ተጫዋቾች አይደሉም፡፡ ተጫዋቾቻችን ከማንም በላይ የውጪ ኳስ የመመልከት ሰፊ እድል አላቸው፡፡ ሆኖም ግን የሆነች ነገር እንኳ ሲኮርጁ አይታዩም፡፡ ሁኔታዎች በተሻለ ተመቻችተዋል፤ በአካል ብቃት በኩል ግን ብዙም እየተሰራ አይደለም፡፡ ምንም ባልነበረ ጊዜ የነበረው ተነሳሽነት አሁን ቢኖር ውጤት የማይመጣበት ምክንያት አይታየኝም፡፡


 

የታዳጊ ቡድኖችን ከመያዝና አካዳሚ ከመክፈትም ባለፈ በኢትዮጵያ እግርኳስ በሲስተም ደረጃ ቀጣይነት ያለው ወጣቶችን የማብቃት ስራዎች እንዲሰሩ ምን መደረግ አለበት ትላለህ?


★ ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት በወጣቶች ላይ ብቻ መሰራት በቂ አይደለም፡፡ በተለይ አስተዳደሩን ከሚመለከተው ውጪ ታዳጊዎችን፣ ወጣቶችን፣ ዋናውን እና በተመሳሳይም የሴቶቹን ቡድኖች በኃላፊነት የሚከታተል፣ ደረጃውን የጠበቀ <ስታንዳርድ> የስልጠና አይነቶችን የሚያወጣ አንድ ትልቅ ቴክኒካል ዲፓርትመንት መቋቋም አለበት፡፡ ብሔራዊ ቡድኖቻችንን በተተኪነት የሚያገለግሉ ከአንድ በላይ የሆኑ ቡድኖችን ማዘጋጀትም ስታንዳርድ በሆነ ስልጠና ለመጡት ተጫዋቾች ቦታ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ከአቶ መንግስቱ ጋርም በየክልሎቹ ተተኪ ቡድኖችን ማዘጋጀት ጀምረን ነበር፡፡ በቀላሉ ሰዎች ይመደቡና የተዘጋጁትን ቡድኖች ክትትል ያደርጉባቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ከብዙ ተተኪ ቡድኖች የምናወጣው አንድ ትልቅ፣ ጥራት ያለውና ጠንካራ ቡድን ይሆናል፡፡ አሁን እኮ በሶስት የቴክኒክ ሰዎች የሚሰራው የይስሙላ ስራ ነው፡፡ በቅርቡ በአዲስ አበባ እግርኳስ ማህበር ውስጥ አስራት ኃይሌ፣ ዮሃንስ ሳህሌ፣ እኔና ሌሎች ወደ ስምንት የምንጠጋ ሰዎች በምርጫው ጉዳይ ተሰብስበን “ጥናት እናድርግ!” ሲባል መጀመሪያ ያቀረብኩት ሐሳብ አሁን እየነገርኳችሁ ያለሁትን ጉዳይ ነው፡፡ ቴክኒካዊ ጉዳይ በድርጅት ወይም በተቋም ደረጃ ነው መመራት የሚገባው፡፡ እስከ ሃያ የሚደርሱ ባለሙያዎችን የያዘ እንጂ ሁለት አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዴት የአንድን አገር እግርኳስ ቴክኒካዊ ጉዳይ ይመራል? ማዕከላዊው ቴክኒካል ክፍል ሁሉንም ክልሎች በዚህ ዘርፍ እንዲመራና እንዲቆጣጠር በማድረግ፣ ከውጪ አገሮች ጋር ግንኙነት በመመስረት የተለያዩ አሰራሮችን በመውሰድ ልዩነት መፍጠርና ውጤቱን ማየት ነው፡፡ ሁሌም በደንብ ያልተዘጋጀ ቡድን ይዞ ግጥሚያዎችን እያደረጉና በሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲሁ በአዲስ ምርጫ ያልተግባቡ፣ በተከታታይነት ለረጅም ጊዜ አብሮ ያልሰሩና ያልተዋሀዱ ተጫዋቾች የተሰበሰቡበት ሌላ ቡድን በማቋቋም የመጣው ውጤት ታይቷል፡፡ በዚህ መልኩ Uniform የሆነ ስራ የሚሰራበት መንገድ ቢመቻች ጥሩ ይሆናል፡፡ እንዳቅማችን ዋናውን የሚተኩ ሁለት-ሶስት ቡድኖች እንዲኖሩን እንስራ፡፡