” እቅዶቼን በደፈናው ሳይሆን በቁጥር ለክቼ ነው ለምርጫ ያቀረብኩት” አቶ ተስፋይ ካህሳይ

አቶ ተስፋይ ካህሳይ ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ከቀረቡት አራት እጩዎች መካከል አንዱ ናቸው። አቶ ተስፋይ በምርጫው ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝደንትነት ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመወዳር የፈለጉበት ምክንያት ምንድነው?  አዲስ ተወዳዳሪ እንደመሆንዎ መጠን? 

በእግርኳሱ ውስጥ ረዥም ጊዜ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ስሰራ ቆይቻለው። በቴሌቭዥን በሬዲዮ በጋዜጣ በተለያዩ መንገዶች ፌዴሬሽን ውስጥ ባልገባም ለእግርኳሱ በሚጠቅሙም ሆነ መሻሻል በሚገባቸው ነገሮች ላይ እሳተፍ ፣ አስተያየት እሰጥ ነበር። በክለቦች እና በክፍለ ከተሞችም የተለያዩ ከእግርኳሱ ጋር የተገናኙ ስራዎችን ሰርቻለው። ይህ ማለት እግርኳሱ ውስጥ አለው ማለት ነው። ያም ቢሆን ሁሌም የእግርኳሳችን ችግር እያመመን ነው የኖርነው። ታዲያ ዳር ላይ ሆኖ መተቸቱ ትርጉም የለውም፤ አንድ ስራ ሲሰራ ሁሌ ከአንተ የማይሻል ሰው ስራውን ሲሰራ እና ምንም ለውጥ ሳይመጣ ሲቀር ለምን አልገባም አልሞክርም ትላለህ። ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ በጣም የሚገርም ነው። ከኢትዮዽያ አንፃር ስታየው ይህ ፌዴሬሽን ደካማ ነው። ደካማ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደ ፊትም ምንም ተስፋ አታይበትም። ስለዚህ ለምን እኔ ገብቼ ያለኝን አቅም ወደ ስራ አልቀይረውም በሚል ነው ለመወዳደር ያሰብኩት። 

አሸንፈው ፕሬዝደንት ሆኑ እንበልና ከዚህ ቀደም በነበረው የምርጫ ሂደት ውስጥ ብዙዎች እቅድ አለን ፣ ለውጥ በእግርኳሱ እናመጣለን ፣ አሁን ካለው ደካማ ፌዴሬሽን የተሻለ ስራ እንሰራለን ብለው ይገቡና ምንም አይነት ለውጥ ሲያመጡ አይስተዋልም። እርስዎ በዚህ ረገድ እግርኳሱን ወደተሻለ ነገር ለማምጣት ፈታኝ የሆነውን ስራ ለመስራት ምን ያህል ተዘጋጅተዋል? 

በመጀመርያ ከሌሎች ተወዳዳሪዎች የእኔ ልዩነት ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች ከ1996 ጀምሮ በእግርኳሱ ውስጥ ብዙ ችግር እንዳለ እናገራለው። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ ጊዚያት በነበሩት ፕሬዝዳንቶች ፊት ቀርቤ ለእግርኳሱ ይበጃል ያልኩትን መፍትሄ ሰጥቻለው። የኢትዮዽያ እግርኳስ እየመጣበት ያለው መስመር ትክክል እንዳልሆነ ብዙ ጊዜ ተናግሬያለው። ስለዚህ ከሌሎቹ የሚለየኝ እኔ አሁን ለመመረጥ ብዬ አይደለም እያወራሁ ያለሁት ድሮም ዳርም ሆኜ አስተያየት እሰጣለው እናገራለው። ተናግረህ ተናግረህ የሚሰማ ስታጣ አንተ ራስህ መግባት አለብህ። ሌላው እኔ እነዚህን እሰራቸዋለው ያልኩትን አስር እቅዶችን በቁጥር ለክቼ አስቀምጬያቸዋለው። ስለዚህ በእነዚህ አራት አመታት ውስጥ ቆጥሬ በሰጠዋቸው እቅዶች መሠረት ይቆጣጠሩኛል ፣ ይገመግሙኛል ማለት ነው። እንደዚሁ በደፈናው ለውጥ መኖር አለበት እያልኩ አይደለም እያልኩ ያለሁት፤ ቆጥሬ ነው እየሰጠው ያለሁት።

የኢትዮዽያ ምርጫ በሴራ ንድፈ ሀሳብ የተሞላ ነው። በዚህ ምርጫ ከባቢ ውስጥ ሆኖ ጤናማ በሆነ መንገድ ለእግርኳሱ የሚበጅ ሰው ይመረጣል ብለው ያስባሉ? እኔም የዚህ ችግር ሰለባ ሆኜ እሸነፋለሁ ብለው ይሰጋሉ?

እንግዲህ ይህ ነው ችግሩ። ሰዎች እግርኳስን የሚወዱ ከሆነ የእግርኳሱ ችግር የሚሰማቸው ከሆነ የእግርኳሱ ህመም የሚያማቸው ከሆነ ፣ እግርኳሱ ለውጥ እንዲያመጣ የሚፈለግ ከሆነ ፣ ለትውልዱ የተሻለ ነገር አስቀምጦ ለማለፍ የሚፈልጉ ከሆነ ህሊናቸውን ተጠቅመው የመሰላቸውን ሰው መምረጥ አለባቸው ።  ጣልቃ ገብነት አለ በየአካባቢው ባለሀብቶች ፣ የመንግስት ባለስልጣኖች…የመሳሰሉት ጣልቃ ገብነት ያደርጋሉ። እናንተ ሚዲያዎችም የምታውቁት ነገር ነው። ይህ ነገር በጣም ያስፈራኛል፤ የሚያስፈራኝ የእኔ መመረጥ አለመመረጥ አይደለም ግን የዛሬ አራት አመትም እዚሁ ቦታ ላይ ምንም ለእግርኳሱ ሳንሰራ እንዳንገናኝ ነው የምፈራው። ምክንያቱም የዛሬ አራት ዓመት አሁን ካለንበት ቦታ በጥቂቱም ቢሆን ትንሽ ከፍ ብለን መታየት አለብን። ካልሆነ ግን ዞሮ ዞሮ የምንጎዳው እግርኳሱ እና ትውልዱ ነው።   

ጤናማ ምርጫ እንዲካሄድ ለተሳታፊዎች ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ደጋግሜ እንደምለው ሁሌም ሁላችንም ስፖርቱን እንደወዋለን ካልን ከአንገት በላይ መሆን የለበትም። ገንዘብ ስላገኙ ወይም የመንግስት ባለ ስልጣናት ይሄን አድርጉ ብሎ ስላዘዛቸው የሚያደርጉ ከሆነ አስቸጋሪ ነው። ድምፅ የሚሰጠው በስውር ስለሆነ የሚሰጡት ድምፅ ለማን እንደሰጡ የማይታወቅ ማንም የማያያቸው ስለሆነ የሚያያቸው ህሊናቸው እና ፈጣሪ ብቻ በመሆኑ ከልባቸው በእውነት ለሚያምኑት እግርኳሱን ለሚጠቅም ሰው ድምፃቸውን ቢሰጡ ደስ ይለኛል።