ዛሬ በተደረገው የብሄራዊ ሊግ የ3ኛ ደረጃ ጨዋታ ሀላባ ከነማ ጅማ አባ ቡናን በመለያ ምቶች አሸንፎ 3ና ደረጃን አግኝቷል፡፡
መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን በጨዋታው ጅማ አባ ቡና ተገቢ ያልሆኑ ተጫዋቾች አሰልፈዋል በሚል ሀላባ ከነማዎች ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ጅማዎች በድሬዳዋ ከነማው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተ ተጫዋቾች አሰልፈዋል በሚል ነው ሀላባ ከነማዎች ቅሬታ ያቀረቡት፡፡
በመለያ ምቶቹ ሀላባ ከነማ ከ5 ምቶች አራቱን ሲያስቆጥሩ ጅማ አባ ቡናዎች ከ4 ምቶች ሁለቱን አስቆጥረው 2 ስተዋል፡፡ በድምር ውጤትም ሀላባ ከነማዎች 4-2 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የሀላባ ከነማን የመጨረሻ የመለያ ምት መትቶ ወደ ግብነት የቀየረውና ቡድኑን ለአሸናፊነት ያበቃው በውድድሩ መልካም አቋም ያሳየውና በምድብ ጨዋታዎች አንድ ግብ ያስቆጠረው ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ነው፡፡
ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ የሀላባ ቡድን አባላት ባለፈው አርብ በመኪና አደጋ 4 የሀላባ ከነማ ደጋፊዎች ህይወት ማለፉን እና በርካቶች መጎዳታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ የሀዘን ስሜት እና ለቅሶ ሜዳውን ለቀዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን በሃዘን ስሜት ውስጥ ሆነው የሰጡት የሃላባ ከነማው አሰልጣኝ ተመስገን ከጨዋታው ይልቅ አሳዛኙን ክስተትና አላግባብ ስለተሰለፉት ተጫዋቾች ማንሳት መርጠዋል፡፡ ‹‹ ጨዋታውን ማድረግ አልፈለግንም ነበር፡፡ ለደጋፊዎቻችን ክብር ስንል ነው ጨዋታውን ያደረግነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡ ጅማ አባ ቡናዎች ባለፈው ጨዋታ ቀይ ካርድ ያዩ ተጫዋቾችን ያሰለፈበት አግባብ አልገባንም፡፡ ትክክለኛ የሆነ ውሳኔ አይደለም፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ሀላባ ከነማ በ3ኝነት ውድድሩን ሲያጠናቅቅ ዛሬ በ9፡00 የፍፃሜው ፍልሚያ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መግባታቸውን ባረጋገጡት ሆሳእና ከነማ እና ድሬዳዋ ከነማ መካከል ይደረጋል፡፡ የጨዋታውን ዋና ዋና ሁነቶች በፌስቡክ ገፃችን መከታተል ይችላሉ፡፡