የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ውሎ

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በዕለተ ማክሰኞ ወሳኝ የጥሎ ማለፍ ዙር ጨዋታዎችን አስተናግዶ ወደ አንደኛ ሊግ የተቀላቀሉ 8 ቡድኖች ተለይተዋል። 

ሀዋሳ ከተማ ስታድየም (ሰው ሰራሽ ሜዳ)

(ቴዎድሮስ ታከለ)

3:00 ላይ በጀመረው የፋሲል ከተማ B እና የኮልፌ ቀራኒዮ ጨዋታ በኮልፌ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ የሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች መካከል በተስተዋለበት ጨወታ ሁለቱም የተሳኩ እና ለግብ የቀረቡ የግብ ዕድሎችን ማግኘትም ችለዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ብርሀኑ በጋሻው ኮልፌን ቀዳሚ አድርጎ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ 66ኛው ደቂቃ የፋሲሉ ተከላካይ ዳንኤል ፍፁም ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት  አምበሉ ፈቱ አብደላ መቶ የፋሲል ግብ ጠባቂ ዳንኤል ስጦታው ቢመልስበትም ዳግም እግሩ ላይ ኳሷ የደረሰችሁ ፈቱ ግብ አስቆጥሮ የኮልፌን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል። 81ኛው ደቂቃ ላይ  የፋሲል ከነማው አማካይ ዮናስ ከተማ ከዳኛው ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የኮልፌው ክንዱ ባየልኝ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ዮናስ ደሳለኝ ለፋሲል ብቸኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በኮልፌ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቆ ኮልፌ ቀራኒዮ ወደ አንደኛ ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ የሚገኙ አስሩም የክፍለ ከተማ ቡድኖች በከፍተኛ ሊጉ እና አንደኛ ሊጉ የሚወዳደሩ መሆን ችለዋል።

5:00 ሰዓት ላይ በቀጠለው ጨዋታ አዲስ አበባ ውሀ እና ፍሳሽ ሀደሮ ከተማን 1-0  አሸንፏል። እጅግ አሰልቺ የሜዳ ላይ እንቆስቃሴን በተመለከትንበት ጨዋታ ሀደሮ ከተማ በአጥቂው አዲስአለም ሀምቢሶ በርካታ አጋጣሚን መጠቀም አልቻለም። በሁለተኛው አጋማሽ 77ኛው ደቂቃ  አስናቀ ፋንታሁን የሀደሮ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ግሩም ግብ አስቆጥሮ አአ ውሀ እና ፍሳሽ ወደ አንደኛ ሊጉ መግባታቸውን ያረጋገጠች ድል አስመዝግበዋል።

7:30 ላይ አረካ ከተማን ከ ካልዲስ ኮፊ ያገናኘው ጨዋታ በአረካ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴ በተመለከትንበት ጨዋታ አረካ ከተማ በማጥቃቱ በኩል የተወጣለት ቡድን ነበር። 66ኛው ደቂቃ ላይ የካልዲስ ኮፊ ተከላካይ ፀጋዬ ወልዴ በራሱ የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ተስፋዬ ወደ ግብነት    ለውጧት አረካ ከተማ ወደ አንደኛ ሊግ ማደጉን ያረጋገጠበትን ጎል አስቆጥሯል። በዚህ ጨዋታ 90ኛው ደቂቃ ላይ የካልዲስ ኮፊን ተጫዋቾች በመማታቱ የአረካ አጥቂ ሙሉቀን አማኑኤል በቀይ ካርድ ተወግዷል።

ቡሬ ከተማን ከቄራ አንበሳ ያገናኘው የ9:30 ጨዋታ መደበኛው ክፍለ ጊዘዜ ያለ ጎል ተጠናቆ ቄራ በመለያ ምቶች አሸናፊ ሆኗል። የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ በሁለቱም በኩል የጠራ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ መደበኛው ዘጠና ተጠናቆ በተሰጡ የመለያ ምቶት ቄራ 3-2 አሸንፏል። ለቄራ አንበሶች ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂ ቴዲ አበራ ሶስት መለያ ምት አድኖ ወደ አንደኛ ሊግ እንዲገባ የረዳ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ግብርና ኮሌጅ ሜዳ

(አብርሀም ገብረማርያም)

03:00 ላይ አሰላ ከተማን ከሲልቫ ውሀ ያገናኘው ጨዋታ በአሰላ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በጨዋታው የተሻለ የተንቀሳቀሱት አሰላዎች በመጀመርያው አጋማሽ ሙራድ ብርሀኑ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ወሳኝ ድል ማስመዝገብ ችለዋል።

ቀጥሎ የተካሄደው የዶዶላ ከተማ እና አንገጫ ከተማ ጨዋታ ከእለቱ ጨዋታዎች የተሻለ ፉክክር የታየበት ሆኖ በመለያ ምቶች በአንገጫ አሸናፊነት ተጠናቋል። በ7ኛው ደቂቃ ከራሳቸው የግብ ክልል ጀምሮ በማራኪ ቅብብል ወደ ዶዶላ ሳጥን በመግባት ዳንዔል ዳና ባስቆጠረው ጎል አንገጫዎች ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋዋታው የገቡት ዶዶላዎች በ24ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ሮቤል ዳንዔል በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው በኃይሉ ከበደ ከመስመር የተሻገለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ዶዶላን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር በ82ኛው ደቂቃ ዳንዔል ዳና ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ አንገጫን አቸ በማድረግ ወደ መለያ ምቶች እንዲያመሩ ረድቷል። አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶችም አንገጫ 3-1 በማሸነፍ ወደ አንደኛ ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል።

በግብርና ኮሌጅ ሜዳ የእለቱ ሶስተኛ መርሐ ግብር በዳንግላ ከተማ እና አንሌሞ ወረዳ መካከል የተደረገው ነው። ጨዋታው ሳቢ ያልነበረ ይልቁንም የዳንግላ ደጋፊዎች ድጋፍ አሰጣጥ እና በመጨረሻ ያሳዩት ምግባር ትኩረት የሚስብ ነበር። ጥቂት የግብ አጋጣሚዎች በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ አንሌሞዎች በሰለሞን ዴታሞ የ64ኛ ደቂቃ ጎል ቀዳሚ ቢሆኑም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ቸርነት ልየው ዳንግላን አቻ አድርጎ መደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 ተጠናቋል። በመለያ ምቶችም ዳንግላ ከተማ አሸንፎ ወደ አንደኛ ሊጉ አምርቷል።

የዳንግላ ደጋፊዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሜዳው ዙርያ የተጣሉ የውሀ መያዣ ፕላስቲኮች እና ቆሻሻ በማፅዳት መልካም ተግባር ፈፅመዋል። (ፎቶ ከላይ)

10:00 ላይ ቴክኖ ሞባይል ከገንፈል ውቅሮ ያደረጉት ጨዋታ እንደቀደሙት ጨዋታዎች ሁሉ መደበኛው ክፍለ ጊዜ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ሚኬሌ ተክሌ በ27ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከርቀት ባስቆጠረው ጎል ቴክኖ ሞባይሎች ለረጅም ደቂቃዎች ከመምራታቸው በተጨማሪ በርካታ ለማምከን የሚከብዱ እድሎችን ሲያመክኑ ተስተውሏል። በ83ኛው ደቂቃም ቴዎድሮስ ሓሸ ለገንፈል ውቅሮ ያስቆጠረው የአቻነት ጎል ዋጋ ሊያስከፍላቸው ተቃርቦ ነበር። መደበኛው ክፍለ ጊዜ 1-1 በመጠናቀቁ በተሰጡት የመለያ ምቶች ቴክኖ ሞባይል 3-2 አሸንፎ ወደ አንደኛ ሊጉ መቀላቀል ችሏል።