ደደቢት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ደብዳቤ ላከ

ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ባለፈው ወር መቀመጫውን ወደ መቐለ ከተማ ማዞሩን እና በተጨዋቾች የዝውውር ላይ አዲስ ደንብ በመከተል ለአንድ ተጨዋች ከ25 ሺ ብር በላይ ላለመክፈል መወሰኑንና ዘመናዊ የእግር ኳስ አደረጃጀትን ወደ ክለቡ ለማምጣት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን መግለፁ ይታወሳል።

ክለቡ ይህንን ውሳኔ ከወሰነ በኋላ በርከት ያሉ ተጨዋቾች ክለቡን ለቀው ወደ ሌሎች ክለቦች እያመሩ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን አዳዲስ ተጨዋቾችን ከከፍተኛው ሊግ ክለቦች እና ከተስፋው ቡድኑ በመቀላቀል የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለመጀመር የፕሪምየር ሊጉን መጀመርያ ቀን እስኪገለፅ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።

ክለቡ ትላንት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በላከው ደብዳቤ የ2011 የፕሪምየር ሊጉ  ውድድር የሚጀምርበትን ጊዜ ፌደሬሽኑ እንዲገልፅለት ጠይቋል። “የፕሪምየር ሊጉ ውድድር የሚጀምርበት ጊዜ ቀደም ቡሎ ባለመገለፁ የምናደርገው የዝግጅት ስራ በግምት እና ባልተጠና መንገድ ነው። ስለዚህ ሊጉ የሚጀምርበት ቀን ቀደም ብሎ ይነገረን።” ያለው ክለቡ አላስፈላጊ የጊዜ እና የገንዘብ ኪሳራ ክለቦች እንዳይደርስባቸው ይደረግ ብሏል።

ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ የሊጉ መጀመርያ ወቅት እንዲገለፅ ጠይቆ የነበረው ደደቢት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፕሮግራም አወጣጥ ላይ ጥያቄ በማንሳት ከ2010 የኢትዮጵያ ዋንጫ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል።