ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ የ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ቻምፒዮን ሆኗል

የ2010 የኢትጵጽያ ከፍተኛ ሊግ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ ሲከናወን ቆይቶ ዛሬ አዳማ ላይ አሸናፊውን አግኝቷል። በምድብ ሀ ባህር ዳር ከተማ፣ በምድብ ለ ደግሞ ደቡብ ፖሊስ በአንደኝነት ምድባቸውን በማጠናቀቃቸው ለፍፃሜው የደረሱ ሲሆን ደቡብ ፖሊሶች 1-0 አሸንፈው የዋንጫው ባለቤት ሆነዋል።                
በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዋና እና ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንዲሁም የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ እና ሌሎች ግለሰቦች ለተጨዋቾቹ ሰላምታ በመስጠት ነው ጨዋታው የተጀመረው።

የመጀመሪያውን አጋማሽ የበላይነት የወሰደው ደቡብ ፖሊስ ተጭኖ የተጫወተ ቢሆንም በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ተዳክሞ ታይቷል። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ምንም አይነት የግብ አጋጣሚዎች ያልፈጠሩ ሲሆን ይልቁንም ኳስን በማንሸራሸር ለመጫወጥ ሲጥሩ ታይቷል። በ23ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በማድረግ ለቡድኑ የግብ እድል ለመፍጠር ችሏል።

በመስመር አጨዋወት የሚታወቁት ባህር ዳር ከተማዋች ዛሬም የሜዳውን መስመር ለመጠቀም ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መሰንዘራቸው ቢታይም ስኬታማ ግን አልነበሩም። ደቡብ ፖሊሶችም ይዘውት የገቡት አጨዋወት ተመሳሳይ በመሆኑ በመስመር ላይ ከፍተኛ ፍትጊያዎች እንዲታዩ አድርጎታል። በ27ኛው ደቂቃ ወጣቱ አጥቂ ብሩክ ኤልያስ በግራ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብነት ቀየረው ሲባል የባህር ዳር ግብ ጠባቂ ምንተስኖር አሎ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ያዳነበት ኳስ በደቡብ ፖሊሶች በኩል የመጀመሪያ ለግብ የቀረበች አጋጣሚ ነበረች። ከሶስት ደቂቃዎች በኃላም ዱላ ሙላቱ በቀኝ መስመር ይዞት የገባውን ኳስ አክርሮ የመታው ሲሆን ምንተስኖት አድኖበታል። 

ቀስ በቀስ ኳስ በመቆጣጠር ተሽለው የታዩት ደቡብ ፖሊሶች በመሀል ሜዳው በቁጥር በዝተው የባህር ዳር ከተማን የመሀል ክፍል በልጠው ለመጫወት ጥረዋል። ከኳስ ቁጥጥሩ ባሻገር ባህርዳሮች ኳስን ወደ መስመር  እንዳያስወጡ ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን በተቃራኒው እነሱ ኳስ ሲያገኙ ወደ መስመር እያወጡ በተደጋጋሚ የባህርዳርን ተከላካዮች ላይ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ታይተዋል። በዚሁ አጨዋወት ተደጋጋሚ ጥረቶችን ያደረጉት ፖሊሶች በ35ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አግኝቷል። ዱላ ሙላቱ ለኬኒያዊው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ያቀበለውን ኳስ ኤሪክ ወደ ግብነት በመለወጥ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ ለመጫን የሞከሩት ባህርዳሮች በ43ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ግርማ ዲሳሳ ያሻገረውን ኳስ ፍቃዱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። 

ከዕረፍት መልስ ባህርዳሮች የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመንጠቅ እና በጊዜ ወደ አቻነት ለመመለስ ሲጥሩ የታየ ሲሆን የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ48ኛው ደቂቃ በሙሉቀን ታሪኩ አድርገው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። አሁንም ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት የጣናው ሞገዶች በተለይ ዳንኤል ኃይሉ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ አክርሮ ከሚመታቸው ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ታይቷል። ፍቃዱ ወርቁን በወሰኑ ዓሊ በመቀየር ሌላ የማጥቂያ ሃይል የጨመሩት አሰልጣኝ ጳውሎስ እቅዳቸው ፍሬ ማፍራት ግን ተስኖታል።

ያገኙትን እድል አሳልፈው ላለመስጠት የጣሩት ደቡብ ፖሊሶች በ70ኛው ደቂቃ ዮሀንስ ዳንኤል በሁለት ቢጫ ያጡ ሲሆን ከቀዩ በኃላ ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲጥሩ ታይቷል። ለዚህም ማሳያ ዱላ ሙላቱ በ72ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ያለቀለት እድል በማግኘት ከግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ጋር ተገናኝቶ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሲል ሙሉቀን ታሪኩ አክርሮ መትቶ የግቡ የቀኝ ቋሚ የመለሰበት ሙከራ አቻ የሚሆኑበትን እና ዳግም ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን እድል ነበር። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት በደቡብ ፖሊስ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ክቡር ትሪቡን አካባቢ የደጋፊዋች ግጭት ቢከሰትም የአዳማ ከተማ ልዩ ሀይል ቶሎ እርምጃ በመውሰዱ ግጭቱ ሳይስፋፋ ቀርቷል።

በመጨረሻም የሽልማት ፕሮግራም የተከናወነ ሲሆን ሁለቱም ተጋጣሚዎች የምድባቸው የበላይ በመሆናቸው የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸው። ቡራዩ ከተማ ከምድብ ሀ፣ ሀላባ ከተማ ደግሞ የምድብ ለ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ተሸልመዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ግርማ ታደሰ – ደቡብ ፖሊስ

” በመጀመሪያው አጋማሽ 15 ያህል ደቂቃዎችን የተጋጣሚያችን ጨዋታ ቅርፅ ለማጥናት የሞከርን ሲሆን ከዛም ወደምንፈልገው መንገድ መቀየር ችለናል። ከዕረፍት መልስ ተጫዋቾቼ ለዋንጫው በመጓጓታቸው ምክንያት ወደኋላ አፈግፍገው ተጨውተዋል። የአንድ ተጨዋች በቀይ ካርድ መውጣትም የበለጠ ተፅእኖ ፈጥሮብናል።

” የዛሬው ድል ለኔ በጣም ልዩ ነው። በ2007 ሀድያ ሆሳዕናን ይዤ ይህን ዋንጫውን አጥቸው ነበር፤ ዘንድሮ አሳክቻለው። በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ እግዜአብሔር ይመስገን።

” ለሚዲያዋች በተለይ ለሶከር ኢትዮጽያ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ለደጋፊዋቻችን እና ለአስተዳደሩ እንኳን ደስ ያለን እላለሁ። ”

መኮንን ገላነህ – ባህር ዳር ከተማ (ምክትል አሰልጣኝ)

” በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ተበልጠናል። ከዕረፍት መልስ ደግሞ እኛ የተሻልን ነበርን። እድል ከኛ ጋር አልነበረም፤ ደጋፊዎቻችንን ይህን ዋንጫ አምጥተን ማስደስት እንፈልግ ነበር።”