አዳማ ከተማ አዲስ ምክትል አሰልጣኝ ቀጥሯል

አዳማ ከተማ ከአንድ ወር በፊት ሲሳይ አብርሀምን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ በቀጠረበት ወቅት ዳዊት ታደሰን በምክትልነት መቅጠሩን ማስታወቁ የሚታወስ ነው። ሆኖም አሰልጣኝ ዳዊት በውል ጉዳይ ላይ ከስምምነት ባለመድረሳቸው ክለቡ ሌላ ምክትል አሰልጣኝ ሲፈልግ ቆይቶ ደጉ ዱባለን መቅጠሩን አስታውቋል። 

በመተሐራ ስኳር፣ ኢትኮ፣ ፐልፕ እና ወረቀት፣ ወንጂ ስኳር፣ አየር መንገድ፣ ጉና ንግድ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና ሐረር ቢራ በተጫዋችነት ያሳለፉት አሰልጣኝ ደጉ ከ2001 ጀምሮ በወጣት ቡድን አሰልጣኝነት ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በዋናው ቡድን አሰልጣኝነት ሲሰሩ ቆይተዋል። አሰልጣኙ በአዳማ ከተማ ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዓመታት የሲሳይ አብርሀም ረዳት ሆነው እንደሚሰሩ ለማወቅ ተችሏል። 

በተያያዘ ዜና ዝግጅታቸውን ካልጀመሩ ክለቦች መካከል አንዱ የነበረው አዳማ ከተማ ነገ መስከረም 3 በባቱ (ዝዋይ) ከተማ የዝግጅት ጊዜውን የሚጀምር ሲሆን ከ25 እስከ 30 ቀናትን በከተማው ቆይታ ያደርጋሉ ተብሏል።