ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሁለት – ክፍል ሁለት)

በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። ባለፈው ሳምንት የምዕራፍ ሁለትን ማስነበብ መጀመራችን የሚታወስ ሲሆን በዚህ ሳምንት ደግሞ የምዕራፉን ቀሪ ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡፡፡ መልካም ንባብ!


|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ ምዕራፍ ምዕራፍ ሁለት – ክፍል አንድ

ምዕራፍ ሁለት

ክፍል ሁለት: የጂሚ ሆጋን እና ሑጎ ሚይዝል ታላቅ አበርክቶት

የስኮትላንዳውያኑ አጨዋወት ስልት ቀማሪ እና ታላቁ መምህር የዘር ሐረጉ ከአየርላንድ የሚመዘዘው እንግሊዛዊው ጂሚ ሆጋን ነበር፡፡ ከአክራሪ የሮማን ካቶሊክ እምነት ተከታይ ቤተሰቦች በበርንሌይ ከተማ ተወልዶ ያደገው ሆጋን በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ እያለ ወደ መንፈሳዊው ህይወት በመሳብ በቅስና ግልጋሎት ስለመስጠት ሲያሰላስል አድጓል፡፡ በመጨረሻ ግን ፊቱን ወደ እግርኳስ በማዞር በአለም ከታዩ ተጽዕኖ ፈጣሪ ምርጥ አሰልጣኞች መካከል አንዱ ሊሆን በቃ፡፡ በ1950ዎቹ የመጀመሪያ አመታት የታላቋ ሃንጋሪ አሰልጣኝ ጉስታቭ ሴቤዝ ሲመሰክርም ” እግርኳስን ጂሚ ሆጋን እንዳስተማረን ተጫወትን፡፡ የእኛ እግር ኳስ ታሪክ ሲዘከር የእርሱ ስም በወርቃማ ሆሄያት መጻፍ አለበት፡፡” ብሎለታል፡፡

አባት ልጃቸው ሲያድግ የሒሳብ ባለሙያ እንዲሆን የነበራቸውን ፍላጎት ጥሶ በአስራ ስድስት ዓመት እድሜው የላንክሻየሩን ቡድን ኔልሰን በመቀላቀል እርሱ እንደሚገልጸው “ትጉህና ጠንካራ ወደ ሆነ የቀኝ መስመር አማካይነት” አድጎ ወደ ሮችዴል በመቀጠልም ወደ በርንሌይ አመራ፡፡ ሆጋን በሁሉም የህይወት መንገዶቹ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን የተቋቋመ፣ የተሻለ ደመወዝ ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችን ያየ፣ ዘወትር ራሱን ለማሻሻል በተለየና ከፍተኛ በሆነ ዝግጁነት የሚተጋ ሰው ነበር፡፡ በመንደሩ የሚያሳየውን ቁጥብ፣ ጥንቁቅና ጥብቅ ስነ ስርዓታዊ ባህሪውን በማስመልከት የቡድን አጋሮቹ በቅጽል ስም ሲጠሩትም “ቄሱ” ይሉታል፡፡ በአንድ ወቅት ላይ ሆጋንና አባቱ አንድ ኋላ ቀር የልምምድ ብስክሌት አበጁ፡፡ በዚህችው ብስክሌት ከአሮጌ እንጨት የተሰራ ማረፊያ ላይ ጉብ ብሎ በቀን ሰላሳ ማይሎችን በመጋለብ ፍጥነቱን ከማሻሻሉ ባለፈ ቅልጥሙ አካባቢ የሚገኙ ጡንቻዎቹን እያፈረጠመና እያጠነከረ ሄደ፡፡

ጥረት አልባ የበላይነት ስሜት ቀደምት < አማተር> ስፖርተኞችን ብቻ የሚወክል ቢመስልም < ፕሮፌሽናል> ወደ ሆነው አለምም ተዛምቶ ታይቷል፡፡ በቀደመው የእግርኳስ ዘመን መደበኛ ልምምድ ማድረግ እምብዛም ትኩረት አይቸረውም፡፡ እንዲያውም የተናቀ ተግባር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ተጫዋቾች በፍጥነት እንዲሮጡ ከማድረግ ባለፈ ምናልባት መስፈንጠርን በተመለከተ ይለማመዱ ካልሆነ በስተቀር ከኳስ ጋር የተገናኙ ስራዎች አይረቤና ጭራሹኑ ጎጂ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር፡፡ ለምሳሌ የ1904ን የቶተንሐም የልምምድ መርኃ ግብር በናሙናነት ብንወስድ በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ከኳስ ጋር የተገናኙ ልምምዶች እንዳካተተ ያሳያል፡፡ ይህም የክለቡ አሰልጣኞች በጊዜው ከሌሎች በተሻለ የኳስ ተኮር ስልጠናዎች በቂ ግንዛቤ ስለነበራቸው የተገኘ ነው፡፡ እንዲያውም እነዚህን ልምምዶች አስመልክቶ “በሳምንቱ ቀናት ውስጥ ባሉት የልምምድ መርኃግብሮች ተጫዋቾች ኳስ እንዲያገኙ አድርግ፤ ምክንያትህን አብራራላቸው፤ ከዚያም በቀጣዩ ቅዳሜ ተጫዋቾች ለኳሱ ከፍተኛ የመራብ ፍላጎት አያሳዩህም፡፡” የሚለው ደካማ የስልጠና ብሂል ቀስ በቀስ ወደ መርህ ደረጃ ተለወጠ፡፡

ሆጋን በአንድ ጨዋታ ላይ የጎል እድል ለመፍጠር ብዙ አካላዊ ጉሽሚያዎችን ችሎ ድሪብል እያደረገ የተጋጣሚ ቡድን ግብ ክልል ሲደርስ አጠንክሮ የመታው ኳስ በሚያናድድ ሁኔታ ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጣበት፡፡ ከዚህ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኙ ስፌን ዊታከርን በጨዋታው ላይ ስለተፈጠሩት ግላዊ ችግሮቹ ” በጨዋታው ቦታ አያያዜ ተገቢ አልነበረምን? እንቅስቃሴዬስ ሚዛኑን ስቷል?” በማለት ጠየቃቸው፡፡ አሰልጣኙም በቸልተኝነት ስሜት ዝም ብሎ መሞከሩን እንዲቀጥልና ከአስር ሙከራዎች አንዱን ማስቆጠር መቻል በቂ እንደሆነ ነገሩት፡፡ ሌሎች ቢሆኑ አለማወቃቸውን አልያም የግዴለሽነት አቋማቸውን ለማሳየት ትከሻቸውን በመነቅነቅ ሁኔታውን ያሳልፉት ነበር፡፡ እንከን የለሽ በሆነ የተሟላ ስራ ብቻ የሚረካው ሆጋን ግን በጉዳዩ ዙሪያ ብዙ አሰበበት፤ አወጋበትም፡፡ እንዲህ አይነት ድክመቶች ከእድል ጋር የተያያዙ ሳይሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ጥገኛ ስለመሆናቸው እርግጠኛ ሆኖ ያውጠነጥን ጀመር፡፡ “ከዚያች እለት አንስቶ ነገሮችን በጥልቀት ለመረዳት ማሰብ እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ይህንንም በትክክል ትልልቅ ስብዕና ካላቸው ተጫዋቾች ከማገኘው ጥሩ ጥሩ ምክሮች ጋር ማዋሃድ ቀጠልኩ፡፡ ወደ አሰልጣኝነቱ አለም ስገባም ሁሌም አብሮኝ የኖረው ስለነገሮች አጥብቆ የመረዳት ፍላጎት አገዘኝ፡፡ ይህ የማወቅ መሻቴ እንደ አንድ ወጣት ፕሮፌሽናል ራሴን እንዳስተምር፣ እንዳሰለጥንና እንዳሻሽል ትልቅ ድጋፍ ማድረጉ ግልጽ ነው፡፡” ይላል፡፡

ሆጋን በበርንሌዮች ኋላ-ቀር የእግርኳስ አቀራረብ ተስፋ ቆረጠ፡፡ በመጨረሻም ገንዘብ-ነክ አለመግባባቶች በ23 አመት እድሜው ለመጀመሪያ ጊዜ ላንክሻየርን እንዲለቅ ገፋፋው፡፡ ቀደም ሲል በበርንሌይ ለጥቂት ጊዜያት በሚያውቃቸው የፉልሃሙ አሰልጣኝ ሃሪ ብራድሾውም ተሳበ፡፡ ብራድሾው የራሱ የሆነ የተለየ አጨዋወት አልነበረውም፤ ከአሰልጣኝነቱ ይልቅም የንግድና አስተዳደር ስብዕናው ያይልበት ነበር፡፡ ሆኖም ግን የእግርኳስ ጨዋታ በምን መንገድ መካሄድ እንዳለበት ግልጽ የሆነ ሐሳብ ነበረው፡፡ የ< ኪክ-ኤንድ-ረሽ> አቀራረብ ደጋፊ ባለመሆኑ ተከታታይ ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን የሚያስቀድሙ ስኮትላንዳውያን አሰልጣኞችን በመቅጠር በቡድኑ አባላት መካከል በአዎንታዊነት የሚጠቀስ የሃገሪቱን ውክልና አረጋገጠ፡፡ የክለቡ ሰዎች ይህንን ባህል ለዘለቄታው እንዲላመዱት ካደረገ በኋላም ቡድኑን ለቀቀ፡፡

የሆጋን አዲሱ ክለቡ መመሪያና አቋም ፍጹም በማያሻማ መልኩ ስኬታማ ነበር፡፡ተጫዋቹ ፉልሐሞች በ1906 እና 1907 በተካሄዱት የሃገሪቱ ደቡብ ሊግ ሻምፒዮንሺፕ አሸናፊ እንዲሆኑ አስቻላቸው፡፡ በ1908 ደግሞ በእግርኳስ የሊግ እርከን የሁለተኛ ዲቪዚዮንን እንዲቀላቀሉ አገዛቸው፡፡ በዚሁ አመት በእግርኳስ ማህበሩ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሰውም በኒውካስል ዩናይትድ ተሸንፉ፡፡ ይህም ሆጋን በክለቡ ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ሆነ፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያት ከጉልበት ጉዳት ጋር ሲታገል በመክረሙ በክለቡ የቢዝነስ ጉዳዮች ሹሙ ብራድሾው ተጫዋቹን ከቡድኑ ጋር ማሰንበት የሚያመጣውን ችግር በማጤን ሆጋን የሚለቅበትን ውሳኔ አሳለፈ፡፡ ከዚያም ሆጋን ለአጭር ጊዜ በሲውንደን ታውን ቆይታ አደረገ፡፡ ኋላም የቦልተን ዎንደረርስ ሰዎች የእሁድ ማለዳ ጸሎት አድርሶ በሚወጣበት አንድ ሰንበት ከቤተክርስቲያን ቅጥር ጊቢ ውጭ ጠብቀውት ወደ ሰሜን-ምዕራብ የሃገሪቱ ክፍል እንዲመለስ አሳመኑት፡፡

በዚያው አመት ቦልተን ወደ ታችኛው የሊግ እርከን በመውረዱ ሳቢያ ተጫዋቹ በክለቡ የነበረው ቆይታ አስደሳች አልሆን አለው፡፡ ሆኖም ወደ ኔዘርላንድስ የተደረገው የቅድመ-ውድድር ዘመን ጉዞ ሆጋን በአውሮፓ የነበረውን እግርኳሳዊ እምቅ ኃይል እንዲሁም ተጫዋቾች አዳዲስ ነገሮችን ለመቃረም ያላቸውን ብርቱ ፍላጎት እንዲገነዘብ ረዳው፡፡ በወቅቱ የእንግሊዝ እግርኳስ የአሰልጣኝነት ሙያን እምብዛም የማያስፈልግ አድርጎ ቢወስድም ደቾቹ ደግሞ በጽኑ ይሹት ነበር፡፡ ዶርድሬችትን 10-0 ከረቱ በኋላ አንድ ቀን ተመልሶ እነዚያ ተጫዋቾች እግር ኳስን እንዴት በአግባቡ ሊጫወቱ እንደሚገባ ሊያስተምራቸው ለራሱ ቃል ገባ፡፡ በወቅቱ ጄምስ ሃውክሮፍት ከተባለ የ< ሬድ ካር> ድርጅት መሃንዲስና ስመጥር ዳኛ ጋር ጥሩ ወዳጅነትን መሰረተ፡፡ ሃውክሮፍት በመደበኛነት የባህር ማዶ ጨዋታዎችን እንዲመራ ስለሚደረግ በርካታ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኃላፊዎችን ያውቃል፡፡ አንድ ምሽት ሃውክሮፍት ዶርድሬችቶች አዲስ አሰልጣኝ ሊቀጥሩ እንደሚፈልጉ ለሆጋን ገለጸለት፡፡ በብሪታኒያውያኑ አጨዋወት የተካነ ስልጡን ባለሙያ በተሻለ እንደሚመርጡ ተስፋ ስለመሰነቁም አወጋው፡፡ ግጥምጥሞሹ የሚገርም ፣ እድሉ ደግሞ ፍጹም ሊታለፍ የማይገባ በመሆኑ ሆጋን ወዲያውኑ ማመልከቻውን አስገባ፡፡ ቃል ከገባ ከአንድ አመት በኋላ በሃያ ስምንት አመት እድሜው በሁለት አመት የቆይታ ውል ቃል ኪዳኑን ሊጠብቅ ወደ ሆላንድ ተመለሰ፡፡

የሆጋን ተጫዋቾች አብዛኞቹ ተማሪዎችና አማተሮች ነበሩ፡፡ ሆኖም “ብሪታኒያውያኑ ሊሰለጥኑበት ይገባ ነበር፡፡” ብሎ በሚያስብበት የፕሮፌሽናሊዝም መንገድ ይይዛቸው ጀመር፡፡ የአካል ብቃት ደረጃቸውን በማሻሻሉ ረገድ ተጋ፤ ተሳካለትም፡፡ ቁልፉ ጉዳይ ግን የኳስ ቁጥጥር ብቃታቸውን ማሳደጉ እንደሆነ ያምን ነበር፡፡ ቡድኑ በቀድሞው የስኮትላንዶች አጨዋወት ስልት የተቃኘ፣ ብልሀት የታከለበት፣ የተደራጀ፣ የሚያድግና የሚሻሻል አቀራረብ እንዲኖረው እንደሚሻ ተናገረ፡፡ አብዛኛዎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡ ተማሪዎች ስለነበሩ ለማጥናትና አዲስ ነገር ለመረዳት ጉጉዎች ሆኑለት፡፡ ሆጋንም በመሰረታዊ የእግርኳስ ንድፈ ሐሳባዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያዎችን እያዘጋጀ ጠመኔና ጥቁር ሰሌዳን በመጠቀም እግርኳስን በምን መልኩ ሊጫወቱ እንደሚገባ የነበረውን ፍላጎት ይተነትንላቸው ጀመር፡፡ በተግባር ስልጠና ላይ ብቻ ከማተኮር ባለፈ በክፍል ውስጥ በምስሎች በተደገፉ ማሳያዎች ተጫዋቾቹ በታክቲክ፣ እንቅስቃሴያዊ የቦታ አያያዝና አጠባበቅ ረገድ ጥሩ ግንዛቤና አረዳድ እንዲኖራቸው አደረገ፡፡

በወቅቱ ደቾች ከጀርመን ጋር አከናውነውት የ2-1 ድል ባገኙበት ጨዋታ ሆጋን ብሄራዊ ቡድናቸውን እንዲመራላቸው ጠየቁት፡፡ ሆኖም በሚጠበቅበት ሃላፊነት ስኬታማ፣ ስመጥርና ብቁ የነበረው ሆጋን በሰላሳ አመቱ በተጫዋችነት ገና ብዙ ሊያበረክት እንደሚችል በማሰቡ የዶርድሬችቶች ውሉ ሲጠናቀቅ የደቾቹን ግብዣ በመተው ቀድሞውኑ ከመዝገባቸው ወዳልፋቁት ቦልተኖች ተመለሰ፡፡ በክለቡ ለአንድ አመት ብቻ ቆይቶ ወደ ላይኛው የውድድር እርከን ከፍ እንዲሉ አስቻለ፡፡ ይሁን እንጂ መፃኢ ግዜው በአሰልጣኝነት የሚገፋበት እንደሆነ ያውቀው ነበር፡፡ በ1912 ክረምት ሌላ ስራ መፈለግ ጀመረ፡፡ ሃውክሮፍትም በድጋሚ የሆጋን እግርኳስ ህይወት ላይ የነበረውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ቀጠለ፡፡ ከታላቁ የኦስትሪያ እግርኳስ አባት ሑጎ ሜይዝል ጋር ወዳጅነት እንዲመሰርትም መንገዱን አመቻቸለት፡፡

ሑጎ ሜይዝል በ1881 በቼክሪፐብሊኳ የቀድሞ ግዛትና ታሪካዊ ከተማ ቦሄሚያ ውስጥ ማላስቻው በተባለ አካባቢ ከመካከለኛው መደብ የአይሁድ ቤተሰቦች ተወለደ፡፡ ገና በለጋ እድሜው ቤተሰቦቹ ወደ ቪየና አቀኑ፡፡ በኦስትሪያም በእግርኳስ ፍቅር ተለከፈ፡፡ ከፍ ሲልም ክሪኬት የተባለው ክለብ ላገኘው መጠነኛ ስኬት የበኩሉን አስተዋፅኦ አበረከተ፡፡ ምንም እንኳ አባቱ ወደ ንግዱ አለም እንዲያመራ ቢፈልጉም እርሱ ግን ትሪስቴ በተባለችው ከተማ ጣልያንኛን አቀላጥፎ የሚናገር እና ሌሎች ቋንቋዎችም ለመልመድ የሚታትር ሰራተኛ ሆኖ አገኙት፡፡ የውትድርና ግዴታውን ሊወጣ ወደ ኦስትሪያ ሲመለስ አባቱ በባንክ ቤት እንዲሰራ ያቀረቡለትን ጥያቄና ያመቻቹለትን እድል ተቀበለ፡፡ ጎን ለጎንም በሃገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ መስራት ጀመረ፡፡ መጀመሪያ በእግርኳስ ማህበሩ ውስጥ የሚያገለግለው ገንዘብ ከማሰባሰብ ጋር በተያያዙ ስራዎች ነበር፡፡ ልክ እንደ ሆጋን ብልህ የመስመር አጥቂ የነበረው ሜይዝል የእግርኳስ አጨዋወት ሊከወን ስለሚገባበት መንገድ ባለው የተለየ ሀሳብና ጽኑ አቋም ቀጣይ የኦስትሪያ እግርኳስ አካሄድን የሚመራ ፍኖተ ካርታ ለመቅረጽ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ቀስ በቀስም ሚናው እየጎላ ሄዶ የኦስትሪያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና አስተዳዳሪነቱ ሲረጋገጥ የባንክ ስራውን ከነአካቴው ተወው፡፡

በ1912 ሃውክሮፍት በመራው ጨዋታ ኦስትሪያና ሃንጋሪ 1-1 በሆነ ውጤት አቻ ተለያዩ፡፡ ሜይዝል በውጤቱ ተበሳጨና ሃውክሮፍትን የቡድኑ ችግር የቱ ጋር እንደሆነ ጠየቀው፡፡ ሃውክሮፍትም የተጫዋቾቹን የተናጠል ቴክኒካዊ ብቃት ሊያሳድግ የሚችልና የጥንት ጓደኛውን ጂሚ ሆጋንን የመሰለ ብቁ አሰልጣኝ የሚያስፈልጋቸው ስለመሆኑ አሳወቀው፡፡ ሜይዝልም ሳይውል ሳያድር በዋነኝነት የኦስትሪያን ብሄራዊ ቡድን ለስቶኮልሙ ኦሎምፒክ እንዲያዘጋጅ፣ በከፊል ደግሞ በሃገሪቱ የሚገኙትን ትልልቅ ክለቦች እንዲመራ በስድስት ሳምንታት የውል ስምምነት ሆጋንን ቀጠረው፡፡

የመጀመሪያው የሆጋን የልምምድ መርኃ ግብር በጥሩ መንፈስ አልሄደለትም፡፡ ኦስትሪያውያኑ ተጫዋቾች አዲሱን አሰልጣኝ ሊረዱት አልቻሉም፡፡ “ስረ-መሰረታዊ መርሆዎችና አስተምህሮዎች ላይ እጅጉን የሚያተኩር አቀራረብ አለው፡፡” ብለው አጉተመተሙ፡፡ ሜይዝል ግን በሆጋን አካሄድ ተደመመበት፡፡ እግርኳስን ስለሚያዩበት ዘዌም ምሽቱን ሙሉ ሲያወጉ አመሹ፡፡ ለአርባ አመታት ያህል በእግርኳሱ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው 2-3-5 ፎርሜሽን ታክቲካዊ በሆነ መነጽር ሲቃኝ እምብዛም ችግር እንዳልነበረበት አመኑ፡፡ ሆኖም በርካታ ቡድኖች ፎርሜሽኑን በሚጠቀሙበት አካሄድ ላይ የግትርነት እና የተገማችነት አዝማሚያ ስለሚያሳዩ በእግርኳስ የተጫዋቾች እንቅስቃሴያዊ ቦታ አያያዝ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ተረዱ፡፡ “የኳሱ ሒደት ሙሉ የጨዋታውን እንቅስቃሴ መምራት ይኖርበታል፡፡” ብለውም ተስማሙ፡፡ በውይይታቸው ፍጥነት ያለው የቅብብሎች ውህደት ከድሪብሊንግ የተሻለ ስለመሆኑ መግባባት ላይ ደረሱ፡፡ በደቡብ አሜሪካ እንደሚታየው ተጫዋቾች ጠመዝማዛ በሆነ ቀላል ስልት የተናጠል ሩጫ ከሚከውኑበት እንቅስቃሴ በላቀ ቴክኒካዊ ክህሎታቸውን በመጠቀም ፈጣን ኳሶችን በጥሩ ሁኔታ ተቆጣጥረው መልሰው ደግሞ በቶሎ የሚለቁበትን መንገድ እያመቻቹ የተሳኩ ቅብብሎች ማድረግ እጅግ ወሳኝ እንደሆነም መከሩበት፡፡ ሆጋን የተጋጣሚ ተከላካይ ክፍልን እንዳይረጋጋ በማድረግ ረገድ ልኬታቸው እና መዳረሻቸው ለተጠበቁ ረጃጅም ቅብብሎች ለየት ያለ ትኩረት የመስጠት ዝንባሌን አሳየ፡፡ ቅብብሎቹ እንዲሁ በዋዛ ፈዛዛ ወደፊት የሚጠለዙ ካልሆኑ ያላቸው ዋጋ አዎንታዊ እንደሆነም ጠቀሰ፡፡ ሜይዝል በተጨባጭ የሌሉ ነገሮች ላይ በጥልቀት የሚያተኩርና ሃሳባዊነት የሚያመዝንበት ሰው ነበር፡፡ ሆጋን ደግሞ ሐሳቦቹ ከህልዮታዊ ጉዳዮች በላይ በነባራዊ እውነታ ላይ የተመሰረቱ እንዲሁም ሁኔታዎችን እንደአመጣጣቸው የሚያስተናግድ ወይም መፍትሄ የሚሰጥ ሰው ሲሆን ለቅብብሎች ቅድሚያ ስለሚሰጥ አቀራረብ ሲሰብክም አልታየም፡፡ ትክክለኛው የአጨዋወት ስልት < ይሄኛው> ነው ብሎ ለረባ ላልረባው ጥንቃቄን የሚያደርግ አረዳድም አላሰፈነም፡፡ በቀላሉ ” ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ምርጡ መንገድ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት መዝለቅ መቻል ነው፡፡” ብሎ ያምን ነበር፡፡

በስቶኮልሙ ኦሎምፒክ ኦስትሪያ ጀርመን ላይ የ5-1 ድል ብትቀዳጅም በሩብ ፍጻሜው ግን በሆላንድ 4-3 ተረታች፡፡ የጀርመን እግርኳስ ፌዴሬሽን ሜይዝል ሆጋንን እንዲሰጣቸው ፈቃድ ቢጠይቁትም በሆጋን ላይ ከፍተኛ እምነት የነበረው ሜይዝል የጀርመኑን ስራ ለሆጋን ከማመቻቸት ይልቅ እዚያው ቆይቶ የኦስትሪያን ቡድን ለ1916ቱ ኦሎምፒክ እንዲያዘጋጅ አዘዘው፡፡ ” ጭልምልም ያለችውን ጭጋጋማ የኢንደስትሪ አካባቢዬን ላንክሻየር ለቅቄ ደመቅመቅ ወዳለችው ቪየና መሄድ ገነትን የመውረስ ያህል አስደሳች ከፍታ ላይ መውጣት ነበር፡፡” ይላል ሆጋን ጊዜውን ሲያስታውስ፡፡ ከኦሎምፒክ ቡድኑ ጋር በሳምንት ሁለቴ እየሰራ በቀሪው ጊዜ የከተማዋን ትልልቅ ቡድኖች ማሰልጠኑን ቀጠለ፡፡ እጅጉን በስራ ከመወጠሩ የተነሳም ከለሊቱ 11:30 እየተነሳ የዌይነር ኤፍ.ሲ.ን የልምምድ መርኃግብር ለማካሄድ ተገደደ፡፡ ኦስትሪያ ሆጋንን ቀሰቀሰች፤ ሆጋንም ኦስትሪያን አነቃ፡፡ “እግርኳሳቸው እንደ ዋልዝ ጭፈራ ቀለል ያለና አስደሳች ይዘት ነበረው፡፡” ሲል ሆጋን ያወሳል፡፡

ሜይዝል ደግሞ በ1916 ቡድኑ ስኬታማ እንዲሆንለት ተስፋን ሰነቀ፡፡ አንደኛው የአለም ጦርነት ግን ህልሙን አጨነገፈበት፡፡ ሆጋንም የእልቂቱ ገፈት ቀማሽ ላለመሆን የብሪታኒያ ቆንጽላ ጋር ቀርቦ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ትውልድ አገሩ በፍጥነት መመለስ ይሻል እንደሆነ ምክር ጠየቀ፡፡ ብዙም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ በተነገረው አርባ ስምንት ሰዓታት ልዩነት ጦርነቱ ታወጀ፡፡ ከአንድ ቀን በኋላም < የውጭ ዜጋ> በሚል ስም ሆጋንም ተያዘ፡፡ የአሜሪካን ቆንጽላ ባለቤቱንና ልጆቹን በመጋቢት 1915 ወደ ብሪታኒያ መለሳቸው፡፡ በጀርመን ወደሚገኝ ጊዜያዊ የእስረኞች ማጎሪያ ከመዛወሩ አንድ ቀን በፊት በቪየና የሚያውቁት እና በከተማዋ የእቃዎች መጋዘን ያስተዳድሩ የነበሩ የብሊዝ ወንድማማቾች ዋስ ሆነው ቀርበውለት ሆጋን ከእስር ተለቀቀ፡፡ ተያዥ የሆኑለት ሰዎችን ልጆች ለአስራ ስምንት ወራት ቴኒስ እንዴት መጫወት እንዳለባቸው በማስተማር ሲያገለግል ከረመ፡፡ ሆኖም ግን ከሃገሪቱ ምስራቃዊ አቅጣጫ 130 ማይሎች ያህል ራቅ ብሎ ሆጋንን ወደ እግርኳስ የመመለስ ጥረት ይደረግ ጀመር፡፡ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የተማረው የቡዳፔስቱ ኤም.ቲ.ኬ. ክለብ ምክትል ስራ አስኪያጅ ባሮን ደርስቴይ ሆጋን ስለሚገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ ሰምቶ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ካደረገ እና ተገቢ ግዴታዎችን ከተወጣ በኋላ ሆጋን በየእለቱ ለከተማው ፖሊሶች በመደበኛነት ሪፖርት የማድግ ፍላጎትን ካሳየ ክለቡን እንዲያሰለጥን ሁኔታዎችን አመቻቸለት፡፡

ሆጋን በሙሉ ፈቃደኝነት ውሳኔውን ተቀበለ፡፡ ከቡድኑ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች አብዛኞቹ በጦር ግንባር የሚገኙ በመሆናቸው ቀዳሚ ተግባሩ ክለቡን የሚመጥኑ ተጫዋቾች በመሰብሰብ ጠንካራ ቡድን መገንባት ሆነ፡፡ ከዚያም ፊቱን ወደ ወጣቶች በማዞር የክለቡን ሁለት ታዋቂ ተጫዋቾች ጂዮርጂ ኦርዝና ጆሴፍ ‘ኬስቢ’ ብራውንን ለመመልመል በቃ፡፡ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ወደ ቡድኑ ካዛወራቸው በኋላ በክለቡ ስታዲየም አንጎል ፓርክ በዝግታ አጎለበታቸው፡፡ ስለተጫዋቾቹ ሲያብራራም “የመለመልኳቸው እኔ ነኝ፤ ስለዚህም የእኔ ናቸው፤ የኔ ብቻ!” ይላል፡፡ “በቡዳፔስት የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ባለ ብሩህ አዕምሮ ወጣቶች ናቸው፡፡ ዘወትር ከትምህርት ሰዓት በኋላ በሜዳ ላይ አገኛቸውና ስለ ጨዋታው ጥበባዊ ዳራ አስተምራቸዋለሁ፡፡” በማለት ወጣቶቹን እንዴት እንደገራቸው ይገልፃል፡፡ በእርግጥም ብራውንና ኦርዝ ለመማር ትጉህና ጉጉ ነበሩ፡፡ ሁለቱም በወቅቱ በማዕከላዊው አውሮፓ የሚገኙ ሌሎች ተጫዋቾችን አይነተኛ ባህሪ የሚያሳዩ፣ ሆጋንም አብረውት እንዲሰሩ የሚመኛቸው አይነት ወጣቶችን የሚወክሉ ሆኑለት፡፡ በቪየናና ቡዳፔስት ሲኖር በቤቱ ያለ ያህል የሚሰማው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ” አህጉራዊው እግርኳስ ከብሪታኒያ እግርኳስ በተሻለ ተጫዋቾች የጨዋታውን ጥበባዊ ገጽታ ገና በልጅነት እድሜያቸው እንዲማሩት ያደርጋል፡፡” ሲልም ልዩነቱን ያስቀምጣል፡፡

የሆጋን እግርኳሳዊ አቀራረብ አስገራሚ ውጤታማነትን ማሳየት ጀመረ፡፡ ውድድሩ በጦርነት ምክንያት ለጥቂት ጊዜያት ተቋርጦ እንደገና ሲጀምር በ1916/17 የውድድር ዘመን ኤም.ቲ.ኬ. የመጀመሪያውን ይፋዊ የሊግ ዋንጫ አነሳ፡፡ ለቀጣዮቹ ዘጠኝ አመታትም ይህንኑ ስኬታማ ጉዞ ቀጠለበት፡፡ ጦርነቱ እያበቃ በሔደበት ጊዜም በቡዳፔስት የተሰባሰቡ ተጫዋቾችን የያዘው ቡድን ቦልተን ዎንደረርሶችን 4-1 በመርታት እያደገ የመጣውን አህጉራዊ ጨዋታ ጥንካሬ፣ የበላይነት እና እድገት ማሳያ ምልክት ሰጠ፡፡ ሆጋን ከኤም.ቲ.ኬ.ተከታታይ ድሎች ውስጥ በሁለቱ ላይ ብቻ አብሯቸው የመሆን እድል ኖረው፡፡

ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም በቻለው ፍጥነት ወደ አገሩ ብሪታኒያ ተመለሰ፡፡ ” በሃንጋሪ ያሳለፍኩት ጊዜ የኦስትሪያውን ያህል አስደሳች ነበር፡፡ ቡዳፔስት ተወዳጅ ከተማ ናት፡፡ በእኔ እይታ ከአውሮፓ በጣም የተዋበችውም ይህቺው መዲና ትመስለኛለች፡፡” ይላል፡፡ ይህም ሆኖ በሁለቱ ከተሞች በቆየባቸው ጊዜያት ከባለቤቱና ልጆቹ ጋር ያልተገናኘባቸው አራት አመታት እጅጉን ከብደውት አለፉ፡፡ ከቡድኑ አንጋፋ ተጫዋቾች አንዱና ከሃያ ሁለት አመታት በኋላ ደግሞ በብራዚል እግርኳስ እድገት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያበረከተው ዶሪ ኩርስችነር የኤም.ቲ.ኬ. አሰልጣኝነት መንበሩን በመረከብ የሆጋን የመጀመሪያ አልጋ ወራሽነት ቦታውን ተቆናጠጠ፡፡

ሆጋን ወደ ላንክሻየር ተመልሶ በሊቨርፑል ከተማ < ዎከር’ስ ቶባኮ> ለተባለ የሲጋራ አምራች ድርጅት የደብዳቤዎችና ሪፖርቶች ክፍል ኃላፊ ሆኖ በመቀጠር ስራ ጀመረ፡፡ ሆኖም የገቢው አናሳ መሆን ካቅሙ በላይ ሆነበትና በጦርነቱ ወቅት የኢኮኖሚ ውድቀት ለደረሰባቸው አካላት የገንዘብ እርዳታ ማድረግ ለጀመረው የእግርኳስ ማህበር የደረሰበትን ችግር አብራርቶ እንዲያቀርብ ምክር ተለገሰው፡፡ ያ ጊዜ በሆጋን የስራ ህይወት ላይ ወሳኝ ለውጥ የተደረገበት ሆነ፡፡ ቀደም ሲል ሁለት መቶ ፓውንድ እዳ ነበረበት፤ ወደ ለንደን የሚመላለስበት የመጓጓዣ ወጪውን የሚሸፍንበት አምስት ፓውንድ ተበድሯል፡፡ የእግርኳስ ማህበሩ ጸሀፊ ፍሬድሪክ ዎል ሆጋንን በማንቋሸሽ መልኩ አስተናገደው፡፡ “እርዳታ የምናደርገው በጦርነቱ ወቅት ለተዋጉት ሰዎች ነው፡፡” አለው፡፡ ለአራት አመታት በሰው አገር የታሰረ እንደሆነና ወታደራዊ ግልጋሎት የመስጠት እድሉ እንዳልነበረው አስረዳ፡፡ የዎል ምላሽም ሶስት ጥንድ የካኪ ካልሲዎችን ሰጥቶ ” በግንባር ያሉት ወጣቶች በነዚህ እጅጉን ደስተኞች ናቸው፡፡” ብሎ አፌዘበት፡፡ ሆጋን በጣም አዘነ፤ ተቆጣም፡፡ በዚህ ክስተት የእግርኳስ ማህበሩ የሆጋንን ፍጹም ይቅርታ ለዘመናት ሳያገኝ ቀረ፡፡ ሃገሪቱም በወግ አጥባቂ ስርዓት በተሸበበው የአጨዋወት መንገዷ ላይ ጥልቅና ብሩህ የእግርኳስ ሐሳቦችን ሊያፈልቅ የሚችለውን ባለሟል ገፍታ የአሰልጣኝነት ክህሎቱን እንዳጣች ኖረች፡፡

ጦርነቱ ካበቃ ጥቂት ጊዜያት በኋላ ኦስትሪያ ከደቡብ ጀርመን ጋር ተጫውታ 5-0 ተረታች፡፡ ይህ ሽንፈት ሜይዝል በሃገሪቱ የእግርኳስ አጨዋወት ስልቱ ላይ ያሳደረውን እምነት የሚፈትን ቢሆንም በሆጋን የተቀረጸውን የእግርኳስ እድገት እቅድ በቪየና ለማስቀጠል ወደደ፡፡ በኑረንበርጉ አባጣ ጎርባጣና የጨቀየ ሜዳ ላይ ተቀራርቦ በመቀባበል ላይ የተመሰረተው አጨዋወታቸው ተግባራዊ ሊደረግ የማይችል እንደሆነ በማስተዋሉ ተስፋ የቆረጠ የሚመስለው ሜይዝልም ወደ ቪየና በሚመልሳቸው ጉዞ ላይ የተለመደውን አጨዋወት ዘይቤ በመተው የበለጠ ቀጥተኛና የአካል ብቃት ላይ በሚያተኩረው ዘዴ መቅረብ ይሻል እንደሆነ ከተጫዋቾቹ ጋር መወያየቱን ቀጠለ፡፡ ተጫዋቾቹ ግን “ፍጹም የማይሆን ነው!” በማለት ምላሽ ሰጡ፡፡ ይህ እምቢተኛ አቋምም በ1930ዎቹ መጀመሪያ አመታት ያደገውና < ዉንደርቲም> ተብሎ የሚጠራው ቡድን የሚታወቅበትን የጨዋታ መሰረታዊ መርሆችን ቀርጾ ለማስቀመጥ አስቻለ፡፡ ይህ ቡድን ስኬታማ መሆን ካልቻሉ ታላላቅ ቡድኖች ውስጥ የመጀመሪያው ነው፡፡ በሜይዝል አመራር ስር “በእግርኳስ ጎሎችን ማስቆጠር በመቶዎች የሚቆጠሩ ውስብስብና የተራራቁ ቅንብሮችን ለማዋሃድ ከሚደረገው ጥረት የቀለለ ተግባር እንደሆነ የሚታይበትና የጭፈራ ውድድር ትዕይነት የሚስተናገድበት መድረክን መሰለ፡፡” በማለት ብሪያን ግላንቪል ጽፏል፡፡

የ< ፒራሚድ> ቅርጽ ያለው መደበኛ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር መሰረታዊ ግኝቱን ይዞ ሰነበተ፡፡ ከጨዋታ አቀራረብ ስልቶች መካካል እየተስፋፋና እተሻሻለ የሄደው የስኮትላንዳውያኑ ቅብብሎች ላይ የተመሰረተው ዘይቤ በእንግሊዝ ከተንሰራፋው አጨዋወት የተለየ መልክ ነበረው፡፡ ይህ ስልት < ዳኑቢያን ስኩል> ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ በዚህ አጨዋወት ከአካላዊ የበላይነት በተሻለ ቴክኒካዊ ክህሎት ቦታ ተቸረው፤ በቡድን መዋቅር ውስጥም አስፈላጊነቱ ናረ፡፡ በደቡብ አሜሪካ ደግሞ እግርኳስ ከመሰረታዊ ይዘቱ፣ቅርጹ አልያም ግኝቱ በተለየ መልክ ጎልብቶ መስፋፋት ጀመረ፡፡ እዚህም ቴክኒካዊ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት ተሰጣቸው፡፡ ሆኖም ግን በዩሯጓይ እና በተለይ ደግሞ በአርጀንቲና በጨዋታ ወቅት በግለኝነት ስሜት የሚደረግ ራስን የመግለጽና ችሎታን የማሳየት አዝማሚያዎች ይበልጡን ተወዳጅ ሆኑ፤ ተቀባይነታቸውም ጨመረ፡፡

ይቀጥላል…


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

-Sunderland: A Club Transformed (2007)

-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

-The Anatomy of England (2010)

-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

-The Anatomy of Liverpool (2013)

-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK