ቻምፒየንስ ሊግ | ጅማ አባ ጅፋር ለመልሱ ጨዋታ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል 

በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የ2018/19 ቅድመ ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳ ውጭ የጅቡቲ ቴሌኮምን 3-1 በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕድሉን አስፍቶ የተመለሰው ጅማ አባ ጅፋር የመልስ ጨዋታውን ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደርጋል።

በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በውድድሩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር የቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጅቡቲ በማቅናት ቴሌኮምን በአስቻለው ግርማ (አንድ) እና በማማዱ ሲዲቤ (ሁለት) ጎሎች 3-1 በመርታት ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉን አስፍቶ መመለሱ ይታወሳል።

ጅማ አባጅፋር ነገ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ለሚኖረው የመልስ ጨዋታ ዛሬ ከረፋዱ 04:30 ጀምሮ በአዲስ አበባ ስቴዲየም  የመጨረሻ ልምዳቸው በሚያደርጉበት ወቅት ከቡድኑ ጋር አብረው ወደ ጅቡት ያልተጓዙትን ተጫዋቾች በመጨመር ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሰርተዋል። ከቡድኑ ጋር ተያይዞ ያለው ዜና ባሳለፍነው ሳምንት በጉዳት ምክንያት ከመጀመርያው ጨዋታ ውጭ የነበሩት ጋናዊው የአምናው የሊጉ ኮከብ ግብጠባቂ ዳንኤል አጄይ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ ለነገ ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ሲታወቅ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ላይ ጎሎችን በማስቆጠር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የታየውና ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የቆየው ጋናዊው አጥቂ ቢስማርክ አፒያ ለጨዋታው እንደሚደርስ መሰማቱ ለጅማ አባጅፋሮች መልካም ዜና ሆኗል።

በሌላ ዜና በጅቡቲው የ3-1 ድል በመጀመርያ ተሰላፊነት መጫወት የቻሉት ግብጠባቂው ዘሪሁን ታደለ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዐወት ገ/ሚካኤል ባጋጠማቸው ጉዳት ከነገ ጨዋታ ውጭ መሆናቸው የህክምና ባለሙያው ገልፀዋል።

የጅቡቲው ቴሌኮም አንድ የውጪ ዜጋ ተጫዋችን ጨምሮ በአጠቃላይ 27 የልዑክ ቡድን በመያዝ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚያደርግ ይሆናል። ነገ 10:00 ላይ በሚደረገው የመልስ ጨዋታም ኬንያውያን ዳኞች ሲዳኙ የጨዋታውን ኮሚሽነር ከደቡብ ሱዳን ናቸው።

አባ ጅፋር ውጤቱን አስጠብቆ በድል ከተወጣ የ2018 የቻምፒየንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚው አል-አህሊን የሚገጥም ይሆናል።