የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-0 አዳማ ከተማ

በሊጉ 15ኛ ሳምንት ባህር ዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን በዚህ መልኩ ሰጥተዋል።
” እኛ በነሱ የሜዳ ክፍል ነው የዋልነው፤ እነርሱ ደግሞ ሜዳ ላይ ሲተኙ ውለዋል” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ

ጨዋታው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

እንደተመለከታችሁት ሙሉ ዘጠና ደቂቃ እነርሱ ሜዳ ላይ ነው የዋልነው። ይዘው ለመሄድ የፈለጉትን ነጥብ በዳኛ ታግዘው ይዘውት ሄደዋል ብዬ ነው የማስበው። በውጤቱ ማንንም መውቀስ አልፈልግም። ስለ ዳኝነቱ ብዙም አልናገርም፤ ሆኖም ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል። በአጠቃላይ ጨዋታው በልጠናቸው በሜዳቸው ነው የዋልነው። እነርሱ ደግሞ ሜዳ ላይ ሲተኙ ውለዋል። ውጤቱን በፀጋ መቀበል ነው።

በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ደስተኛ ነህ ?

ደስተኛ ነኝ፤ ግን ያገኘናቸው አጋጣሚን አልተጠቀምንም። ተጫዋቾቼ ይህን ነጥብ አግኝተው የተሻለ ደረጃ ይዘን በዋንጫው ፉክክር ውስጥ ሆነን እንድንጨርስ ይፈልጉ ስለነበር ከፍተኛ ጉጉት ላይ ነበሩ። አሁንም ከዋንጫው ፉክክር አልወጣንም። በዛሬ ጨዋታ ሦስት ነጥብ ለማግኘት እኔና ተጫዋቾቼ ፈልገን እስከ መጨረሻው ታግለን አልተሳካም። ተጫዋቾቼን ግን አመሰግናለው።

አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ቢቀራችሁም በሁለተኛው ዙር ምን ታቅዳለህ ?

እንዳያችሁት በቡድኔ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች በሙሉ የመጫወት አቅም ያላቸው ወጣቶች ናቸው። ባለፈው ዓመት እስከ ነሐሴ ድረስ በከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ደክመው ነው በዛው ወደ ፕሪምየር ሊግ የገባነው። አሁን እረፍቱን እንዴት አድርገው ተጫዋቾቼ ያገግማሉ የሚለው ነገር ነው እያሰብኩ ያለሁት።

” ውጤቱ አስታራቂ ነው” ሲሳይ አብርሃ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

የመጀመርያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን የጎል እድልም መፍጠርም ችለናል። ነገር ግን ስለቸኮልን መጠቀም አልቻልንም። ሁለተኛ አጋማሽ እነርሱ ረጃጅም ኳሶች መጫወት ጀመሩ። ያው ከሜዳ ውጭ የነበረ ጨዋታ በመሆኑ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሞክረን አልተሳካም። ድባቡ የደጋፊው በጣም ደስ ይል ነበር።

በውጤቱ ደስተኛ ነህ?

ያው ውጤቱ አስታራቂ ነው። መጀመርያ አጋማሽ ነበር ጎል ማስቆጠር የነበረብን ጥሩ በሆንበት ጊዜ ማለቴ ነው። ሁለተኛው አጋማሽ ሃምሳ ሃምሳ ነው። ስለዚህ በቂ ውጤት ነው፤ አስታራቂ ነው። ባህር ዳርም ጥሩ ቡድን ነው። ደጋፊውም በጣም ያምራል።

የበረከት ደስታ በተጠባባቂ ወንበር መቀመጥ ?

ትንሽ ህመም ነበረበት። ከዚህ በተጨማሪ በልምምድ ወቅት በምታየው ነገር ነው ተጫዋች ወደ ሜዳ የምታስገባው። በእግርኳስ ቋሚ የሚባል የለም። ልምምድ እና ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ከሆንክ እሱ ይታያል። በረከት 14 ጨዋታ ላይ በመጀመርያ አሰላለፍ ላይ የነበረ ነው። ሌሎች ተጫዋቾችም አሉ፤ እነርሱን ትጠቀማለህ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *