የፊፋ እግርኳስ ልማት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ፅህፈት ቤት በአዲስ አበባ ተከፈተ

የዓለም አቀፉ የእግርኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ በ2016 ለጀመረው “ፊፋ ፎርዋርድ” የእግርኳስ ልማት ማስፈፀምያነት በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ፅህፈት ቤቶችን መክፈቱን በመቀጠል 10ኛው ቢሮውን በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከፍቷል።

የምስራቅ አፍሪካን የእግርኳስ ልማት እንቅስቃሴ ለመከታተል ያለመው ይህ የክፍለ አህጉር ፅህፈት ቤት ከደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል በመቀጠል በአፍሪካ ሦስተኛው ሲሆን ቦሌ አካባቢ ፍሬንድሺፕ ሞል ጀርባ በሚገኘው አፎሚ ህንፃ ላይ ይገኛል። በኪራይ የተገኘው ይህ ቢሮም ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው።

የቢሮውን መከፈት በማስመልከት ሰኞ ቀትር ላይ በተዘጋጀው የማብሰርያ መርሐ ግብር ላይ የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚንስትር ሒሩት ካሳ፣ የፊፋ ዋና ፀኃፊ ፋትማ ሳሞራ፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ርስቱ ይርዳው፣ የካሬብያን እና አፍሪካ እግርኳሰ ልማት ዳይሬክተር ቬሮን ሞሴንጎ-ኦምባ እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ጂራ የተገኙ ሲሆን በመርሐ እብሩ መጠናቀቂያ ላይም የካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ተገኝተዋል።

የቢሮውን መከፈት የሚያበስረው ሪባን በጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና ሒሩት ካሳ ከተቆረጠ በኋላ በቬርን ሞሴንጎ-ኦምባ አማካኝነት በተጀመረው መርሐ ግብር የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ጂራ ባደረጉት ንግግር የፅህፈት ቤቱን መከፈት ጥቅም ገልፀዋል። ” እንኳን ወደ ሁለተኛ ቤታችሁ እና ወደ አፍሪካዋ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዲሁም የአፍሪካ እግርኳስ አባት ይድነቃቸው ተሰማ ሀገር ኢትዮጵያ በሰላም መጣችሁ። ወደ አመራርነት ከመጣን 7 ወራት ባስቆጠርንበት በዚህ ወቅት በሀገራችን፣ በዞናችን እና በአህጉራችን የእግርኳስ ልማት ላይ ለመስራት ጥሩ እድል ላይ እንገኛለን። የዚህ ቢሮ መከፈትም የምናልመው የረጅም ጊዜ እቅድን ለማሳካት ከማገዙ በተጨማሪ ፊፋ ይበልጥ ወደ እኛ ቅርብ እንዲሆን የሚያደርግ ነው። መንግስታችን የኪራይ ወጪውን በመሸፈን ለቢሮው መከፈት ትልቁን ሚና ተጫውቷል። ለዚህም መንግስታችንን በተለይም የስፖርት ኮሚሽን እና ኮሚሽነሩ ርስቱ ይርዳውን ማመስገን እፈልጋለሁ። ” በማለት መልካም የስራ ጊዜን ተመኝተው ንግግራቸውን ቋጭተዋል።

በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አዲስ አበባ በመገኘታቸው እና ቢሮውን በመመረቃቸው ደስታቸውን ገልፀዋል። አያይዘውም በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገኝተው ንግግር ስለማድረጋቸው እና ስለተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድም ገለፃ አድርገዋል።

” ትላንት በአፍሪካ መሪዎች ፊት ንግግር አድርጌ ነበር። ስለ እግርኳስ ኃያልነት ገልጫለሁ። እንዴት እግርኳስ አንድነትን እንደሚፈጥር፣ ከባቢን እንደሚቀይር ተናግሬያለሁ። ከአፍሪካ ኅብረት ጋርም ካፍን ባካተተ መልኩ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል። ዋና ዋና ነጥቦቹም አንደኛ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና ሙስናን መታገል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው። በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ሙስና ነው። ይህንን መታገል እና ለማስቆም መሞከር ይኖርብናል። ሁለተኛው የሚያተኩረው የስታድየሞች ፀጥታ እና ደህንነት ላይ ነው። ሰዎች ከዚህ በኋላ እግርኳስ ለመከታተል ወጥተው መሞት የለባቸውም። ሶስተኛው እና ዋናው ነጥብ ደግሞ እግርኳስን በትምህርት ቤቶች ማስፋፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው። በዓለማችን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና 700 ሚልየን ህፃናትን ማዳረስ እንፈልጋለን። ለዚህም 11 ሚልየን ኳሶችን እያከፋፈልን እንገኛለን። በእግርኳስ አማካኝነት ትምርህት እንዲያገኙ 100 ሚልየን ዶላር ፈሰስ አድርገናል። ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *