ዮናታን ሙሉጌታ
በ2018 በሩሲያ ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው የሚሳተፉትን አምስት ሀገራት ወደሚለየው የምድብ ድልድል ለመግባት ከኮንጎው አቻው ጋር የደርሶ መልሱን የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳው ላይ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 4ለ3 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በጨዋታው ላይ የነበሩትን አንዳንድ ታክቲካዊ ነጥቦችን እንደተለመደው አቅርባላችኋለች፡፡
በምስል አንድ ላይ እንደተመለከትነው ሁለቱ ቡድኖች ዝርያቸው (Variants) 4-4-2 የሆኑና በጨዋታ ሂደት የተወሰኑ የአተገባበር ልዩነቶች የታዩባቸው የሜዳ ላይ አደራደሮች (formations) ተጠቅመዋል፡፡ በተለመደው የ4-4-2 (flat 4-4-2) እና 4-1-3-2 መካከል የሚዋዋለውን የብሄራዊ ቡድናችን አጨዋወትም በኮንጎው ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ላይም በስፋት ተስተውሏል፡፡ በኮንጎ ብሄራዊ ቡድን በኩል ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች አንዱ ኮውቡምባ (9 ቁጥር) ወደኋላ ቀረት ማለትና ኳስን ለመቀበል መሞከር እንዲሁም ከሁለቱ የመሀል አማካዮች አቩዎኑ (23 ቁጥር) ወደ አጥቂዎቹ በተለይም ወደ ኮውቡምባ ቀረብ እያለ ኳሶችን ለማሻገር ጥረት የሚሞክርባቸው አጋጣሚዎች በቀር በጨዋታው አብዛኛውን ጊዜ የ ክላውድ ሌሮይ ቡድን ወደ flat 4-4-2 የቀረበ አጨዋወት ነበረው፡፡
እንደሚታወቀው የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን በተጫዋቾች ጥራት ፣ በኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ፣ በአካል ብቃትና በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ሰፊ ልምድ ባላቸው አሰልጣኙ በቅርብ ጊዜያት ከገጠምናቸው ቡድኖች እንዲሁም ከራሳችንም ብሔራዊ ቡድንም ላቅ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ቡድኑ የያዛቸው ተጫዋቾች በአፍሪካ እና በአውሮፓ ሊጎች ላይ ያላቸው ልምድ የትላንቱን ጨዋታ በሚፈልጉት መንገድ ለማስኬድ የጠቀማቸውም ይመስላል፡፡
በትላንቱ ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይነት ያለው የተጫዋቾች የቦታ አያያዝ መጠቀማቸው በጨዋታው ላይ በተለይም በመሀል ክፍሎቻቸው ላይ በተቃራኒ ቡድን ከሚገኙና ተመሳሳይ ሚና ካላቸው ተጫዋቾች ጋር እንዲጋፈጡ አድረርጓቸው ነበር፡፡ ይህም አንድ ለ አንድ ወይንም ደግሞ በጋራ (units) በሜዳው ክፍልፋዮች ላይ ከተቃራኒ ቡድን አቻ ተጫዋቾች ጋር የሚደረጉ ፉክክሮችን በተለይም በመሀል ሜዳና በሁለቱ መስመሮች በተደጋጋሚ እንድንመለከት አስችሏል፡፡
(ምስል 2)
በነዚህ ከላይ በተጠቀሱት አጋጣሚዎች ላይ በሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የኮንጎ ተጫዋቾች የተሻሉ ነበሩ፡፡ ለዚህም ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው በጨዋታው በግልጽ የታየው የሁለቱ ቡድኖች የተጫዋቾች ጥራት ደረጃ ልዩነት ነው፡፡ የአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ቡድን በቅርቡ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ እንደ ጎል እድል መፍጠሪያ አማራጭነት ይጠቀምባቸው የነበሩት ሁለቱን መስመሮች ነበር፡፡ እነዚህ መስመሮች ትላንት የፈጠራ አቅማቸው በጣሙን ተዳክሞና የኮንጎ ብሄራዊ ቡድን ዋነኛ የማጥቃት ምንጮች ሆነው ነበር፡፡ ሁለቱ የኮንጎ የመስመር አማካዮችና ተከላካዮች ተናበው በመጫወት በጨዋታው አብዛኛው ክፍለ ጊዜ በማጥቃቱ ላይ አመዝነው የኛን የመስመር አማካዮች በረከት እና አስቻለው ወደ ስዩምና ነጂብ ተጠግተው እንዲጫወቱ አስገድደዋቸዋል፡፡ ይህም ጫና የመስመር ተከላካዮቻችንን በመከላከል እንዲወሰኑ አስገድዷቸዋል፡፡
(ምስል 3)
ኮንጎዎች በመከላከል ላይ በሚሆኑበት ጊዜም የቡድናችንን የመስመር የማጥቃት ጨዋታ የመስመር ተከላካዮቻቸው ከመስመር አማካዮቻቸው ጋር እንዲሁም በቅርብ ከሚገኘው የመሀል አማካይ ጋር በመሆን በረከት እና አስቻለው ከሽመልስ ጋር የሚገናኙበትን ክፍተት በመዝጋት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የመስመር ጨዋታ መቆጣጠር ችለዋል፡፡
የመሀል ሜዳው እንቅሰቃሴም ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩን ትንተናዎች ላይ በተደጋጋሚ ስንጠቅሰው የነበረው የጋቶች ፓኖም ከተከላካዮች ኳስን ተቀብሎ የማሰራጨት እና ከፊቱ የሚገኘው የአጥቂ አማካይ የፈጠራ ሂደት እንዲረዳው መገኘት ባለበት የተጋጣሚ የመከላከል ሳጥን አካባቢ እንዲገኝ የመርዳ ሚና ትላንትናም የተሳካ አልነበረም፡፡ ጋቶች ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በተጋጣሚ የአማካይ ተሰላፊዎች አማካይነት በዙሪያው በሚፈጠርበት ጫና ምክንያት ተረጋግቶ ሚናውን መወጣት አልቻለም፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች ሽመልስ ከተቃራኒ ቡድን የመከላከል ክፍል ርቆ ወደ ጋቶች ቀርቦ ሲታይ ነበር፡፡ ይህ ችግር ወደ ማጥቃት በሚደረገው ሽግግር ላይም በኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ከሁዋላ ተመስርተው የተጋጣሚ የመከላከል ክልል ውስጥ ሳይገቡ ለሚቋረጡ ኳሶችም ምክንያት ሆኗል፡፡ እንዲሁም ሁለቱ አጥቂዎች ከሽመልስ ጋር የነበራቸውን ርቀት እያሰፋው ለተጋጣሚያችን አማካዮች ኳስን የማቋረጥና የማደራጀት ስራቸውን አቅልሎላቸው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሽመልስ ከሁለቱ የመስመር አማካዮች ጋርም የነበረውን ቅንጅት ለመመስረት ሰፊ ሜዳ እንዲያካልልም አድርጎታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በማጥቃት ላይ የሚታየውን መበታተን ለማገዝ ጋቶች ወደፊት ጠጋ በሚልበት ወቅትና ኳስ በምንነጠቅበት ጊዜ ተጋጣሚ ወደ መልሶ ማጥቃት ሲገባ ጋቶች ብቸኛው የተከላካይ መስመሩ ሽፋን እንደመሆኑ መጠን በመከላከል ሽግግር ቦታውን ሳይዝ የኮንጎ ተጨማቾች አደጋ የሚፈጥሩበት እድልን ሲያገኙ ነበር ከነዚህም አጋጣሚዎች አንዱ ጎል ሆኗል፡፡ (ምስል 3)

ጋቶች ከማጥቃት ወደ መከላከል የሚያደርገውን ሽግግር ጨርሶ ቦታውን ላይ ባለመገኘቱ ሳላዲን ቦታውን ትቶ ኳስ ለማስጣል የሞከረበትና በስዩምና በአስቻለው መሀል የተፈጠረውን ክፍተት ቢፉውማ (13 ቁጥር) ሲጠቀምበት፡፡
ከላይ ለተጠቀሱት የመሀል ሜዳው የመሳሳት ችግሮች መናሻ የሆነው የጋቶች ፓኖም ሚና ሊጤን የሚገባው ነው፡፡ እዚህ ጋር እንደመፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ጋቶችን ትላንት ቀይሮት ከገባው ከበሀይሉ ጋር ማጣመር ነው፡፡ በሀይሉ በቦታው በመከላከለያ ከሚካኤል ደስታ ጋር ጥሩ ቅንጅት አለው፡፡ እንደመፍትሄ ሀሳብ የጋቶችና የበኃይሉ አብሮ መሰለፍ የሚከተሉትን ጥቅሞች ያስጠናል፡፡
1.ለሽመልስ የበለጠ ወደፊት መጠጋትና ሙሉ በሙሉ ወደፈጠራው ማተኮር ይረዳል፡፡ ይህም ከመስመር አማካዮቹም ሆነ ከፊት አጥቂው ጋር ለመቀራረብ እና ኳሶችን ለመስጠት እና ለመቀበል እንዲሁም በራሱ ወደ ግብ ለመሞከር የበለጠ ወደተጋጣሚ ግብ እንዲቀርብ ይረዳዋል (ምስል 6ን ይመልከቱ) ፡፡
2.ለቡድኑ ተከላካዮች ሽፋን በአግባቡ የሚሰጥ እና በመከላከል ሽግግር ጊዜ የማይበታተን ቅርፅ የያዘ አማካይ መስመርን ለመፍጠር ያስችላል፡፡ በተለይም የኮንጎዎች ሁለቱ ወሳኝ የመስመር ጥቃቶችን ከመስመር አማካዮቻችን እና ተከላካዮቻችን በተጨማሪ በግራም በቀኝም በሚገባ የሚሸፍን የመሀል ሜዳ አማካይ እንዲኖረን ያደርጋል
(ምስል 5 ይመልከቱ)
3.ወደ ማጥቃት በሚደረግ ሽግግር ወቅት ጋቶች እስከ ተጋጣሚ ሳጥን ድረስ የመጠጋት ሚና ቢኖረው እንኳን ከበስተኋላው የሚተወው ቦታ በበኃይሉ መሸፈን ይቻላል፡፡ ይህም የጋቶችን ተክለሰውነት እና ኳስ የማቀበል ስኬት እንዲሁም ከርቀት ግቦችን የማስቆጠር ብቃት ያለስጋት ለመጠቀም ያስችላል
(ምስል 6 ይመልከቱ)
4.ከመሀል ሜዳው ተገንጥለውና ለተጋጣሚ ተከላካዮች ምቹ ሆነው የሚቆሙትን ሁለት አጥቂዎቻችንን ቁጥር ወደ አንድ ዝቅ በማድረግ ከበስተሁዋላው በሁሉም አቅጣጫዎች የጎል እድል የሚፈጥርለትና እና ወደሱ የተጠጋ የአማካይ ክፍል የሚኖረውን ስል አጥቂ ይፈጥራል፡፡ የሚያገኘውንም የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን ያሰፋለታል
(ምስል 6)
5.የመሀል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫን በመፍጠር የተጋጣሚን የመሀል አማካዮች የጎል እድል ፈጠራን ለማጨናገፍ እንዲሁም የራስን የማጥቃት ሂደት ለማስጀመር ይረዳል፡፡
6.ጋቶች በማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት ከጎንዮሽ እንቅስቃሴ ይልቅ ቀጥተኛ አጨዋወትን ይጠቀማል፡፡ በኃይሉ በ4-2-3-1 ፎርሜሽን ከአጠገቡ ቢሰለፍ በጎንዮሽ እንቅስቃሴ የመስመር ተከላካዮችን እና አማካዮች የሚረዳበት እድል ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪም ጋቶች ከግብ ክልላችን ሳጥን እስከ ተጋጣሚ ሳጥን ድረስ በነፃነት የመጫወት እና የግብ እድሎችን የመፍጠር እድል ያገኛል፡፡ ከጋቶች ጎን የሚሰለፈው ሽመልስ (ኤልያስ) የበለጠ ነጻነት እና የኳስ አቅርቦት ያገኛል፡፡ ይህ አሰላለፍ ከንፅፅር በመስመር የሚደረጉ የማጥቃት ሽግግሮችን የሚረዳ በመሆኑ ለመስመር ተከላካዮቻችንም የማጥት ነጻነት ይፈጥራል፡፡
በአጠቃላይ የመሃል ሜዳ ችግራችንን በዚህ መልኩ ለመፍታት ከሞክርንና በትላንቱ ጨዋታ የታየብንን የቆሙ ኳሶችን የመከላከል ከፍተኛ ችግር ካሻሻልን ምንም እንኳን ከተጋጣሚችን ያነሰ የእግር ኳስ ደረጃና የተጨዋቾች ጥራት ላይ ብንገኝም ከነገ በስቲየው ጨዋታ ውጤት ይዘን መመለስ የምንችልበት አጋጣሚ መፍጠር እንችላለን፡፡
የቆሙ ኳሶች የመከላከል ችግር
በትናንትናው ጨዋታ ለሶስተኛው ጎል መቆጠር ምክንያት የነበረው የማዕዘን ኳስ ሲሻማ በኢትዮጵያ የግብ ክልል ውስጥ የነበረው የተጨዋቾች ቁጥር ኢትዮጲያ 8-5 ኮንጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ጎሉን ያስቆጠረውን ንዲንጋ (8 ቁጥር) ን የያዘው ተጨዋች አልነበረም፡፡ ቡድኑ በቆሙ ኳሶች ላይ ያለውን የአቋቋም እና የተጫዋች አያያዝ (Man Marking) ማሻሻል ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም በአካል ብቃት ከኛ ከሚሻሉ ቡድኖች ጋር ስንጫወት የቆሙ ኳሶችን ለመከላከል ከቁጥር ብልጫ በዘለለ በዞን የመከላከል (Zonal Marking) ክህሎትን ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
መልካም እድል ለብሄራዊ ቡድናችን!