ዛሬ በተካሄዱት 2 የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ለ2015 የሴካፋ ውድድር ፍፃሜ ያለፉት ቡድኖች ተለይተዋል፡፡ አስተናጋጇ ኢትዮጵያም ከግማሽ ፍፃሜው ተሰናብታለች
ቀትር 6፡45 የተጀመረው የሩዋንዳ እና ሱዳን ጨዋታ መደበኛው 90 ደቂቃ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት የተጠናቀቀ ሲሆን በተሰጠው ተጨማሪ 30 ደቂቃ 1-1 አቻ ሆነው ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት አምርተዋል፡፡
በ18ኛው ደቂቃ አብዱልጋድር ቡባካር በፈፀመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ ለቀሪዎቹ 100 ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋች የተጫወተችው ሱዳን በጭማሪው ሰአት 10ኛ ደቂቃ ላይ አጣሂር ኤል ጣሂር ባስቆጠረው ግብ መምራት ችለው ነበር፡፡ ጄን ባፕቲስቴ በ25ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ግብ ግን ሩዋንዳን አቻ አድርጎ ወደ መለያ ምቱ እዲየመሩ አስችላለች፡፡
በተሰጡት የመለያ ምቶች ሩዋንዳ 4-2 በማሸነፍ ለ2015 ሴካፋ ፍፃሜ መድረሷን ስታረጋግጥ ከሩዋንዳ በኩል ተቀይሮ የገባው ኢሴ ሶንጋ ተቀይሮ በገባ 30 ሴኮንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአደገኛ አጨዋወት በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱ አስገራሚ ሆኗል፡፡
የሱዳኑ ፋሮጌ አብደላ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
በ9፡30 የተጀመረው የኢትዮጵያ እና የዩጋንዳ ጨዋታ በመደበኛው እና በተጨማሪ 30 ደቂው ግብ ባለማስተናገዱ በመለያ ምቶች ክሬኖቹ 5-3 አሸንፈው ለፍፃሜ አልፈዋል፡፡
ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት በዚህ ጨዋታ ኢትዮጵያ ካለፉት ጨዋታዎች በተሻለ ተንቀሳቅሳለች፡፡ በተለይም የተከላካይ መስመሩ ጥምረት የቡድኑ ጥንካሬ ሆኖ አምሽቷል፡፡
ጨዋታውን ለመለየት በተሰጡት የመለያ ምቶች የኢትዮጵያ የመጀመርያ ፍፁም ቅጣት ምት መቺ የሆነው ጋቶች ፓኖም ሲያመክን አስቻለው ፣ በኃይሉ እና ኤልያስ ወደ ግብ ቀይረዋል፡፡ ከዩጋንዳ በኩል የተመቱት ሁሉም ፍፁም ቅጣት ምቶች ወደ ግብነት ተቀይረዋል፡፡ ዩጋንዳም 5-3 አሸንፋ ወደ ፍፃሜው አልፋለች፡፡
የብሄራዊ ቡናችን አማካይ ኤልያስ ማሞ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል፡፡
የ2015 ሴካፋ በመጪው ቅዳሜ ሲጠናቀቅ ለደረጃ አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ከ ሱዳን ይጫወታሉ፡፡ በፍፃሜው ደግሞ ዩጋንዳ ከ ሩዋንዳ ይፋለማሉ፡፡