አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በሽረ እንዳሥላሴ የሚገኙ አካዳሚዎችን ጎበኙ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጠኝ ሆነው ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ክልሎች በመሄድ የታዳጊ ፕሮጀክቶችን እየጎበኙ የሚገኙት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በትናትናው ዕለት በሽረ ከተማ የሚገኙ አካዳሚዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ስሑል ሽረ ከመከላከያ ያደረጉትን ጨዋታ በሽረ ስታድየም በመገኘት የተከታተሉት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በትናትናው ዕለት የተለያዩ አካዳሚዎችን ሲጎበኙ አርፍደዋል። በሱሑል ሽረ ዋናው ቡድን ስር የሚገኙትን ከ20 ፣ ከ17 እና ከ15 ዓመት በታች ቡድኖችን ጎብኝተዋል። በመቀጠል ዘ ይርጋ የተሰኘ ግለሰብ ከ10-15 ዓመት ውስጥ ያሉ ታዳጊዎችን በመያዝ እያሰለጠነበት የሚገኝውን የታዳጊዎች ፕሮጀክት የተመለከቱ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በከተማው የሚገኙ በተለያዩ የእድሜ ዕርከን የሚገኙ የታዳጊ ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል።

ከጉብኝታቸው በኃላ በሽረ ስለነበራቸው ቆይታ አስመልክቶ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሲናገሩ ” በሄድኩባቸው የሽረ ፕሮጀክቶች የብዙዎቹ ጥያቄዎች የሙያ ማሻሻያ ዘመኑን (ጊዜውን) የሚጠይቅ የአሰልጣኞች ስልጠና እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ፤ በቀጣይም ከቴክኒክ ኮሚቴው ጋር በመነጋገር አንድ ነገር እናደርጋለን። በተለይ በጣም የተገረምኩት እና በግሌ ያስደሰተኝ ነገር ፕሮጀክቶችን ከተጫዋቾች ወላጆች ጋር ያስተሳሰሩ መሆኑ ነው። የልጆቹን የተጫዋችነት ብቻ ሳይሆን የቀለም ትምህርታቸውን ከወላጅ ጋር በመሆን ይከታተላሉ ፣ ይቆጣጠራሉ በእግርኳሱ ብቻ ተስበው በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡትን ይመክራሉ ፤ ምክሩን የማይቀበሉ ከሆነ ከፕሮጀክቱ እስከ ማስወጣት ይደርሳሉ። ይህ ከተጫዋችነት ባሻገር ጥሩ ዜጋ ለመፍጠር መልካም ሆኖ አግኝቸዋለው። ለተደረገልኝ መልካም አቀባበል ለሽረ እግር ኳስ አመራሮች እና የስፖርት ቤተሰቡ ምስጋና እያቀረብኩ በቀጣይ መሰል ክልሎች በመሄድ አቅሜ የፈቀደውን አደርጋለው ” ብለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡