አዲስ አበባ የ2020 የፊፋ ኮንግረስን እንድታስተናግድ ተመርጣለች

የእግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪው ፊፋ በቀጣይ ዓመት ግንቦት ወር ላይ የሚደረገውን 70ኛው የፊፋ ስብሰባ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧን በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በተደረገው 69ኛው ስብሰባ የመዝግያ ስነ ስርዓት ይፋ አድርጓል።

የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በተጠናቀቀው ወር የዓለም ሚዲያ ነፃነት ቀንን ለተከታታይ ሦስት ቀን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገዷ እና በ2020 ለሚደረገው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም እንድታዘጋጅ በመመረጧ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የተሰጧትን ስብሰባዎች በሚገባ እየተወጣች መሆኑ ለኮንግረሱ ተመራጭ አድርጓታል ተብሏል።

በተያያዘ የፊፋ ዜና በፈረንሳይ እየተካሄደ በሚገኘው የፊፋ ኮንግረስ ጂያኒ ኢፋንቲኖ በድጋሚ አስከ 2023 የፊፋ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የ2018 ሪፖርት እና ፋይናንሻል ሪፖርት ከመቅረቡም ባሻገር ለ2020 የሚሆን በጀት በጥልቀት ገምግመው አፅድቀዋል። በጠቅላላም 810 ሚሊዮን ዶላር ለእግር ኳስ ፈሰስ እንደሚደረግም ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡