የዓምናው የፕሪምየር ሊግ “ዋንጫ” የት እንደሚገኝ ያውቃሉ?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው የውድድር ዘመን በአወዛጋቢው ሁናቴዎች ታጅቦ ወደ መገባደጀው ላይ እንገኛለን። 

ሊጉ የሀገሪቱ ከፍተኛው ውድድር ቢሆንም የጨዋታዎቹ እና በዙርያው የሚገኙት ነገሮች የወረደ የጥራት ደረጃ፣ ለአሸናፊው የሚበረከተው ሽልማት እና ቻምፒዮን በመሆኑ የሚያገኛቸው የፋይናንስ እና ሌሎች ጥቅሞች በውድድር ዓመቱ ከተጫዋቾች ዝውውር ለደመወዝ፣ አስተዳደራዊ ወጪዎች እና ለመሳሰሉት ከሚያፈሱት ገንዘብ ጋር በእጅጉ የማይመጣጠን ነው። የሚበረከተው ዋንጫም “ተራ” በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ከስፖርት ሱቆች ተገዝቶ የሚሰጥ፣ የተለየ መለያ የሌለው እና በየዓመቱ የሚቀያየር በመሆኑ ዋንጫውን ትርጉም የለሽ ያደርገዋል።

በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ቡድኖች የሚያስመዘግቧቸው ስኬቶች ከዕለት ደስታ ያለፈ ትርጉም እንዳይሰጣቸው ሲያደርጋቸው እያስተዋልን እንገኛለን። ለዚህም እንደ ዓብነት የምንመለከተው የዓምናው የፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ጅማ አባ ጅፋር የተበረከተለት ዋንጫን ነው። 

ዋንጫው በክለቡ ፅልፈት ቤት የሚገኝ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ይልቁንም በሐምሌ ወር አጋማሽ ባዘጋጁት አንድ ዝግጅት ላይ በጅማ ከተማ በሚገኝ አንድ ሆቴል ተረስቶ እና አስታዋሽ አጥቶ በፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) ተቀምጦ ይገኛል። የሆቴሉ ሰራተኞች ሁኔታውን ተመልከትው ክለቡ ዋንጫውን እንዲወስድ ቢጠይቁም እስካሁን ወሳጅ አጥቶ በሆቴሉ እንደሚገኝ ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡