የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ሦስተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በባቱ ከተማ እየተካሄደ ሦስተኛ ቀኑን ሲይዝ አዲስ አበባ ፖሊስ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል። ላስታ ላሊበላ፣ መቱ ከተማ እና ቂርቆስ ክ/ከተማም አሸንፈዋል።

03:00 ላይ ኮልፌ ቀራንዮ ከ አዲስ አበባ ፖሊስ ያደረጉት የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ፖሊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ኮልፌ ቀራንዮ አራፊ በመሆኑ በዛሬው ዕለት የመጀመርያውን ምድብ ጨዋታ ሲያደርግ አዲስ አባባ ፖሊስ የምድቡ የመጀመርያው ጨዋታው ላስታ ላሊበላን 3-1 አሸንፎ ነው የዛሬውን ሁለተኛ ጨዋታ ያደረገው።

ጥሩ ፉክክር ቢደረግበትም ጎል የሚያስቆጥሩ ጠንካራ አጥቂዎች በሁለቱም ቡድኖች ባለመኖራቸው የጎል ሙከራ በተደጋጋሚ መመልከት አልቻልንም። ኮልፌ ቀራንዮዎች በ5ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳ የተጣለን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ የግብጠባቂው አቋቋም አይቶ ቺፕ ቢያደርጋትም ለጥቂት በግቡ አናት በወጣበት ሙከራ የጎል አጋጣሚ ሲፈጥሩ 17ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ የግራ መስመር አጥቂ እዮብ ገ/ማርያም በሚገርም ፍጥነት ከራሱ የሜዳ ክፍል አንስቶ ኳሱን እየገፋ ተከላካዮችን በመቀነስ አመቻችቶ ያቀበለውን እዮብ ደረጄ ወደ ጎልነት በመቀየር ፖሊሶችን መሪ አድርጓል። ለዚህች ጎል መቆጠር የእዮብ ገ/ማርያም አስተዋፆ ከፍተኛ ነበር።

ጥሩ እግርኳስ የሚጫወቱት ፖሊሶች ኳሱን አደራጅተው ወደ ፊት በመሄድ ተጨማሪ ጎል መሆን የሚችሉበትን ዕድል እዮብ ገ/ማርያም አግኝቶ በቀጥታ መሬት ለመሬት ቢመታውም ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል። ጨዋታው በጠንካራ ፉክክር በጎል ሙከራ ያልታጀበ ሆኖ ቀጥሎ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ ለእረፍት ወጥተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ፊት የማይሄድ የኳስ ንክኪ ብቻ በዝቶ ሲታይ በዕለቱ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው የፖሊሶቹ አጥቂ እዮብ ገ/ማርያም ወደ ጎል ከሞከረው ኳስ ውጭ ሌላ የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በአዲስ አበባ ፖሊስ 1–0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ ተከታታይ ሁለት የምድብ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻሉት እና የምድቡ መሪ የሆኑት ፖሊሶች ከወዲሁ ስምንት ውስጥ ለመግባት ያላቸውን እድል አስፍተዋል።

05:00 በቀጠለው ሌላኛው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ያገኙትን እድሎች በአግባቡ አለመጠቀማቸው ዋጋ የከፈሉት ቢሸፍቱዎች በላስታ ላሊበላ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል። ቢሸፍቱ ከተማ የመጀምርያ የምድብ ጨዋታውን ጎፋ ባሪንቼን ከመመራት ተነስቶ በጥሩ ብቃት 3-1 ማሸነፉና ላስታ ላሊበላ በደካማ አቋም በአዲስ አበባ ፖሊስ 3-1 መረታቱን ተከትሎ የጨዋታው አሸናፊነት ግምት ለቢሸፍቱ ከተማ ቢሰጥም ላስታ ላሊበላ ግምቶችን ሁሉ ፉርሽ አድርጎ አሸንፎ ወጥቷል።

ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ወስደው በተደጋጋሚ የላሊበላዎችን በር ሲፈትሹ የዋሉት ቢሾፍቱዎች ጥቃታቸውን መሰንዘር የጀመሩት በ7ኛው ደቂቃ ወደ ፊት በተጣለለት ኳስ አማካዩ አምሀ አበበ ነፃ ኳስ አግኝቶ ግብጠባቂው እንደምንም ተንሸራቶ ባዳነበት እንዲሁም በሁለት አጋጣሚ ድንቅነህ ከበደ ሳይጠቀምበት በቀራቸው እድሎች ነበሩ። ልምድ ችግር ካልሆነ በቀር ጥሩ ኳስ መጫወት የሚችሉት ላስታ ላሊበላዎች ከመጀመርያ ጨዋታቸው በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን 23ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ፀጋዬ ከርቀት በቮሊ የመታውና በግቡ አናት ለጥቂት የወጣበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

ከእረፍት መልስ በ47ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱ ተከላካይ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ የላስታው አጥቂ ማቲያስ ሹመት የግብጠባቂውን አቋቋም ዓይቶ የመታው ኳስ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ኳስ በእጅ በመነካቱ ላስታዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አስማማው በስፋት ወደ ጎልነት በመቀየር ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል። ከዚህ ጎል መቆጠር በኃላ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ የላስታን የግብ ክልል በሁሉም የሜዳ ክፍል ወረው የተጫወቱት ቢሸፍቱዎች እጅግ በማይታመን ሁኔታ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን አምክነዋል። በቢሸፍቱ በኩል በዛሬው ዕለት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ሙሴ እንዳለ የርቀት ጠንካራ ኳስ የግብ አግዳሚ ሲመልስበት የተገኘውን ኳስ በድጋሚ በጋሻው ክንዴ ነፃ ኳስ አግኝቶ ወደ ሠማይ የሰደዳት ጎል መሆን የምትችል የምታስቆጭ ዕድል ነበረች። እያዩ ሲሳይ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ያመከነው ፣ አብዱልአዚዝ አማን በተመሳሳይ የሳተውም ሌሎች ቢሸፍቱን ዋጋ ያስከፈሉ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ። ላስታዎች በከፍተኛ የመጫወት ፍላጎት መረባቸውን ላለማስደፈር በከፈሉት ዋጋ እና በግብ ጠባቂያቸው ፍስሀ ረዲ ብቃት ታግዘው ጨዋታውን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።

07:00 በቀጠለው የዛሬው ሦስተኛ ጨዋታ ዳሞት ከተማ ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ ጥሩ ፉክክር አድርገው በቂርቆስ ክ/ከተማ 3–2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሁለቱም ቡድኖች በመጀመርያ የምድብ ጨዋታቸውን ሽንፈት አስተናግደው እንደመምጣታቸው ጨዋታዉን አሸንፈው ለመውጣት ብርቱ ፍኩክር ያደርጋሉ የተባለውን ግምት ሜዳ ላይ አሳይተውን ወጥተዋል። ጎል መቆጠር የጀመረው ገና በ5ኛው ደቂቃ ሲሆን በጥሩ ቅብብል በግራ መስመር ገብተው የተሻገረን ኳስ በግሩም ሁኔታ በባህርዳር ፕሮጀክት ያደገው ወጣቱ አጥቂ ሐብታሙ ገደፋው ግሩም ጎል አስቆጥሮ ነበር ቂርቆሶች ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ፉክክሩ አይሎ ቀጥሎ ቂርቆሶች በድጋሚ በ26ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን በምናቀው አማካዩ ቢንያም ገሠሠ አማካኝነት በግምት ከ17 ሜትር ርቀት ባስቆጠረው አስገራሚ ጎል ልዩነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገውታል። አልፎ አልፎ የጎል ዕድል ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ዳሞቶች 45ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተላከውን ኳስ ታዘባቸው ዳኜ አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ዳሞቶች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው ጎል ፍለጋ የተጫኑ ሲሆን በተለይ በሁለቱ የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ምርጥ ብቃቱን በውድድሩ እያሳየ የሚገኘው ባለ ግራ እግሩ ፈጣሪ ተጫዋች አብርሃም አሠፋ አማካኝነት በጥሩ መንገድ ወደ ፊት በመግባት የቂርቆሱ ግብጠባቂው ዮናስ ጉደታ ያዳነበት ሲሆን ከሁለት ደቂቃ በኃላ በ55ኛው ደቂቃ ከቀኝ ወደ ግራ ተከላካዮችን እያታለለ ቆርጦ በመግባት ኳሱን አመቻችቶ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ምርጥ ጎል አስቆጥሮ ዳሞቶችን ሁለት አቻ ማድረግ ችሏል።

በጎል ታጅቦ የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 66ኛው ደቂቃ ላይ በዳሞት ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ሐብታሙ ገደፋው ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ ቂርቆሶችን መሪ አድርጓል። በቀሩት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ጎል ፍለጋ ነቅለው የወጡት ዳሞቶች ራሳቸውን ለቂርቆስ የመልሶ ማጥቃት አጋልጠው የነበረ በመሆኑ ቂርቆሶችም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ተጨማሪ ጎል የሚያስቆጥሩበትን እድል ሳይጠቀሙ ጨዋታው በቂርቆስ. 3–2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ምንም እንኳ ውጤቱ በርካታ ኪሎ ሜትር አቋርጠው የመጡትን የዳሞት የልብ ደጋፊዎችን ያስደሰተ ባይሆንም በስታዲዮም ውስጥ ይሰጡት የነበረው የድጋፍ ሁኔታ የዕለቱ ድምቀት ነበር።

09:00 የተካሄደው የዛሬ ውሎ የመጨረሻ አራተኛ ጨዋታ ለ77ደቂቃ በጎዶሎ ልጅ ተጫውተው የወጡት መቱ ከተማዎች ራያ አዘቦን 2–1 አሸንፈው ወጥተዋል። አራፊ የነበረ በመሆኑ የምድቡን የመጀመርያ ጨዋታ ያልተጫወተው መቱ ከተማን በመጀመርያ ጨዋታው ብልጫ ወስዶ ዳሞት ከተማን 2-1 አሸንፎ ከመጣው ራያ አዘቦ ጋር ያገናኘው ጨዋታ የመቱን ሁለት ጎሎች ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት በኃላ እስራኤል ይገዙ ሲያስቆጥር የራያ አዘቦን የማስተዛዘኛ ጎል አምበሉ ሙሉ ካሕሳይ አስቆጥሯል። በመቱ ከተማ በኩል በጨዋታው 17ኛ ደቂቃ ጉዲና ከበደ ተጫዋች በክርኑ በማታቱ ምክንያት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።

የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ነገ እረፍት ያደርግና ሐሙስ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ይቀጥላል

03:00 መቱ ከተማ ከ ጋሞ ጨንቻ

05:00
ራያ አዘቦ ከ ቂርቆስ ክ/ከተማ

07:00
ኮልፌ ቀራንዮ ከ ከጎፋ ባሬንቼ

09:00
አዲስ አበባ ፖሊስ ከ ቢሾፍቱ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡