ሀዲያ ሆሳዕና ከዋና አሰልጣኙ ጋር ይቀጥላል

የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ አሸናፊ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ሀዲያ ሆሳዕና የዋና አሰልጣኙ ግርማ ታደሰን ውል ለተጨማሪ ዓመት ለማደስ ከስምምነት መድረሱን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል። 

አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ የምድብ ሐ የበላይ ሆኖ በማጠናቀቅ በድምር በ48 ነጥቦች አሸናፊ እንዲሆን የረዱት ሲሆን ክለቡ ከ2 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግም አስችለዋል። አሰልጣኙ ውላቸው በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ የተጠናቀቀ ቢሆንም ከክለቡ ጋር ባደረጉት ድርድር ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው የ2012 የውድድር ዘመንን በክለቡ የሚያሳልፉ ይሆናል። 

በዝውውር መስኮቱ እስካሁን ምንም እንቅሴቃሴ ያላደረገው ሀዲያ ሆሳዕና ከነገ ጀምሮ የአዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ይፋ እንደሚያደርግ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መላኩ ማዶሮ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑ በ2012 በተሻሻለ የሜዳ ይዘት ብቅ ለማለት በማሰብ የሳር ተከላ፣ የተጨማሪ ተመልካች መቀመጫዎች ግንባታ ማከናወን እና የመሳሰሉት ተያያዥ ጓዳዮች ላይ ጠንክሮ እየሰራ እንደሆነ አያይዘው ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡