መቐለ 70 እንደርታ የቻምፒየንስ ሊግ የሜዳ ጨዋታውን የት ያደርግ ይሆን? 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነው መቐለ 70 እንደርታ በ2019/20 የቻምፒንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ ከኢኳቶርያል ጊኒው ካኖ ስፖርት አካዳሚ ጋር መደልደሉ ይታወቃል።

ክለቡ የመጀመርያውን ጨዋታ የሚያደርገው ከሜዳው ውጪ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ሊያደርግበት ያሰበው የትግራይ ስታዲየም የካፍ እውቅና እስካሁን ባለማግኘቱ በእድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባው አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ሊያደርግ እንደሚችል ተገልጿል።

የመቐለ ምክትል ፕሬዝዳንት ልባርጋቸው ምህረቱ ለሶከር ኢትዮጵያ የአበበ ቢቂላ ስታዲየምን እንዳስመዘገቡ ገልፀው እስከ መልሱ ጨዋታ ድረስ የትግራይ ስታድየም በካፍ ዕውቅና አግኝቶ በሜዳቸው እንደሚጫወቱ ተስፋ አድርገዋል። “ጨዋታውን በሜዳችን እና በደጋፊ ፊት ነው ለማድረግ ያሰብነው። ይህንን ለማድረግም ከዚህ ቀደም የካፍ ተወካዮች መጥተው የሰጡት አስተያየት እና መሟላት ያለበትን ጉዳዮች በነገሩን መሠረት እያዘጋጀን ነው። በሚቀጥለው ሳምንት መሟላት ያለባቸውን ነገሮች አጠናቀን የካፍ ተወካዮችን በመጥራት እንዲመለከቱ፤ ፍቃድም እንዲሰጡን ጠንክረን እየሰራን ነው። የአበበ ቢቂላን ስታዲየምን ያስመዘገብነው በካፍ እውቅና ያለው ሜዳ ማስመዝገብ ስላለብን ነው። ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የአዲስ አበባ ስታዲየም ለጨዋታ ምቹ ላይሆን ስለሚችል አበበ ቢቂላን ነው የመረጥነው። በአጠቃላይ ግን ከውድድሩ በፊት የሚጠብቅብንን በቶሎ አጠናቀን በሜዳችን ነው ይህን ጨዋታ ለማድረግ ያሰብነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡