ፋሲል ከነማ የሁለት ተጫዋቾችን ውል ሲያደስ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ መልቂያ አስገብተዋል

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ፋሲል ከነማ የሁለት የውጪ ዜጎቹ ኮንትራትን ሲያራዝም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አስታውቋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት መጀመሪያ ክለቡን በአንድ ዓመት ውል የተቀላቀለው ናይጄርያዊው ኢዙ አዙካ ጥሩ የሚባል የውድድር ዓመት ያሳለፈ ሲሆን 10 የፕሪምየር ሊግ ግቦችንም አስቆጥሯል። ፋሲል ከነማም ካሳለፈው ጥሩ የውድድር ዓመት በመነሳት ለተጨማሪ የአንድ ዓመት ውሉን ለማደስ ተስማምቷል። 

በመሀል ተከላካይነት እና በአማካይ ስፍራ በወጥነት ግልጋሎት ያበረከተው ከድር ኩሊባሊም በተጨማሪ አንድ ዓመት ውል ክለቡ ጋር ለመቀጠል የተስማማ ሲሆን ይህ ተጫዋች ባለፈው ክረምት ደደቢትን በመልቀቅ ዐፄዎቹን እንደተቀላቀለ ይታወሳል።

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀሪ አንድ አመት ኮንትራት ቢኖራቸውም ለክለቡ ባስገቡት ደብዳቤ መሰረት ባጋጠማቸው የቤተሰብ ችግር ክለቡን መልቀቅ እንደሚፈልጉ በመግለፅ ለክለቡ ደቡዳቤ ማስገባታቸውን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። ክለቡን የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ እንዲሆን የረዱት አሰልጣኙ በካፍ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከታንዛኒያው አዛም ጋር እስከሚያደርጉት ጨዋታ ድረስም እንደሚቆዩ አሳውቀዋል። ፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ በተጫዋቾች ዝውውር እና የነባሮችን ውል በማራዘም ሥራ ላይ እንዳሉ ገልጾ አሰልጣኙን ለማቆየት ጥረት እያደረገ እንደሆነም ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡