ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምቷል

ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ሀዲያ ሆሳዕና ከሦስት ተጫዋቾች ጋር እንደተስማማ የክለቡ አሰልጣኝ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

ደቡብ ፖሊስን ዘንድሮ በአምበልነት የመራው የመሀል ተከላካዩ ደስታ ጊቻሞ ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ለመቀላቀል ከስምምነት ከደረሱት መካከል ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ለረጅም ዓመታት በጉዳት ከሜዳ ከራቀ በኋላ ዳግም ወደ እግርኳስ ተመልሶ በ2010 ከደቡብ ፖሊስ ጋር ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደግ ችሏል። ከአንድ ዓመት በኋላም ከአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል።

ሌላኛው ወደ ቀድሞ አሰልጣኙ ያመራው ተጫዋች ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ብሩክ ኤልያስ ነው፡፡ በ2009 ከሀዋሳው “ካሣሁን የእግር ኳስ ቡድን” ከተገኘ በኋላ በደቡብ ፖሊስ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ቆይታን ያደረገ ሲሆን የ2010 የከፍተኛ ሊግ ኮከብ ተጫዋች መሆንም ችሏል። ወጣቱ አጥቂ ለሆሳዕና የማጥቃት አማራጭ ያሰፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሦስተኛው ወደ ሆሳዕና ለማምራት የተስማማው ተጫዋች አብዱልሰመድ ዓሊ ሆኗል። ከኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት (ኢኮስኮ) ድቻን ከተቀላቀለ በኋላ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በወላይታ ድቻ በበርካታ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት ተሰልፎ መጫወት የቻለው ተጫዋቹ እንደ ሁለቱ ተጫዋቾች ሁሉ የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት የአንድ ዓመት ውል እንደሚፈራረም አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡