ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ሰባት – ክፍል ሁለት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 26ኛ ሳምንት መሰናዶ ስለ ብራዚል በሚያወሳው ምዕራፍ ሰባት ሁለተኛ ክፍል የጋሪ ኩርስችነርን ታላቅ አበርክቶ ይመለከታል ። 


W-M (3-2-2-3) ፎርሜሽንን ከአውሮፓ ወደ ብራዚል ለመውሰድ የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው በጄንቲል ካርዶሶ አማካኝነት ነበር፡፡ በወቅቱ ካርዶሶ ይህን ሃሳብ ከግብ ለማድረስ በኹለት መሰረታዊ ተግዳሮቶች እጅጉን ተፈተነ፡፡ አንደኛው ቀደም ሲል በእግርኳስ ተጫዋችነት አለማሳለፉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጥቁር የመሆኑ ጣጣ ያመጣበት በቀላሉ ተቀባይነት የማግኘት ችግር ሆነ፡፡ ታታሪው ጄንቲል ህይወቱን ለመምራት በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል፤ በጫማ ጠራጊነት፣ ሆቴል አስተናጋጅነት፣ በከተማ የኤሌክትሪክ ባቡር ሾፌርነት እና በዳቦ ጋጋሪነት የሙያ መስኮች ከተሰማራ በኋላ በመጨረሻ በንግድ መርከብ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረ፡፡ አዲሱ ሥራውም ወደ አውሮፓ የሚደረጉ የተከታታይ ጉዞዎች ዕድል ፈጠረለት፤ በዚህ ምክንያት ካርዶሶ በአውሮፓ ትርፍ ጊዜውን በሙሉ እግርኳስን ለመመልከት እንዳዋለ ይገመታል፡፡

ጄንቲል ኮርዶሶ በሒደት ቀንደኛ የእንግሊዝ እግርኳስ አድናቂ ወደ መሆን አዘነበለ፡፡ በእንግሊዝ ሳለም የኸርበርት ቻፕማን አርሰናል ን ሜዳ ላይ ሲተገብር ከጅምሩ የማየት አጋጣሚ እንዳገኘ ይመሰክራል፡፡ “የመላ-ጉዞዎቹን ታሪክ ማውጋት የሚወድና ከገጸ ባህሪ የላቀ ስብዕና የታደለ ሰው ነበር፡፡” ይላል ጸሃፊው ሶተር ስለ ካርዶሶ ሲያስብ፡፡ በእርግጥ እግርኳሳዊ ወጎቹ ለዛ እንዲኖራቸው ተብሎ የተቀባቡ ቢሆኑ እንኳ የብራዚላዊውን ታክቲካዊ ትንታኔዎች የማቅረብ አቅም ግን መካድ አይቻልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ጄንቲል በአውሮፓ ቆይታው የፎርሜሽኑን አተገባበር በጥልቀት ተመልክቷል፤ አማራጭ አቀራረቦቹን (Variants) አጢኗል፤ አቀራረቡ ከብራዚላውያኑ ስልት ሰፊ ልዩነት እንዳለውም ተረድቷል፡፡ ስለዚህም በወደፊቱ እግርኳስ ከፍተኛ ተዘውታሪነት እንደሚያተርፍ ገመተ።

ካርዶሶ ጊዜውን በባህር ስራውና በእግርኳስ መካከል ከፋፍሎ ለመጠቀም በሞከረባቸው የ1930ዎቹ ዓመታት የማሰልጠን እድል ገጥሞት ነበር፡፡ የካሪዮካ መንደር ትንሽ ቡድን በነበረው <ሲሪዮ ሊባኔዝ> W-M ፎርሜሽንን ተገበረ፤ እዚያው ሆኖ የሊዮኒዳስ እድገት ላይ ክትትል ማድረግ ጀመረ፡፡ ኔልሰን ሮድሪጉዌዝ የተባለው ዝነኛ ጸሃፊ-ተውኔት “ሊዮኒዳስ ትክክለኛው ብራዚላዊ ተጫዋች ነበር፡፡ ዕይታው፣ ፈጠራው፣ አይደክሜነቱ፣ የዋህነቱ እና ስሜታዊነቱ የሁሉም ብራዚላውያን ታላላቅ ተጫዋቾች መገለጫ ባህሪን ይወክላል፡፡” በማለት ስለ አጥቂው ጽፏል፡፡ ተጫዋቹ እንግሊዞች በW-M የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር የሚያሰልፉትን የመሃል አጥቂ (Centre-Forward) አይነት አልነበረም፡፡ በእርግጥ ቅርጽ (Shape) በቀጥታ ሊወሰድ አልያም ሊኮረጅ ይችላል፤ ዘይቤን (Style) መገልበጥ ግን ይበልጥ አስቸጋሪ ይመስላል፤ የሊዮኒዳስ ሚናም የዚህ ሐሳብ ማሳያ ይሆናል።

ሲሪዮ ሊባኔዝ የኮርዶሶን ግኝት በመላው ሃገሪቱ እንዲናኝ ለማስቻል የሚረዳ አቅም አልያዘም ነበር፡፡ ክለቡ “ትንሽ” በመሆኑ የአሰልጣኙን ፈጠራ ለብዙዎች የማሳየት በር ሊከፍት አልቻለም፡፡ በንጽጽር “ተለቅ” ያለ ክለብ ወደነበረው <ቤንሱኬሶ> ሊዮኒዳስን አስከትሎ ካመራ በኋላም ቢሆን ሐሳቡን በቀላሉ የሚቀበሉ ተመልካቾች ለማፍራት ተቸግሯል፡፡ ተጫዋቾች የቡድን ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት ኮርዶሶ የሶቅራጠስ፣ ሲሴሮና ጋንዲን ንግግሮች እየጠቀሰ ያነቃቃቸዋል፡፡ በብራዚል የእግርኳስ መዝገበ-ቃላት ውስጥም የተለያዩ ፍቺዎች እየሰጠ የራሱን አሻራ ማሳረፍ ችሏል፡፡ ለአብነት ያህልም ” ‘ጥሩ ተጫዋች ነው፡፡’ ለማለት ‘እባብ ነው፡፡’ ” ይል ነበር፡፡ ” ‘የሜዳ አህያ” ማለትም ” አስደንጋጭ ውጤት” ማስመዝገብ እንደሆነ ይገልጽ ነበር፡፡ ሶተር ግን ” ብዙዎች የካርዶሶን ታክቲካዊ ግንዛቤ በአግባቡ አልተረዱትም፡፡” ይላል፡፡

ምንም እንኳ እግርኳሳዊ እሳቤዎቹ ተገቢ ድጋፍ ከማግኘታቸው በፊት ህይወቱ ብታልፍም W-M ፎርሜሽን ብራዚል ውስጥ ሰፊ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከአውሮፓዊው ጋሪ ኩርስችነር የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ ባለሙያ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ” ኩርስችነር ብራዚል ሲደርስ ጄንቲል ስለ W-M ብዙ ይሰብክ ነበር፡፡ ነገር ግን ጄንቲል ካርዶሶ እውቀቱን በተግባር የሚያሳይበት እውቅናና ከፍ ያለ ክብር ተነፍጎታል፤ በእርግጥም <ፉትቦል ሲስተማ/Futebol Systema/> የተባለውን የአጨዋወት ሥርዓት ለመተግበር የሞከረው ኩርስችነር ነበር፡፡” ይላል በፍላሚንጎ ከኩርስችነር በፊት አሰልጣኝ የነበረና በኋላም እርሱን የተካው ፍላቪዮ ኮስታ ለአይዳን ሐሚልተን በሰጠው ቃለ ምልልስ፡፡

ብዙ ዕውቀት ይዞ ከሩቅ ሃገር የመጣ ብልህ ስደተኛ፣ እንደ ሁሉም ሃቀኛ ነቢያት በሃገሩ ያልተከበረ፣ በህይወት እያለ ምስጋና ያልተቸረው፣…. ኩርስችነር በብራዚል የአፈ ታሪክ ሰው የሚመስል ትርክት አለው፡፡ የቀደመ ዝና ሳይኖረው እና ከምንም ተነስቶ ታላቅ የእግርኳስ መምህር ለመሆን የበቃ  አሰልጣኝ ነበር፡፡ “እርሱ ሃንጋሪያዊ፣ ቼካዊ ወይም ቦህሚያዊ ስለመሆኑ እንኳ እውቀቱ አልነበረንም፡፡” ይላል በቴሌቪዥን የእግርኳስ ተንታኙ እና የፍላሚንጎ ክለብ ታሪክ ታላቁ ተራኪ ሮቤርቶ አሳፍ፡፡ እርግጥ ኩርስችነርን በሚመለከት የተፈጠረው ግራ መጋባት በቀላሉ ሊረዱት የሚቻል ነገር ነው፡፡ የሆነ ወቅት ላይ ከስሙ ሆሄያት (Kurschner) ውስጥ “R” እና “U” ቦታቸው ተቀያይሮ ተጻፈና “ኩርስችነር” የሚለው ዋነኛ ስያሜው በብራዚል “ክርስችነር” (Kruschner) በሚል ቃልና ድምጸት ተተካ፡፡ ይሁን እንጂ ማንም “ክርስችነር” ብሎ የድረገጽ ፍለጋ ቢያደርግ ምንም ዓይነት መረጃ አያገኝም፡፡

አሌክስ ቤሉስ <ፉትቦል> በተሰኘው መጽሃፉ መግቢያ ላይ “ብራዚል የማስረጃ እጦት የተጸናወታት ናት፤ ከፍተኛ የመረጃዎች ታዓማኒነት ችግር ይስተዋልባታል፤ በታሪክ፣ አፈታሪክ፣ ዲስኩር፣ ጭምጭታዎችና ሹክሹክታዎች የታጀለች ሃገር ናት፡፡” ሲል አስፍሯል፡፡ ይህ እንግዲህ የኩርስችነርን ምስጢራዊ ህልውና ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ይህ የሰውየው አለመታወቅ ብቻ የፍላሚንጎውን ፕሬዚደንት ጆዜ ባስቶስ ፓዲልሃ ክለቡ በካሪዮካ ግዛት ገናና እንዲሆን ያላቸውን ዓላማ ለማሳካት እንዲሁም አዲስ ስታዲየም የማስገንባት ውጥናቸውን ከዳር ለማድረስ ከፍተኛ በጀት የመመደብ ፍቃደኝነት ሲያሳዩ ኩርስችነር ላይ ለምን ቀልባቸው እንዳረፈ ስውሩ የአሰልጣኙ ማንነትን ፍንጭ አይሰጥም፡፡ ጆዜ ባስቶስ ምንም አይነት ዓላማ ይኑራቸው ኩርስችነርን ሲቀጥሩ የ<ዳኑቢያን እግርኳስ> ባህልን የተላመደ አሰልጣኝ በእጃቸው አስገብተዋል፤ ከዚህ በተጨማሪ ከዝነኛው ጂሚ ሆጋን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት መመስረት የሚያስችል ባለሙያ አግኝተዋል፡፡ ሆጋን የሃንጋሪ፣ ኦስትሪያና ጀርመን የእግርኳስ አባት እንደነበር በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ የብራዚሎች እግርኳስ አያት ስለመሆኑ ብዙም አልተወራም፡፡

ኩርስችነር የተወለደው በቡዳፔስት ነው፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ በMTK ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡ በ1904 እና 1908 ከክለቡ ጋር የሊግ ድሎችን አሳክቷል፤ ለብሄራዊ ቡድኑም በርካታ ጥሪዎች ቀርበውለት በዓለምአቀፍ ደረጃ ሃገሩን መወከል ችሏል፡፡ ዋነኛ የመጫወቻ ሚናው የግራ መስመር አማካይነት (Left-Half) የነበረ ቢሆንም አልፎ አልፎም መሃል ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ በኳስ ቁጥጥር ላይ በሚያሳየው የላቀ ብልሃትና ስልጡንነት እውቅናን አትርፏል፤ ኳስ በግንባር የመግጨት ችሎታውም በተለየ የሚጠቀስለት ተጫዋች ነበር፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ የመጨረሻዎቹ ጊዜያት በጄሚ ሆጋን የመሰልጠን እድል አግኝቷል፤ ሆጋን በ1918 የMTK ክለብን ሲለቅ መንበሩን ያስረከበው ለኩርስችነር ነበር፡፡ አሰልጣኙ ከቡድኑ ጋር ዋንጫ ማሸነፍ ቢችልም በMTK ከዓመት በላይ ሊቆይ አልወደደም፤ ክለቡን ለቆ ወደ ጀርመን አቀና፡፡

በጀርመን ከ<ስቱትጋርተር-ኪከርስ> ጋር መጠነኛ ስኬት አስመዘገበ፡፡ በ<ኑረንበርግ> ቆይታው ደግሞ ይበልጡን ውጤታማ ሆነ፤ የጀርመን ብሄራዊ ዋንጫንም አሸነፈ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ጥቂት ጊዜ በ<ባየር ሙዩኒክ> ከርሞ ክለቡ ” የምንጊዜውም ምርጥ ፍጻሜ ” በሚባለው ጨዋታ ከ<ኤስ.ቪ. ሃምቡርግ> ጋር ተፋልሞ ያሳካውን ድል ለመጋራት ቻለ፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወቱ የመጀመሪያ ዓመታት ኩርስችነር እንደ ጉትማን መረጋጋት ተስኖት ታይቷል፡፡ በመቀጠል ያመራው ወደ <ኤይንትራክት ፍራንክፈርት> ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እዚያም ብዙ አልሰነበተም፡፡ ሲውዘርላንድን ቀጣዩ መዳረሻው አደረገና <ኖርድስተርን ባዜል> የተሰኘውን ክለብ ተረከበ፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ቆይታው ቡድኑ ወደ ላይኛው የሊግ እርከን እንዲሻገር አገዘ፤ ነገር ግን የሲውዙን ክለብ ወዲያውኑ ለቀቀ፡፡ ከዚያም የሲውዘርላንድ ብሄራዊ ቡድንን ለፓሪሱ ኦሊምፒክ ለማዘጋጀት ለይስሙላ ብቻ ዋና አሰልጣኝ ከነበረው ሌላኛው እንግሊዛዊ ቴዲ ዳክዎርዝ እና ጄሚ ሆጋን ጋር ተቀላቀለ፡፡ ይህ የአሰልጣኞች ቡድን በፈረንሳይ ምድር በሲውዘርላንድ እግርኳስ ታሪክ እጅግ ትልቅ ተብሎ የሚጠቀሰውን ስኬት አስመዘገበ፤ ሆኖም ለፍጻሜ ቀርበው ቀደም ሲል ዋንጫውን ባሸነፈችው ኡሯጓይ ተረቱ፡፡

ኩርስችነር <ሽዋርዝ ዌይዝ-ኢሰን> የተባለውን ክለብ ለመያዝ በድጋሚ ወደ ጀርመን ቢመለስም እዚያም ብዙ አልከረመም፤ በ1925  የሲውዘርላንዱን <ግራስሆፐርስ> ክለብ በአሰልጣኝነት ለመምራት ተስማማ፡፡ በዙሪክ ቀጣዮቹን ዘጠኝ ዓመታት በእርጋታ ተደላድሎ ተቀመጠ፡፡ በካርል ራፕን ከመተካቱ በፊትም ከክለቡ ጋር ሦስት የሊግ ዋንጫዎችንና አራት የጥሎ ማለፍ ድሎችን ተጎናጸፈ፡፡ አሰልጣኙ በጀርመን ሰንብቶ አልያም የዳኑቢያኑ ዓይነተኛ 2-3-5 ፎርሜሽን በዋነኝነት ወደሚተገበርበት ሃንጋሪ ተመልሶ ቢሆን ኖሮ ነገሮች ከዚህ የተለዩ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ በሲውዘርላንድ ኩርስችነር በW-M ፎርሜሽን አዎንታዊ ጎኖች እንዲሁም ከዚሁ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ ግትር አደራደር በሚውጣጡ ሌሎች ፎርሜሽኖች (Variants) ከፍተኛ እምነት አሳደረ፡፡ እናም ፓድሊሃ በ1937 ኩርስችነርን ቀርቦ ካነጋገረው በኋላ የብራዚሎች እግርኳስ ላይ አብዮት ያስጀመረውን ፎርሜሽን ከአሰልጣኙ ጋር አብሮ ወደ ሪዮ ዲ ጂኔይሮ ወሰደ።

‘የብራዚሎች እግርኳስ ልክ እንደ እንግሊዞቹ የወግ አጥባቂነት ባህርይ ይታይበት ነበር፡፡’ ብሎ ማሰብ በራሱ የዋህነት ይመስላል፡፡ ኩርስችነር የብራዚልን ምድር ሲረግጥ የፍላሚንጎ የመሃል ተከላካይ አማካይ (Center-Half) ፋውስቶ ዶስ ሳንቶስ ነበር፡፡ “ጥቁሩ ተዓምረኛ” እየተባለ ይጠራ የነበረው ፋውስቶ በጨዋታዎች ላይ የራሱን ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ድንቅ የቴክኒክ ቄንጠኛም ነበር፡፡ በብራዚል እግርኳስ ባህል ውስጥ የመሃል-ተከላካይ አማካዮችን (Centre-Half) ከላይ፥ የመስመር ተከላካዮችን (Fullb-Backs) ከታች የሚያስቀምጥ በግልፅ የሚታወቅ የመጫወቻ ቦታዎች ተዋረድ (Positioning Hierarchy) ስለተንሰራፋ ፋውስቶ ወደኋላ አፈግፍጎ የመከላከል ሥፍራ ተጫዋች የሚሆንበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ ለኩርስችነር አሳወቀ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ደጋፊዎች እና ጋዜጠኞችም የተለያየ አቋም አሳዩ፡፡ ፓዲልሃ መሃል ገብቶ በተጫዋቹና አሰልጣኙ መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት መፍትሄ አበጀ፤ ለሥነምግባር ጥሰቱ ፋውስቶን ቀጣው፤ ለሚከፈለው ሥራ የሚጠበቅበትን ብቻ እንዲወጣም አስጠነቀቀው፡፡ ኩርስችነር እግርኳስን ለማዘመን ጠንክሮ የሚሰራ፣ ከጊዜው ጋርም ተመሳስሎ የሚኖርና የማይበገር ባለሙያ ስለመሆኑ ቢያንስ ይህ ውሳኔው ማመሳከሪያ ሆነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኙ ለወግ- አጥባቂነት አቤቱታ፣ የግለኝነት ባህርይ እንዲሁም ለተጫዋቾቹ የተናጠል ፍላጎት ቦታ የመስጠት አድርባይነት አልነበረበትም፡፡

በእርግጥ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የመላመድ ሒደቱ ያን ያህል ቀላል አልሆነለትም፡፡ ከሃሳብ አፍላቂዎች ጥልቅና ተራማጅ እይታዎች ሙሉ በሙሉ ጥንቅቅ ብለው የሚመነጩት አልፎ አልፎ ሲሆን በእግርኳስ የእሳቤ ፈጠራ ክህሎት ያላቸው ሰዎችም ቁጥር አናሳ ነበር፡፡ እነዚህ ከባቢያዊ ሁኔታዎች የራሳቸውን ተጽእኖ አሳርፈዋል፡፡ አሳፍ እንደሚለው ከሆነ ኩርስችነር ወደ ክለቡ እንደመጣ ባየው የህክምና ፋሲሊቲዎች እጅጉን ደንግጧል፡፡ምንም እንኳ በመሰረታዊ የታክቲክ አክራሪነት ባህርዩ ቢታወቅም የመጀመሪያ ውሳኔው ተጫዋቾቹ በፍጥነት የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ ማዘዙ ነበር፡፡ በወቅቱ ፋውስቶ የመጀመሪያ ደረጃ የሳምባ ነቀርሳ ህመም ምልክቶች ተገኙበት፤ ስቃዩ ጠንቶበትም በሽታው ከሁለት ዓመት በኋላ የተጫዋቹን ህይወት ቀጠፈ፡፡ ፋውስቶ ቀድሞ ከሚጫወትበት ቦታው ወደ ኋላ ባፈገፈገ ሚና እንዲጫወት የተወሰነበት ምናልባት የጤናው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ በመሄዱ ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ተጫዋቹ ህመሙ ባይብስበት ኖሮ ኩርስችነር የጥንቱን 2-3-5 ፎርሜሽን የሙጥኝ እንዲል ይገደዳል? ወይስ ፋውስቶን በመሃል ተከላካይነት (Half-Back) ተጠቅሞ ሌላ ተጫዋችን በጥብቅ የመሃል-ተከላካይ አማካይነት ሚና (Defensive Centre-Half) እንዲሰለፍ በማድረግ W-M ፎርሜሽንን ይተገብራል? ይሆን የነበረውን ለመገመት እጅግ አዳጋች ነው፡፡

ኩርስችነር ለ 3-2-2-3 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር (W-M) የነበረው አረዳድ በብሪታኒያ ከተለመደው ወጣ ያለ ይመስላል፡፡ በሲውዘርላንድ እግርኳስ አጨዋወት ባህል ውስጥ ያደገና ስልቱን የተማረ ቢሆንም እንደ <ዳኑቢያን>ነቱ ለኸርቢ ሮበርትስ አይነቱ ቋሚ ተከላካይ ተጫዋች (Stopper) የመሃል ተከላካይ- አማካይነቱን (Centre-Half) ኃላፊነት ወይም ሌላ የሜዳ ላይ ሚና ለመስጠት አልፈለቀደም፡፡ አሰልጣኙ ፋውስቶ ዶስ ሳንቶስን ቢይዝም ብራዚላዊው ተጫዋች ኩርስችነር ለሚፈልገው የአጨዋወት ዘይቤ አይነተኛ አማራጭ አልነበረም፡፡ ኩርስችነርና ብራዚሎች W-M ፎርሜሽንን የሚያዩት ከቪቶሪዮ ፖዞው <ሜትዶ> ሥልት ጋር በማቀራረብ ነበር፡፡ የመሃል ተከላካይ-አማካዩ (Centre-Half) የመስመር አማካዮች (Half-Backs) ከሚሰለፉበት የስፋት መስመር ወደኋላ ጥቂት አፈግፍጎ እና ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ወደፊት ተጠግቶ የ ቅርጽን በያዘው አሰላለፍ የሚታወቀው ይህ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ኩርስችነርና ብራዚላውያን ለ3-2-2-3 ፎርሜሽን የተጠጋ መዋቅር ስለመሆኑ ያስቡ ነበር፡፡ ሶተር እንደሚያስረዳውም በወቅቱ በብራዚሎች ዘንድ ዘዴው ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጥ እንደሆነ ተደርጎ ቢታሰብም የእንግሊዞቹን ያህል ጥብቅና በአሉታዊ የአጨዋወት ሥልት የሚጠቀስ አልነበረም፡፡

ድብቅ የኋላ-ታሪክ የነበረው ኩርስችነር በብራዚል መጨረሻውም አላማረም፤ እያደር የአሰልጣኝነት ተጽዕኖው እየወረደ፤ ተሰሚነቱም እየቀነሰ ሄደ፡፡ የቀድሞው የፍላሚንጎ ተጫዋችና የኩርስችነር ረዳት ፍላቪዮ ኮስታ በሃንጋሪያዊው አሰልጣኝ የታየውን የፖርቹጊዝ ቋንቋ ድክመት እንደ ትልቅ እንከን እያስወሰደበት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ኩርስችነርን ያንኳስሰው ጀመር፡፡ የ ፎርሜሽንን ህጸጾች እየነቀሰም ያስቸግረውና የአሰልጣኙን መልዕክት ይንቅ ገባ፡፡ በንትርኩ መሃልም በገዛ ፈቃዱ ፋውስቶን ወደ መደበኛ ቦታው መለሰው፤ ነገርግን የክለቡ ውጤት አሽቆለቆለ፡፡ ፍላሚንጎዎች በሃያ ስድስት ጨዋታዎች ሰማንያ ሶስት ግቦችን ቢያስቆጥሩም በካሪዮካ ሻምፒዮና በቀንደኛ ተቀናቃኛቸው ፍሎሚኒሴዎች ተቀድመው ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ፡፡ የሃገሪቱ ጋዜጦችም በኩርስችነር የጨዋታ ዘይቤና ስብዕና ላይ በሰፊው ተሳለቁበት፡፡ በ1938 የውድድር ዘመን የመጀመሪያ ጨዋታ በስታዲዮ ደ ጋቪያ የተደረገ የመክፈቻ ፍልሚያ ፍላሚንጎዎች በቫስኮደጋማዎች 2-0 ተረቱ፤ እናም ኩርስችነር ላይ የቅጣት በትር አረፈ፤ ወዲያውኑ ከክለቡ እንዲባረር ተደረገ፤ ምክትሉ ፍላቪዮ ኮስታም ተካው፡፡

በብራዚል የሚታወቅና አድናቆት የሚቸረው ሰው ሆኖ ባለመገኘቱ፣ ሃሳቡን የተረዱት ጥቂቶች ብቻ የነበሩ በመሆናቸው እና በሃገሪቱ የተሳካ ጊዜ ካለማሳለፉ አንጻር ብዙዎች ኩርስችነር ወደ አውሮፓ ሊመለስ ይችላል ሲሉ ገመቱ፡፡ ይሁን እንጂ የሚክሎስ ኾርዚ መንግስት ከናዚ ጀርመን ጋር ይፋዊ የኃብረት ስምምነት በማወጁ ምናልባት በቡዳፔስት ጸረ-አይሁዳውያን ዘመቻ ይፋፋማል በሚል ስጋት ኩርስችነር በሪዮ ቆየ፡፡ ከዚያም በ1939 የ<ቦታፎጎ> አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡ ነገርግን በክለቡ ብዙ አልዘለቀም፤ በቀጣዩ ዓመት ቡድኑን ለቀቀ፡፡ በ1941 በረቂቅ ቫይረስ ተጠቅቶ ለሞት ተዳረገ፡፡

የአሰልጣኙ ተቀባይነት ላይ የተነሱ ጥርጣሬዎች በሙሉ እንዳሉ ሆነውም ኩርስችነር በ1938ቱ የፈረንሳዩ የአለም ዋንጫ ለወቅቱ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አድኼማር ፒዬንታ አማካሪ ሆኖ እንዲያገለግል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለያዩ ጋዜጦች ዘጋቢ ሆኖ ይሰራ የነበረው ቶማስ ማዞኒ በፓሪሱ የስታድ ደ ኮለምበስ ስታዲየም የፈረንሳይ እና እንግሊዝን የወዳጅነት ግጥሚያ ለመታደም ሄደ፡፡ እንግሊዞቹ ጨዋታውን በቀላሉ ተቆጣጥረው 4-2 አሸነፉ፤ ማዞኒ የድንጋጤ ይዘት ባለው ቃና እንግሊዞች ሙሉውን ጊዜ ሶስት ተከላካዮች ይዘው እንደተጫወቱ ጻፈ፤ ሐሳቡን ሲደመድምም በብራዚል እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ፈጽሞ ሊወደድ እንደማይችል አሳወቀ፡፡

በጊዜው ለውጦች እየታዩ ነበር፡፡ በ1938ቱ የአለም ዋንጫ ብራዚል ማርቲን ሲልቬራያን የማጥቃት ሒደቱን የሚመራ የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Attacking Centre-Half) አድርጋ ተጠቀመች፤ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚጫወቱት ሁለቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside Forwards) ሮሜውና ፔራይኮ በሜዳው ቁመት ጥቂት ሜትሮች ወደኋላ ተመልሰው <ፖንታ ደ ላንሳ/Ponta da lanca> የተባለውን የሜዳ ላይ እንግዳ ሚና መወጣት ጀመሩ፡፡ አዲሱ የተጫዋቾቹ ኃላፊነት ግርድፍ ትርጉም <የማጥቃት መዋቅሩ የላይኛው ጫፍ> የሚል ትርጉም ይሰጣል፤ ለጥቂት ጊዜ በሒደት ላይ የነበረው ሽግሽግ እየተለመደ ሄደ፡፡ በ1930ዎቹ መጨረሻ 2-3-5 ፎርሜሽንን የሚጠቀሙ ሃገራት አምስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች በመደዳ (በአንድ የጎንዮሽ መስመር ላይ) ተጣበው ሲጫወቱ አስተዋሉ፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍና ኦስትሪያዎች በፊተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ነጻ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ማቲያስ ሲንድለር ወደኋላ አፈግፍጎ መጫወቱን ቀጠለ፤ በአርጀንቲና እና ኡሯጓይ ደግሞ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚንቀሳቀሱት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) ከመደበኛ ቦታቸው ይልቅ ከጥልቅ የሜዳ ክፍል እየተነሱ መጫወታቸው የተለመደ ሆነ፡፡ ሲልቬይራ ከሉዊዚቶ ሞንቲም በላይ ማጥቃት ላይ የሚያተኩር ተጫዋች ነበር፡፡ ያም ሆኖ በ1938 የብራዚሎች ፎርሜሽን ከቪቶሪዮ ፖዞ <ሜትዶ> ስልት መጠነኛ ልዩነት ነበረው፡፡

በእርግጥ ዘይቤው ብራዚሎች በውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ እንዲደርሱ አግዟቸዋል፡፡ ከቶርናመንቱ በኋላ በተሰራው ጥናት የወቅቱ ጋዜጠኛና በ1969 የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሆነው ጃኦ ሳልዳንሃ ብራዚሎች ሶስተኛው ተከላካይን (Third Back) በሚያካትተው የአጨዋወት ሥርዓት ከዚያ የበለጠ ርቀት ሊጓዙ ይችሉ እንደነበር ይገልጻል፡፡ ምንም ተባለ ምን በዓለም ዋንጫው ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች አስር ግቦችን አስተናግደዋል፤ ሶስቱ በፍጹም ቅጣት ምት የተቆጠሩባቸው ነበሩ፡፡ ሳልዳንሃ ይህ የጎል መጠን ከሚፈለገው ተጫዋች በላይ የያዘው የተከላካይ ክፍል (Over-manned Defence) በጫና ውስጥ ሲሆን በቀላሉ እንደሚሸበር ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡