ሲዳማ ቡና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

የዝውውር ገበያውን የነባር ተጫዋቾችን ውል በማራዘም የተቀላቀለው ሲዳማ ቡና አማካዮቹ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን እና ብርሀኑ አሻሞን በሁለት ዓመት ውል አስፈርሟል።

የቀድሞው የኤሌክትሪክ ተጫዋች ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለቆ ወደ ወደ ሀዋሳ ከተማ ካመራ በኋላ በክለቡ ሁለት መልካም ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን ከሀዋሳ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ ሌላው የከተማው ክለብ አምርቷል።

ሌላው ሲዳማን የተቀላቀለው ብርሀኑ አሻሞ ነው። የእግርኳስ ህይወቱን ከሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን ጀምሮ በዋናው ቡድን መጫወት ከቻለ በኋላ ወደ ደደቢት አቅንቶ መጫወትም ችሏል። ተጫዋቹ ደደቢትን በመልቀቅ ወደ ወልዋሎ አምርቶ እስከ ዘንድሮ የውድድር ዓመት በተከላካይ አማካይ ስፍራ ላይ በቋሚነት ከተጫወተ በኋላ ሲዳማን ቀላቅሏል። በቡድኑም ለተሰላፊነት ከዮሴፍ ዮሐንስ ጋር ይፎካከራል።

ሁለቱን ተጫዋቾች በአንድ አመት ውል ያስፈረመው ክለቡ በቀጣዩ ቀናትም እስከ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾች ለማስፈረም እና የቡድኑን ወሳኝ ተጫዋቾችን ውል ለማራዘም እንቅስቃሴ ላይ መሆኑን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡