ጅማ አባጅፋር ተጫዋቾችን ማስፈረም ጀምሯል

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸውን ዋና አሰልጣኝ አድርገው ከሾሙ በኃላ ወደ ዝውውሩ ለመግባት የዘገዩት አባ ጅፋሮች የአምስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀዋል።

በጅማ አባቡና እና በአዳማ ከተማ ያሰለፈው አጥቂው ብዙዓየሁ እንደሻው ለጅማ አባ ጅፋር ፊርማውን ያኖረ የመጀመርያ ተጫዋች ሆኗል። ብዙዓየው በ2010 በከፍተኛ ሊግ ከጅማ አባቡና ጋር የተሳካ ቆይታ በማድረግ የውድድር ዓመቱ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀ ሲሆን ወደ አዳማ ከተማ ካመራ በኃላ በተለያዩ ጉዳዮች ከቡድኑ ጋር በገባው ውዝግብ ምክንያት የታሰበውን ያህል ቆይታ ሳያደርግ መለያየቱ ይታወቃል።

2009 ጅማ አባ ቡና ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ከነበሩት መካከል አንዱ የነበረው እና ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለው፣ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከሰበታ ከነማ ጋር ቆይታ ያደረገው የግራ መስመር አጥቂው ሱራፌል ዐወል ለአባ ጅፋሮች ፊርማውን ያኖረ ሁለተኛ ተጫዋች ሆኗል።

ፈጣኑ የመስመር ተከላካይ ተመስገን ደረሰ ለአባጅፋር ለመጫወት የተስማማ ሦስተኛ ተጫዋች ነው። ተመስገን በጅማ አባ ቡና ጥሩ አቅሙን ያሳየ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር።

አማኑኤል ጌታቸው ከጅማ አባቡና እና በግብ ጠባቂው ሰኢድ ይመር ከአርባምንጭ ከተማ። ጅማ አባጅፋርን የተቀላቀሉ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በቀጣዩ ቀናት የዝውውር እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው በመቀጠል ተጨማሪ ተጫዋቾችን ያስፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ