የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 1-1 ሀዲያ ሆሳዕና

ዛሬ በአዳማ ከተማ ዋንጫ ባለሜዳው አዳማ ከተማ በተስፋዬ ነጋሽ እንዲሁም የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ሀዲያ ሆሳዕና በሄኖክ አርፍጮ ግቦች አቻ ተለያይተዋል። ከጨዋታው በኋላም የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ቡድናችን ዛሬ ያሳየው እንቅስቅሴ እየተሻሸለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።” ደጉ ዱቡሞ

ስለጨዋታው እንቅስቃሴ

“በእንቅስቃሴው ቡድናችን ዛሬ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን አድርጓል። ተጋጣሚያችን የሚፈልገውን ነገር እንዳይተግብር በማድረግ እኛ የምንፈልገውን ማድረግ ችለናል። በአጠቃላይ ቡድናችን ዛሬ ያሳየው እንቅስቅሴ እየተሻሸለ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።”

አጋጣሚዎችን ስላለመጠቀም

“ይህ ችግር አሁንም አለ ፤ ይህም ዋጋ አስከፍሎናል። በተቻለን መጠን ጠንክረን ሰርተን ከስር መሰረቱ እንፈታዋለን።”

በቀኝ መስመር ስላደለው የቡድኑ እንቅስቃሴ

“አዎ በቀኝ መስመር አድልተን እያጠቃን በግራውም እንዲሁ ክፍተት ላለመተው ነበር አስበን የገባነው። እንዳያችሁትም ፍልስፍናችን ሰርቶልን ግብ ያስቆጠርነውም ሆነ አብዛኞቹን የግብ ዕድሎች የፈጠርነው ከዛ በሚነሱ ኳሶች ነበር።”

” እንደመጀመሪያ ጨዋታችን እኔ ደስተኛ ነኝ ” ግርማ ታደሰ

ስለቡድኑ እንቅስቃሴ

“ቡድኑ ያያችሁት ነው ፤ ኳስ ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋል። ወደራሱ ሜዳ የሚመጣውን በአግባቡ ይቆጣጠራል። እንደመጀመሪያ ጨዋታችን እኔ ደስተኛ ነኝ ፤ በቀጣይ ከዚህ ተሽለን ብቅ እንላለን።”

ስለማጥቃት እንቅስቃሴው መዳከም

“እውነት ነው ፤ ይህን ችግር እንፈታዋለን። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚቻል ፍንጭ አይተናል። በቀጣይ ይህን እና ሌሎች ችግሮቻችንን ፈትተን ብቅ እንላለን።”


© ሶከር ኢትዮጵያ