የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-0 ፋሲል ከነማ

በመጀመርያው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዳማ ከተማን ከ ፋሲል ከነማ ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ያገኘነውን አጋጣሚ ያለመጠቀም ክፍተቶች ነበሩ” የአዳማ ከተማ ም/አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ

የማግባት አጋጣሚ አለመጠቀም

ዛሬ ያየነው ይሄን ነው። ያገኘነውን አጋጣሚ ያለመጠቀም ክፍተቶች ነበሩ። በቀጣይ አስተካክለን እንመጣለን። እንቅስቃሴያችን ግን ጥሩ ነበር።

የተጫዋች ቅያሪ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ መቀዛቀዝ አስከትሏል?

እኛ አስበን የነበረው ተስፋዬ እና እስማኤልን በማስገባት በመስመር ለማጥቃት ነው። በሦስት አጥቂ የነበረውን ተስፋዬን በማስገባት አራተኛ የማጥቂያ መንገድ ለመፍጠር ነበር። እንዳሰብነው በተወሰነ መልኩ ጥሩ ነበር።

“አቻ ውጤት ፈልገን ወደ ሜዳ አልገባንም” ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ

ጨዋታው ጥሩ ነው። ከሁሉም በላይ እጅግ በጣም ደስ ያለኝ የህዝቡ ወደ ድሮ ሠላማዊ ፍቅር በመመለስ በጨዋነት መደገፉ ነው። በቀጣይም የፕሪምር ሊጉ ጨዋታዎች በዚህ መልኩ እንዲቀጥል ጥሩ ጅማሮ ነው። ወደ ጨዋታው ስመለስ ባሳለፍነው ጨዋታ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ ትልቅ ተጋድሎ ነው ያደረግነው። ማሸነፋችን የፈጠረው መነሳሳት እንዳለ ሆኖ በተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ በአካልም በስነ ልቦናውም የፈጠረው ጫና ነበር። ጥሩ ብቃታችንን አሳየን ባይባልም ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ነገር አሳይተናል። ትልቁ ነገር ሻምፒዮን እንሆናለን ብለህ ስታስብ በእያንዳንዱ ከሜዳ ውጭ የምታደርገው ጨዋታ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። አዳማ ትልቅ ቡድን ነው፤ ዛሬ ነጥብ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። በሜዳችን ለምናደርገው ጨዋታ ትልቅ መነሳሳት ነው።

በጨዋታው አቻ ውጤት ፈልገው ነበር ?

አቻ ውጤት ፈልገን ወደ ሜዳ አልገባንም። ነገር ግን ያገኘነው ነጥብ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ከምንም ይሻላል። ማሸነፍ ትልቅ ነገር እንዳለው ሁሉ አቻ መውጣትም ለቀጣይ ውድድር ያነሳሳል። ከትልቅ ውድድር መጥተን ያውም ከጠንካራ ቡድን ጋር ነጥብ መጋራት መልካም ነው ብዬ አስባለው።

የሱራፌል ዳኛቸው ቅያሪ አቻ ውጤት በማሰብ ይሆን?

እንደውም ሱራፌልን እዛው እረፍት ላይ ላስቀረው ነበር። ግን ትንሽ ሞክር ብዬ ህመም ድካም እየተሰማው ነው ያጫወትኩት እንጂ ውጤት ለማስጠበቅ አይደለም። በዛብህን ወደ ፊት እንዲያጠቃ በማድረግ ሐብታሙ ተከስተን ወደ ኃላ አድርገን ነው ያጫወትነው።

በአዳማ ከተማ ዋንጫ እና በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ላይ ቡድኑ ከነበረው ፈጣን እንቅስቃሴ ዛሬ ወረድ ብሎ የመታየቱ ምክንያት ምድነው ?

በባለፉት ጨዋታዎች ላይ እያንዳንዱ ያደረገው መሰዋዕትነት ቀላል አልነበረም። ያም ቢሆን ፕሪሚየር ሊጉን በጥሩ መንገድ ካልጀመርከው ዕቅድ ማቀድ ብቻ ትርጉም የለውም። ስለዚህ ከጨዋታ ጨዋታ ራሳችንን እያሻሻልን እንመጣለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ