የመጀመሪያ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዐበይት ትኩረቶች

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ትላንት እና ከትላንት በስቲያ በተደረጉ ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጓል፡፡ ከ2012 የመክፈቻ ሳምንት ጨዋታዎች የታዘብናቸውና ትኩረት ከሚሹ ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹን በዚህ መልኩ አስቀምጠናቸዋል።

የክለቦቻችን ማለያ ነገር

በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ የእግርኳስ ክለቦች አዲስ የውድድር ዘመን ሲጀምሩ ከቀደመው ዓመት መለያቸው የይዘት ማሻሻያዎችን በማድረግ አዲስ መለያን ይዘው መቅረብ የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ለቡድኑ አዲስ ገፅታ ከማላበሱ በተጨማሪ የማልያ ሽያጭ ገቢን በመጨመር ለክለቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል

በሀገራችን ያለው ግን የተገላቢጦሽ ናቸው፡፡ አመዛኞቹ ክለቦች የክለቡን ማንነት የማይገልፅ ማልያ በዘፈቀደ ከመጠቀም ጀምሮ በአዲስ የውድድር ዘመን አዲስ ማልያ የመጠቀም ልምድ የላቸውም። በአንደኛው ሳምንትም አብዛኞቹ ክለቦች ባለፉት ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የነበሩባቸው መለያዎችን ዳግም ይዘው ቀርበዋል፡፡

ከሰበታ ከተማ፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ስሑል ሽረ እና ድሬዳዋ ከተማ ውጭ ያሉት ክለቦች ተመሳሳይ የሆነ ማለያዎችን ይዘው ሲቀርቡ ከተጠቀሱት ክለቦች መካከልም ድሬዳዋ ከተማ በጨዋታ ቀናት ሲጠቀምበት የማይስተዋል መለያን የተጠቀመ ሲሆን የመቐለዎች ደግሞ እምብዛም ከቀደሙት ጋር በይዘትም ሆነ በቀለም ስብጥር የማይቀራረብ መለያን ለብሰው ተመልክተናል፡

ተስፈኛው ሰመረ እና ተገማች ያልሆነው ወልዋሎ

ዐምና ከክለቡ ሁለተኛ ቡድን ወደ ዋናው ቡድን በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አማካይነት ያደገው ሰመረ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እና በመጀመሪያ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳየው እንቅስቃሴ ዘንድሮ በሊጉ ከወዲሁ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበት ተጫዋች ሆኗል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት በ56ኛውና 90ኛው ደቂቃ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው ሰመረ ዘንድሮ በሊጎ አንዳች ነገር ያስመለክተናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ወልዋሎ በውድድር ዘመኑ ለግምት አስቸጋሪ ቡድን ይዞ እንደቀረበ ማሳያ የሆነ ሳምንት አሳልፏል፡፡ ቡድኑ ሰበታ ከተማን በረታበት ጨዋታ ላይ በመጀመሪያ 11 ውስጥ 7 የመከላከል ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ይዞ መግባቱ ግርምትን የሚያጭር አጋጣሚ ነበር። ከዚህ ቀደም በሌሎች ሚናዎች የምናውቃቸው ተጫዋቾች በተቃራኒው የተለዩ ሚናዎችን ይዘው ሲገቡም ተስተውሏል፡፡

ይህ የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ተግባር ቡድኑ ተገማች እንዳይሆን ያለመ ከሆነ በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ቢሆንም በየጨዋታዎቹ የተጫዋቾችን ሚና መለዋወጡ ተጫዋቾች ለሚና ግርታ እንዲጋለጡ እና በተፈጥሯዊ ቦታቸው ላይ የሚሰጡትን የላቀ አገልግሎት ከመገደብ ባሻገር እንደተጫዋችም እድገታቸውን ሊገታ የሚችል ነው።

በጎ ጅምር በክለቦች የደጋፊዎች መካከል

በስታዲየም ነውጦች ክፉኛ ሲታመስ የቆየው የኢትዮጵያ እግርኳስ ከሰሞኑ መጠነኛ የመሻሻል ምልክቶች ስለመኖራቸው ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች መካከል የታየው ሰላማዊ የሆነ ድጋፍ አሁን ደግሞ በወላይታ ድቻና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ተደግሟል።

ከሜዳ ውጭ ባሉ ጉዳዮች የከረረ ጡዘት ውስጥ ገብተው የነበሩት የወላይታ ድቻና የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በትግራይ ዋንጫ የጀመሩት በጎ ጅምር ሶዶ ላይ ቀጥሎ ጨዋታው በሰላም ተጀምሮ በሰላም ተጠናቋል።

ዐምና በገለልተኛ ሜዳ የተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዘንድሮ በሰላም መካሄዱ በቀጣይ በከፍተኛ ስጋት ለተወጠረው እግርኳሳችን መጠነኛ የመተንፈሻ ጊዜን የሰጠ ድርጊት ሲሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባራት በሌሎች ስታዲየሞች ይደገማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሜዳዎች ጉዳይ

አዲስ የተቋቋመው የሊጉ ዐቢይ ኮሚቴ ከሳምንታት በፊት የሊጉ ተሳታፊ ክለቦችን የመጫወቻ ሜዳ ሁኔታ ተዟዙሮ በመገምገም የሊጉን ውድድር ለማድረግ ብቁ አይደሉም ያላቸው ሜዳዎችን አስከማገድ የደረሰ ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። በዚህም ሰበታ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ስሑል ሽረ እና ወልዋሎ መመዘኛውን እስኪያሟሉ የተወሰኑ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎቻቸውን በተለዋጭነት ባስመዘገቡት ሜዳ እንዲያካሂዱ ውሳኔ መሰጠቱ ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን እሁድ በአንደኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ በሜዳው ሲዳማ ቡናን ባስተናገደበት ጨዋታ ለወትሮም ቢሆን ምቹ ባለመሆኑ ጥያቄ የሚነሳበት የሶዶ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ጉዳይ የትኩረት ማዕከል ነበር። ባለሜዳዎቹ ድቻዎች 2ለ0 ባሸነፉበት በዚሁ ጨዋታ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው የሜዳውን አስቸጋሪነት በስፋት አንስተዋል።

ይህም ጉዳይ የዐቢይ ኮሚቴው ምልከታ ከደጋፊዎች ደህንነትና ፀጥታ አንፃር የተቃኘ ስለመሆኑ ፍንጭ የሰጠ አጋጣሚ ነበር።

መፍትሄ ያጣው የክለቦች ደካማ የውስጥ አስተዳደር

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሆኑት ሰበታ ከተማ (4) እና ጅማ አባጅፋር (4) በክረምቱ የዝውውር መስኮት ያስፈረሟቸውን የውጭ ዜጋ ተጫዋቾች የመኖሪያ ፍቃዳቸው በጊዜ ባለመጠናቀቁ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሌሎች ክለቦች ከውጭ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ጉዳያቸው በወቅቱ ተጠናቆ ለክለባቸው ግልጋሎት መስጠት ሲችሉ የሁለቱ ክለቦች ግን የተጫዋቾችን አገልግሎት በአስተዳደራዊ ቸልተኝነት የተነሳ በወቅቱ መጨረስ ባለመቻላቸው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

ይህም ሁኔታ በቀጣይ በፍጥነት የእርምት አርምጃ ተወስዶ መፈታት የሚገባው ጉዳይ ነው።

የዲሲፕሊን ቅጣትና አደናጋሪው አተገባበር

በመጀመሪያ ሳምንት ከተደረጉ ስምንት መርሐ-ግብሮች ውስጥ ሁለቱ ከዓምና በይደር በተላለፉ ቅጣቶች የተነሳ በዝግና ከሜዳ ውጭ ተከናውነዋል፡፡ በቀጣይ ሳምንትም ተመሳሳይ የዐምና የቅጣት ውሳኔዎች ይተገበራሉ።

መቐለ 70 እንደርታ ከሀዲያ ሆሳዕና ያደረጉት ጨዋታ ዓምና በ23ኛው ሳምንት ፋሲል ከደደቢት ባደረጉት ጨዋታ የመቐለን መለያ የለበሱ ተመልካቾች በተፈጠረ ሁከት ላይ ተስትፈዋል በሚል ክለቡ አንድ ጨዋታ ያለ ተመልካች ጨዋታ እንዲያደርግ ቅጣት ቢተላለፍበትም ቅጣቱ ዓምና ተፈፃሚ መሆን ሲገባው ተንከባሎ ለዘንድሮ ተላልፏል፡፡

በተመሳሳይ ጅማ አባጅፋር በ26ኛው ሳምንት በሜዳው ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በነበረ ጨዋታ በተፈጠረ የስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት ሁለት በሜዳቸው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ከሜዳ ውጭ እንዲያደርጉ ቅጣት ቢተላለፍም በወቅቱ ተፈፃሚ መሆን ባለመቻሉ ዘንድሮ የትላንቱን ጨምሮ ቡድኑ ቀጣይ ጨዋታውንም በገለልተኛ ሜዳ የሚያደርግ ይሆናል።

አስገራሚው ነገር ከዚህ የቅጣት አተገባበር ጋር በተያያዘ ፌዴሬሽኑ ለዓመታት የዕርምት እርምጃ ሳይወስድበት የቆየ ድክመቱ ሆኖ መቆየቱ ነው፡፡ ቅጣት የሚተላለፈው ጥፋት አጥፍቷል ተብሎ የተቀጣን አካል ለማስተማር ሆኖ ሳለ በተቀመጠው ደንብ መሠረት በወቅቱ ቅጣቱን ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ውሳኔው በቅድመ ሁኔታ የሚሻርበት ወይም በይደር የሚቆይበት አካሄድ ቅጣቶች እንዳይፈሩና ተመሳሳይ ጥፋቶችን ለማድረስ የልብ ልብ የሚሰጡ በመሆኑ በቀጣይ ሊታረሙ ይገባቸዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ