ሎዛ አበራ በማልታ ሊግ ያስቆጠረቻቸውን ግቦች ቁጥር አስር አደረሰች

በማልታ የተሳካ ጊዜ በማሳለፍ የምትገኘው ሎዛ አበራ ዛሬ ቡድኗ ቢርኪርካራ ራይደርስን 8-1 ባሸነፈበት ጨዋታ በሃያ ሰባተኛው እና ሰባ አምስተኛው ደቂቃዎች ሁለት ግቦች አስቆጥራ በማልታ ሊግ ያስቆጠረቻቸው ግቦችን ቁጥር አስር አድርሳለች።

በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ወደ ማልታ አቅንታ በመጀመርያው ጨዋታዋ ሄበርንያንስ ላይ ሁለት ግብ በማስቆጠር ዓመቱን የጀመረችው ሎዛ እስካሁን በተደረጉ 6 የሊግ ጨዋታዎች አስር ግቦች ስታስቆጥር ከኮርክ ሲቲ በተደረገ የአቋም መለኪያ ጨዋታም አንድ ግብ ማስቆጠሯ ይታወሳል።

ሎዛ አበራ ከሞስታ ጋር በተደረገ ጨዋታ ሐት-ትሪክ ስትሰራ ከኪርኮፕ፣ ሄበርንያንስ እና ራይደርስ ጋር በተረጉ ጨዋታዎች በሶስቱም ጨዋታዎች ሁለት ሁለት ግብ በማስቆጠር በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች በእያንዳንዳቸው አንድ ግብ አስቆጥራለች።

ከምጋር ዩናይትድ ጋር በተደረገው ጨዋታ ብቻ የተጋጣሚን ግብ ሳትደፍር የወጣችው አጥቂዋ በቢርኪርካራ ቆይታዋ በሁሉም ጨዋታዎች ሙሉ ዘጠና ደቂቃ ቡድኗን አገልግላለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ